የአሰልጣኞች ገጽ | ወርቁ ደርገባ [የመጨረሻ ክፍል]

የአሰልጣኞቻችን የእግርኳስ አስተሳሰብ ፣ የስልጠና ሀሳብ ፣ የስራ ህይወት እና የውጤታማነት መንገድ ዙርያ ትኩረት በሚያደርገው ” የአሰልጣኞች ገጽ ” አምዳችን ካለፉት ሦስት ሳምንታት የቀጠለው የአሰልጣኝ ወርቁ ደርገባን የመጨረሻ ቃለ ምልልስ ይዘን ቀርበናል።

በዛሬው የክፍል አራት መሰናዷችን ስለ አሰልጣኝነት ስራ እና የክለቦች እንዲሁም የደጋፊዎች ተፅዕኖ አውግተናል። ለቃለ ምልልሱ እንዲያመችም ከ”አንቱ” ይልቅ “አንተ” በሚለው ተጠቅመናል።


ክፍል ሦስትን ማግኘት እዚህ ይጫኑ ፡ LINK


በሚልኪያስ አበራ እና አብርሀም ገብረማርያም


ከፕሪምየር ሊጉ በታች ባሉ ውድድሮች ማሰልጠን እጅግ በጣም ከባድ እንደሆነ ይነገራል፡፡ እንደዚህ ያከበዱት ምክንያቶች የትኞቹ ናቸው?


★ እጅግ በጣም ጠንካራ በሆነው ውድድር የምትፈልገውን ተጫዋች አለማግኘት፣ የመጫወቻ ሜዳዎቹ ዝቅተኛ የጥራት ደረጃና የጸጥታው ጉዳይ ውድድሩን ከባድ የሚያደርጉ ዐብይ ምክንያቶች ናቸው፡፡ ትልቁ ከባቢያዊ የስራ ተግዳሮት ያለው እዚያ ነው፡፡ እውነት ለመናገር በፕሪምየር ሊጉ መስራት ምንም አይከብድም፡፡ ጥሩ ጥሩ ተጫዋቾች ይኖሩሀል፤ ደህና ገንዘብ ይመደብልሀል፤ በንጽጽር የተሻለ ጥበቃ ይደረግልሀል-ታሰለጥናለህ፡፡ ብሔራዊ ሊግ ውስጥ ያለው ችግርም ከፍተኛ ነው፡፡ በምታሰለጥነው ክለብ በቂ ተጫዋቾች ሳይኖሩ አመራሩ ውጤት ይጠብቅብሀል፡፡ ሌላው ደግሞ ስፖርቱና ፖለቲካው አንድ ላይ እየታዩ በመሆኑ የከተማ አስተዳደር ቡድኖች እየበዙ መጥተዋል፡፡ በክለብ አመራርነት ቦታ ላይ የተቀመጡ ሰዎች እስከ ማስፈራራት የሚደርስ ተግባር ይፈጽማሉ፡፡ ቀደም ብዬ እንደገለጽኩላችሁ አስተዳደራዊ ስርዓቱ እንዲህ መሆን የለበትም፡፡ ይሄ እኮ ሙያ ነው! አመራሩ የሚመለከተው ጉዳይ አይደለም፡፡ “የኔ ከተማ ቡድን አሸነፈ!” ለማስባል ብቻ በሚደረጉት አላስፈላጊ ሁነቶች ብዙ ጥፋቶች ይፈጠራሉ፡፡ ይህም እግርኳሱ ላይ የሚፈጥረውን አሉታዊ ተጽእኖ ከባድ አድርጎታል፡፡ የእግርኳስ ሽንፈትን በጸጋ መቀበል አለብን፡፡ በከተማ ላይ የተመሰረተና እግርኳሳዊ ያልሆነ አላማ የሚያንጸባርቅ “የከተማ የበላይነትን” የሚመረኮዝ የአሸናፊነት ስሜት ጥሩ አይደለም፡፡ እኔ እንዲያውም እግርኳሱ እየተካሄደ የሚገኝበት ፎርማት ቢቀየር ደስ ይለኛል፡፡ የፕሪምየር ሊግ ደረጃችን ገና ነው፡፡ ይህን ውድድር ለማድረግ በብስለታዊ አመራር፣ በገንዘብ አቅም፣ በበቃ የሰው ኃይልና በሌሎችም ገና ጠንክረን አልተደራጀንም፡፡ ስለዚህ ቀደም ብለን እንደምናደርገው ከተሞች በራሳቸው ክልል ውስጥ በሚያደጓቸው ውድድሮች ከየከተሞቹ ሁለትም ይሁን ሶስት በደንብ ተፈትነው የሚወጡትን ቡድኖች አሰባስቦ በአንድ ቦታ ማጫወት ቢጀመር ትንሽ ሰላም ይገኛል፡፡ በአሁኑ ወቅት ክለቦች ለእግርኳሱ ብዙ ገንዘብ እያወጡ ምንም አይነት ጥቅም እያገኙበት ባለመሆኑ እድገት ሊያሳዩ አልቻሉም፡፡ ስለዚህ በድሮው ፎርማት ብንሄድ ‘ትንሽ ለውጥ ለማምጣት ያግዛል፡፡’ እላለሁ፡፡ የፎርማት ለውጥ በትክክል ያስፈልጋል፡፡


