ከቅዱስ ጊዮርጊስ ታዳጊ ቡድን የተገኘው እና በአሁኑ ሰአት ለባህርዳር ከተማ በመስመር አማካይነት በመጫወት ላይ የሚገኘው ሚኪያስ ግርማ ለሙከራ ወደ ታይላንድ እንደሚያቀና ተሰምቷል።
አሁን አሁን በሀገራችን ውስጥ ያሉ ተጨዋቾች ወደ ውጭ እየወጡ የመጫወት ዕድልን ሲያገኙ ይታያል። በግብፅ ሊግ የሚገኙት ሽመልስ በቀለ እና ኡመድ ኡኩሪ እንዲሁም በአልባኒያ የሚጫወተው ቢኒያም በላይ ተጠቃሾች ናቸው። አሁን ደግሞ በቀኝ መስመር ተመላሽነት ከቅዱስ ጊዮርጊስ ታዳጊ ቡድን በመነሳት ከአምና ጀምሮ የከፍተኛ ሊጉ ባህርዳር ከተማን እያገለገለ የሚገኘው ሚኪያስ ግርማ ቀጣዩ ለሙከራ ወደ ታይላንድ የሚያቀና ተጨዋች ሆኗል፡፡ ለ11 ቀናት ሙከራ ወደ ደቡብ ምስራቅ እስያዋ ሀገር የሚያመራው ተጨዋቹ ስለ ሁኔታው ለሶከር ኢትዮጵያ ሲናገር ” የፈለጉኝ ሁለት ክለቦች ናቸው። ይህን ዕድል ስላገኘውም ደስ ብሎኛል። በአግባቡ ለመጠቀምም በዝግጅት ላይ እገኛለው። ” ብሏል። እንደ ሶከር ኢትዮጵያ ምንጮች ከሆነም ተጨዋቹ ላይ ፍላጎት ካሳዩ ቡድኖች መካከል በሀገሪቷ የሊግ ውድድር 13ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጠው ቻይናት ሆረንቢል አንዱ ነው።
ከጋቶች ፓኖም ጋር ዴቪድ በሻህን በወኪልነት የሚጋራው ሚኪያስ ግርማ ነገ ማለዳ ወደ ታይላንድ የሚያመራ ሲሆን ሙከራውን በስኬት ካጠናቀቀ የአንድ አመት ውል ካለው ባህርዳር ከተማ ጋር በስምምነት እንደሚለያይ እና ካልተሳካለት ግን ዳግም ወደ ክለቡ እንደሚመለስ ሰምተናል፡፡