 

አሰልጣኞች ከታችኛው የሊግ እርከን ወደ ላይኛው ፕሪምየር ሊግ ቡድኖችን አሳድገውም በቀጣይነት ባሻሻሉት ክለብ ላይ የመቆየት እድል አይሰጣቸውም፡፡ ስራው ለሌላ የፕሪምየር ሊግ “ባለልምድ” አሰልጣኝ ይሰጣል፡፡ አሰልጣኞቹ በለፉበትና ውጤት ወይም ለውጥ ባመጡበት ክለብ እንዲቀጥሉ የቆይታ ጊዜ የማይሰጣቸው ለምንድን ነው?


★ ይሄ አሰራር የተለመደ ሆኗል፡፡ ማንም የማያውቀው ቡድን <ላይ> ሲደርስ ነው የሚታወቀው፡፡ ሩጫው እዚህ ጋር ይጀምራል፡፡ ኮሚቴ ውስጥ የተቀመጠው ሰውዬ ” ባክህ ወርቁ አይሰጠንም፤ ስለዚህ ከሌላኛው እንቀበል፡፡” ይልና እዚያው ካጠገብህ ስራህ ላይ ፈተና መሆን ይጀምራል፡፡ ጥሩነቱ እኔ በሐረር ቢራ ስሰራ በመጀመሪያው አመት ቡድኑ ወደ ላይ አደገና ሁለተኛ አመትም እንድቀጥል ተደረኩኝ፡፡ በውሌ መሰረትም ሁለቱን አመት ጨርሼ ወጣሁ፡፡ በአየር ኃይልም የነበረኝ ቆይታ ተመሳሳይ ነው፡፡ እዚህ ጋር ማንሳት የምፈልገው አንድ ቅሬታ አለኝ፡፡ ብዙውን ጊዜ “የተለያዩ ክለቦችን ወደ ፕሪምየር ሊጉ ያሳደጉ አሰልጣኞች እጅግ በጣም የተወሰኑ ናቸው!” በሚል ከአንድና ከሁለት ሰዎች በላይ እንዳልሆኑ ተደርጎ ይወራል፡፡ በዚህ ጉዳይ በጣም ነው የምገረመው። በቅርቡም እውቅና ለመስጠት በተደረገው የዮድ አቢሲኒያው ግብዣ ላይ የፌዴሬሽኑ ፕሬዘዳንት አቶ ጁነይዲ ባሻ በተገኙበት መድረክ ላይ ይህን ተናግሬያለው፡፡ “የቀድሞ አሰልጣኞችን ፕሮፋይል የሚያገላብጥ የለም፡፡” ብያለው፡፡ እኔ አራት ጊዜ ክለቦችን ወደ ሊጉ አሳድጌያለው፡፡ አንድም ይህን የሚናገር አካል አልገጠመኝም፡፡ ለምንድን ነው ያ ስራ ዋጋ የማይሰጠው? ሐረር ቢራን፣ አየር ኃይልን፣ አንበሳንና ደደቢትን አሰድጌያለሁ፡፡ በእርግጥ በደደቢት በመጨረሻ ሰዓት ላይ የተፈጠረውን ነገር አውቃለሁ፡፡ ከሲዳማ ጋር በነበረው ጨዋታ ወደ ላይ ለማለፍ በተደረገው ትንቅንቅ እስከ መደብደብ ደርሻለሁ፡፡ በዛ ጨዋታ ውጤት ነው ክለቡ ይግባኝ ጠይቆ ወደ ፕሪምየር ሊግ የገባው፡፡ እሱ <ለኔ የሚገባ ክሬዲት> ነው፡፡ ውድድሩን በ11 ነጥቦች እንመራ ነበር፤ ሲዳማም እንዲሁ ከሌላኛው ምድብ መሪ ሆኖ ተገናኘን፡፡ ከየመጣንበት ምድብ በቀጥታ ማለፍ እንጂ መገናኘት ስለማይኖርብን እነ ኮሎኔል አወል ይህን ጥያቄ አንስተው ክለቡ ወደ ፕሪምየር ሊጉ አለፈ፡፡ ያን እንግዲህ እኔ ነኝ የሰራሁት፡፡ ሆኖም እንዲህ አይነቱ ስራ የአንድ አሰልጣኝ ብቻ ተደርጎ በየሚዲያ ይወራል፡፡ እኛ የየት አገር ቡድን ነበር ያሰለጠነው? በሱማሊያ ይሆን እንዴ? እውነቴን እኮ ነው፡፡ ሁኔታው ሞራል ይነካል፤ እኔ ሄጄ ስለሰራሁት ነገር ማንንም መጠየቅ አልፈልግም፤ በራሱ ‘አንድ ቀን ይወጣል!’ ብዬ ነው የማስበው፡፡ እንዲሁ በቀላሉ ሳይሆን በድካም የሚገኝን ውጤት ነው፡፡ ከረጅም ጊዜ በፊት አንበሳ ትራንስፖርትን ወደ ላይ ያወጣሁትም እኔ ነኝ፡፡ በሆነ ጉዳይ ጣልቃ ሲገባብኝ ስራዬን በራሴ ፈቃድ እተዋለሁ እንጂ በችሎታ ማነስ ምክንያት ከአንድም ክለብ ተባርሬ አላውቅም፡፡ ለሌላው መማሪያ እንዲሆን ስለማስብ ንጽህናንና ታማኝነትን አስቀድማለሁ፡፡ ያው አንዳንዴ እንዲህ ሲሰማህ ትናገረዋለህ፡፡


አንጋፋ የምትባሉት አሰልጣኞች በግልጽ እንደሚታየው እየተገፋችሁ፣ ከስራውና ከብዙሀን መገናኛውም እየራቃችሁ ነው፡፡ ከልምዳችሁ ሊገኝ የሚገባውን ትምህርትም የምታስተላልፉበት መንገድ አልተፈጠረም፡፡ የህይወት ተመክሯችሁን ሊማርበት የሚፈልግ አካል ካልመጣ በቀር እናንተ ገፍታችሁ በተግባራዊ ሂደት የዳበረውን እውቀታችሁን ልታካፍሉ አትሞክሩም…


★ ልክ ነው፡፡ ትልቅ የቴክኒክ ዲፓርትመንት ቢኖር ወይም ቢቋቋም ብዙ የሰው ኃይል መፈለጉ አይቀርም፡፡ ከዚህ ቀደም በኢትዮጵያ እግርኳሰ ፌዴሬሽን ትዕዛዝ አምስት ጊዜ የአሰልጣኝነት ኮርሶችን ሰጥቻለው፡፡ አሁን ግን በዚህ በኩል እገዛህን የሚፈልግ አካል አይገኝም፡፡ ቢያንስ አሰልጣኞች እንዲፈሩ ለማድረግ የሚያሰለጥንና የሚያስተምር ሰው ያስፈልጋል፡፡ በፌዴሬሽኑ ውስጥ ቴክኒካል ዲፓርትመንት ያለም አይመስለኝም፡፡ በፊት የነበሩት እነ መኮንንም ቢሆኑ ከሶስት አይበልጡም፤ አሁን ግን እነሱም ሳይወጡ አይቀርም፡፡ እንዴት የአንዲት አገርን እግር ኳስ የሚመራ አካል ዘላቂ ቴክኒካል ዲፓርትመንት አይኖረውም? እኛ አሰልጣኞች እኮ ለቴክኒካል ክፍሉ የምንመኘው በርካታ የሰው ኃይል ባለቤት የሆነ ተቋም እንዲሆን ነው፡፡ እንደዚህ አይነት ድርጅት ሲኖር በእግርኳሱ ውስጥ ያለፉና የሰሩ ባለሙያዎችን ይፈልጋል፡፡ እውቀቱ ያላቸውንና ማስተማር የሚችሉትን አሰልጣኞች ልምዳቸውን እንዲያጋሩ እድሉን ያመቻቻል፡፡ ለምሳሌ እኔን ይጠራና በአንዱ የአገሪቱ ክፍል ላሉ አሰልጣኞች ኮርስ እንድሰጥ ፕሮግራም ያወጣል፡፡ በዚህ መንገድ አሰልጣኞቹም ልምዳቸውን የማካፈል አጋጣሚና የማስተማር ስራ ያገኛሉ፤ በዘርፉ የሚገኙ ባለሙያዎችም ጥሩ ተሞክሮ ይኖራቸዋል፡፡ ችግሩ የሚሰራውን አካል እንዲሰራ የሚያደርግና የሚመራው ሰው ማጣቱ ነው፡፡ ይሄ ዋነኛው ምክንያት ነው ብዬ አስባለሁ፡፡ የሚሰራ ሞልቷል፤ ብዙ ሊሰራ የሚችል ነገር አለ፡፡ ለአገሪቷ እግርኳስ እድገት የተቋቋመ ትልቅ የቴክኒክ ዲፓርትመንት ቢኖር ሰፊ ስራ መስራት ይቻላል፡፡ አቶ መንግስቱ ወርቁ የብሔራዊ ቡድኑ አሰልጣኝና ቴክኒካል ዳይሬክተር በነበረ ጊዜ በእያንዳንዱ ክልል ውስጥ ያሉ ባለሙያዎችን በሚገኙበት አካባቢ ያሉትን የብሔራዊ ቡድን ተጫዋቾች አሰልጣኝ አደረጋቸው፡፡ የተመረጡት አሰልጣኞች ከዚህ በሚላክላቸው ፕሮግራም መሰረት ተጫዋቾቹን ይሰበስቡና ያሰለጥኗቸዋል፡፡ የብሔራዊ ቡድኑ የጨዋታ ቀን ሲደርስ ተጫዋቾቹ ይሰበሰቡና ብሔራዊ ቡድኑን ይቀላቀላሉ፡፡ ጊዜና የገንዘብ ወጪን በሚቀንስ አሰራር ተጫዋቾቹ በያሉበት ዝግጁ ይሆናሉ፤ እዚህ ሲሰባሰቡ ደግሞ ተጨማሪ የመዋሀድ ልምምድ ያደርጋሉ፡፡ ዋናው ለባለሙያው ስራን መፍጠር የሚችል መሪ ማግኘቱ ነው፡፡


“ከ1970ዎቹ መጀመሪያ ጀምሮ እስከ 1990ዎቹ አጋማሽ ድረስ በስልጠናው ዘርፍ በአንጋፋነት የሰሩትን ያህል ጠንከር ያለ ባህሪን የተላበሰ እና ተፅእኖ የመፍጠር ኃይል ያለው አሰልጣኝ በአሁኑ ወቅት የለም፡፡” የሚል ተደጋጋሚ አስተያየት ይሰጣል፡፡ “የአሁኖቹ አሰልጣኞች በተጫዋቾች ዘንድ የሚሰጣቸው ክብር ከእናንተ አይነቶቹ ቀደምት አሰልጣኞች አንጻር ወረድ ያለ ነው፡፡” ይባላል፡፡ ይህን ልዩነት የፈጠረው ምን ይመስልሀል? በእናንተ ዘመን የነበሩትን አሰልጣኞች ስብዕና መልሶ ለማግኘትስ ምን መደረግ ይኖርበታል?


★ እኔ ‘በአሁኑ ጊዜ ጥሩ የሆኑ አሰልጣኞች የሉም’ ማለት አልችልም፡፡ ሆኖም የአሰልጣኝነት ሙያ ውስጥ ብዙ ተጽዕኖዎች መምጣት ጀምረዋል፡፡ የኮሚቴዎች ጣልቃ ገብነትና ድሮ ያልነበረ የተጫዋቾች ጫና በሙያው ላይ አንዣቧል፡፡ እነዚህ አሉታዊ ሁኔታዎች የዚህን ትውልድ አሰልጣኞች ፈሪ አድርጓቸዋል፡፡ ‘ለምን ሙያችንን አናስከብርም? ለምን እንፈራለን?’ ብለን መጠያየቅና መማማር አለብን፡፡ በእርግጥ ፍርሀቱ ከሆነ ችግር አንጻር የመጣ ሊሆን ይችላል፡፡ አሰልጣኞች ችሎታ እያላቸው ለተጫዋቾችም ይሁን ለክለቦች ተገዢ የሚሆኑበት ሒደት መከባበር የማይኖርበትን መንገድ ይፈጥራል፡፡ እነዚህን ችግሮች ማስቀረት የሚቻልበትን ብልሀት አጥብቀን መፈለግና አሰልጣኞችም በጋራ መመካከር ይኖርብናል፡፡ የህብረትና ትብብር ኃይል ቢኖረን፣ ጠንካራ የቴክኒክ ኮሚቴ ቢቋቋም፣ በክለቦቻችን የአሰልጣኞች ግምገማ ሲደረግ የችግሮችን መነሻ በማወቅ የመፍትሄ ምክክሮች ቢካሄዱ መልካም ነው፡፡ ‘እስኪ አካሄዳችንን እንለውጥ’ በማለት አመራሮች በአሰልጣኙ ስራ ጣልቃ እንዳይገቡና ተጫዋቹን የሚያሰለጥነው አሰልጣኙ እንጂ ሌላ አካል እንዳልሆነ እንዲያውቁ ማድረግ አለብን፡፡ በልምምድ ወቅት “ይህኛው አይነት ስልጠና ይቅርብን፤ አይሆንም፡፡” የሚል ተጫዋች እንዳለ ሰምቻለሁ፡፡ ስልጠናን የሚያስለውጥ ተጫዋች! ምን አይነት ዘመን ነው? ተጫዋቹ የሚሰጠውን የልምምድ አይነት መቀበል ግዴታው ነው፡፡ እንደዚህ አይነት ችግሮችን ለመቅረፍ ከክለቦች ጋር በመተባበር ለተጫዋቾች (ተጫዋቹ ማንም ይሁን!) የስራ መመሪያና ደንቡን መስጠትም ሌላው አማራጭ ነው፡፡ ሌላው ችግራችን ደግሞ አንዳንዴ ትልቁን ተጫዋች እናከብርና አነስ ያለውን ቸል ስንል ስራችንም ለተጫዋቾቹ በሚኖረን ግምት ልክ ይበላሻል፡፡ ስለዚህ ሁሉንም እኩል ማየት እንልመድ፡፡ ጥያቄያቹ ላይ የተመለከቱትን ችግሮች ያጎሉት ምክኖች እነዚህ ናቸው፡፡ “እኔ ገንዘቤን እስካገኘሁ ድረስ የፈለገውን ቢሆን…….” የሚባል ነገር መጣ፡፡ ሙያውም መያተኛውም ረከሰ፡፡ እውነቴን ነው የምለው በዚህ ሀሳብ ከተቀጠለ ነገ እኮ ተጫዋቹ ተነስቶ ሊመታህ ይችላል፡፡ ብዙዎቹ ይህን አድርገውታል፡፡ ለምን?
ተማሪህ- ልጅህም ወንድምህ ነው፡፡ በዚህ አተያይ በየቀኑ ሊረዳህ ከሚችል የክለብ አመራር ጋር በመሆን ምክርና ባስ ሲልም ተግሳጽ በመስጠት ነገሮችን ማሻሻል ይቻላል፡፡ ዋናው ነገር ሙያውን ለማስከበር ትንሽ ጠበቅ ማለት ማስፈለጉን መረዳቱ ላይ ነው፡፡


በኢትዮጵያ የአሰልጣኞች ትውልዶች መሀል የተቋረጠ ነገር ያለ ይመስልሀል? ለምሳሌ ገና በወጣትነትህ ከጀርመን የአሰልጣኝነት ትምህርት ተምረህ በመጣህ ጊዜ እንደ መንግስቱ ወርቁ ያሉ የረጅም ዓመት ልምድና የብዙ እውቀት ባለቤት የሆኑ አሰልጣኞች እናንተን በመቅረጽ ረገድ ወሳኝ ሚና ነበራቸው፡፡ በጎልማሳነት ዘመንህ ደግሞ እንደ ሥዩም አባተ አይነቱን በኢትዮጵያ የዘመናዊ እግርኳስ አሰልጣኝነት ሰፊ ተመክሮና ሀሳብ ያለው ባለሙያ አግኝተህ አብረህ ሰርተሀል፡፡ በሒደት ግን ካንተ ጋር የሙያና የእድሜ አቻ የሆናችሁት ወደ አንጋፋነት ስትሸጋገሩ በወቅቱ ወጣት የነበሩት አሰልጣኞች ከእናንተ የተማሩት ነገር የለም? ወይስ የመቀራረቡና ልምድ የመለዋወጡ ነገር አልነበረም?


★ እንደሚመስለኝ ተቀራርቦ መነጋገርን ጠላንና መከባበሩ ጠፋ፡፡ ለኔ የC፣ B እና A የአሰልጣኝነት Licence ትርጉም የለውም፡፡ ቁምነገሩ ኮርሱን ወስዶ ሰርተፍኬቱን መያዙ አይደለም፡፡ ላይሰንሱ ሳይኖረው በረጅም ጊዜ ልምድና በተግባራዊ እውቀት ከባለ ወረቀቱ የተሻለ አሰልጣኝ ሊኖር መቻሉን ማመን አቃተንና በመከባበር ቁጭ ብለን መወያየት አልቻልንም፡፡ የአሰልጣኞች ማህበር ስብሰባ ጠርቶን ስንገኝ በጣም በሚያሳዝን ሁኔታ “የድሮ አሰልጣኞች” እና “የአሁን ዘመን አሰልጣኞች” የሚል ክፍፍል ተጀመና አፈንግጦ የራስን ቡድን የመያዝ ነገር መጣ፡፡ <የአሰልጣኝነት ፍልስፍና> በሚባለው ጉዳይም መለያየቱ ቀጠለ፡፡ በየትኛውም የአጨዋወት ፍልስፍና ጥሩ ኳስ መጫወት በአካላዊ አቅም የሚለካ ነው፡፡ ስለዚህ ችሎታና አቅም ያለው ተጫዋች ያስፈልጋል፡፡ ከጥሩ ኳስ ጋር የአካል ብቃት ያስፈልጋል፡፡ ይህን ማሳየት ሳትችል ስለ ፍልስፍና ሁልጊዜ ብትለፈልፍ ዋጋ አይኖረውም፡፡ ዋናው ነገር እድሉ ሲሰጥ ሰርቶ ማሳየት ነው፡፡ የሞከሩትም ቢሆን ሁሌ ሲባረሩ እናያለን፡፡ ለምን እዛ ውስጥ እንገባለን? መከባበር እና መነጋገር አለብን፤ የዚህ መልካም መንገድ መጥፋት በመካከላችን የተፈጠረውን ክፍተት አመጣ፡፡ እውነት ለመናገር እኛም “እናውቃለን!” ብለን ሳንኮፈስ “እንማማር” ነው የተባባልነው፡፡ መራራቁ ግን ልምድ መለዋወጡን የተሳካ እንዳይሆን አደረገው፡፡ ሆኖም በማህበሩ ውስጥ የምንገናኛቸው ጥሩ ጥሩ ወጣት አሰልጣኞች አሉ፡፡ አንድ ቀን ‘ሁኔታው ይለወጥና ነገሮች ይስተካከላሉ’ ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ፡፡ በአጨዋወት ፍልስፍና፣ በተጫዋቾች እና አሰልጣኞች ስነምግባርና በሌሎችም እግርኳሳዊ ርዕሶች ላይ የመወያየት ጥብቅ ልማድ ስናዳብር የተሸፋፈኑ ነገሮች ግልጽ እየሆኑ ይሄዳሉ፡፡ ምናልባት ያን ጊዜ መከባባሩ ይጀምራል ብዬ እገምታለሁ፡፡ በእርግጥ ከዚህ ቀደምም በተወሰነ ደረጃ መጠነኛ መሻሻሎች መታየት ጀምረው ነበር፡፡ በአሁኑ ወቅት ምንም ሳናውቅና የተመረጠው ሰው ሳይታወቅም ማንኛውም አሰልጣኝ በፈለገው ጊዜ ተነስቶ ወደ ክለብ ይገባል፡፡ በጣም በሚያሳዝን ሁኔታ አሰልጣኝነት ትልቅ ሙያ የመሆኑ ጉዳይ እየቀረ በመሆኑ እንደከዚህ ቀደሙ ማስታወቂያ እንኳ አይለጠፍም፡፡ እኛ ጉዳዩን ተቃውመን በብዙሀን መገናኛ በገሀድ ተናግረናል፡፡ አሰልጣኝነት እኮ ሙያ ነው፤ ለምንድነው የብቃት ደረጃ በውድድር የማይለካው? በእኛ አገር የእግርኳስ ስታንዳርድ በንጽጽር ብቁ የሆነውን እጩ አወዳድሮና መርጦ እንጂ ዝም ብሎ መቅጠር አግባብ አይመስለኝም፡፡ ተቃውሞውን በመስማት እየወጡ ያሉት ማስታወቂያዎችም ቢሆኑ የ<ይስሙላ> ናቸው፡፡ “ማስታወቂያው ይለጠፍ!” ይባልና ቅጥሩ አግባብ ባልሆነ መንገድ እንደሚፈጸም በጭምጭምታ እንሰማለን፡፡ “ታውቋል እኮ! እገሌ ነው ቡድኑን የሚይዘው!” በሚል ቀድሞ መረጃው ይደርሰናል፡፡ እንዲያም ሆኖ የስራ ልምዳችንን እናቀርባለን፤ የሚገባው ግን ሌላ ነው፡፡ ይህ ነገር መቅረት አለበት፡፡ ለምን የአሰልጣኝነት ሙያ እንደዚህ ይረክሳል? በተለይ እኛ አገር የልምድና የስኬት ማስረጃዎች ውድድር የግድ ያስፈልጋል፡፡ አውሮፓውያኑ ጋር ሁሉም በተቀራራቢ ደረጃ የሚገኙ ስለሆኑና የዚህን አይነት ብልሹ ስርዓት ስለሌለ መርጦ ለመውሰድ ቀላል ይሆንላቸዋል፡፡ በእግርኳሳችን ውስጥ በተለያዩ መንገዶች ስርቆት ስለሚበዛ “ፍትሀዊ የቅጥር መንገዶች ይኖራሉ፡፡” ብሎ ማሰብ ይከብዳል፡፡ እንደ ሌሎች የስራ መስኮች የሙያ ብቃት ውድድር ሊኖር ይገባል፡፡ ለዚህም ጥሩ ዲፓርትመንት ተዋቅሮ ክለቦች አሰልጣኞችና ተጫዋቾችን የሚቀጥሩበትን መስፈርት፣ መመሪያና ደንብ መከታተል ይኖርበታል፡፡ ነገ ፌዴሬሽኑም አሰልጣኞቹን ይፈልጋቸዋል፡፡ ከፍተኛ ቁጥጥር የሚፈልግ የሙያ ዘርፍ ቢሆንም በአስፈላጊው መጠን ቁጥጥርና ክትትል እየተደረገበት አይደለም፡፡ ሌላውና ትልቁ የኢትዮጵያ እግርኳስ ችግር የክለብ አመራሮች አመራረጥ ስርዓት ነው፡፡ ሒደቱ ሙሉ በሙሉ መለወጥ አለበት፡፡ የችግሩ ስር ያለው ክለቦችና የሚመሯቸው አካላት ጋር እንጂ ከላይ ያለውማ ፊት ለፊት የሚታየው ነው፡፡ በአመራሩ ቦታ ላይ በአግባቡ፣ በሀቅና ለእግርኳሱ እድገት ሊሰሩ የሚችሉ ሰዎች መመረጥ አለባቸው፡፡ ያን ጊዜ የሁሉም ስራ የተሻለ ይሆናል፡፡ ፌዴሬሽኑን የሚመሩ ባለስልጣናት በከፍተኛ ፍትጊያ ወደ ቦታው እንደሚመጡት ሁሉ ክለቦችን የሚያስተዳድሩ አካላትም በግልጽነት ላይ በተመሰረተ የምርጫ መስመር ሀላፊነት እንዲሰጣቸው የሚያደርግ ስርዓት ማውጣት አለባቸው፡፡ ከላይ በትንሹ የነካካኋቸው ነገሮች ሁኔታዎችን እያጠሩ የሚያስኬዱ ይመስለኛል፡፡


በነባራዊው ሁኔታችን ላይ ሆነህ የወደፊቱ የእግርኳስ አሰልጣኝነት ስራ ተስፋዎችና ስጋቶች ምን አይነት ይዘት የሚኖራቸው ይመስልሀል?


★ የአሰልጣኞች ማህበር፣ የተጫዋቾች ማህበርና የክለቦች አደረጃጀት በዘመናዊ መንገድ የሚመራ ከሆነ የተጫዋቾች የስራ ተነሳሽነት፣ የባለሙያው ጥረትና የእግርኳሱ እድገት በእርግጠኝነት ይሻሻላል፡፡ ወሳኙ ነገር ያልተጠናከረውን እና የሚልፈሰፈሰውን መሪ አካል ማጠንከር ነው፡፡ ያ ካልሆነ ተጫዋቹ፣ አሰልጣኙና ሌላውም የሚመለከተው ሰው ተልፈስፍሶ ይቀራል፡፡ “አይሆንም፤ እዚህ ክለብ ውስጥ ለማሰልጠን ማሟላት ያለብህ መስፈርቶች አሉ!” የሚልህ የበላይ አካል ሲመጣ በንጽህናና በታማኝነት የመስራት ፍላጎት፣ የተወዳዳሪነት መንፈስና ራስን ዝግጁ የማድረግ ተነሳሽነት ይመጣል፡፡ የአሰልጣኞች ማህበር መሪዎች በሰፊውና ጠለቅ ባለ ሁኔታ ውይይት በማድረግ አባል ያልሆነ ሰው እዚያ አካባቢ እንዳይደርስ ማድረግም ይኖርባቸዋል፡፡ የአባልነት ፍቃድ የሌለው ሰው ለምን ይመጣል? ያልሆኑትስ ለምን አባል አይሆኑም? ማህበሩ የአባላቱን መብት ለማስጠበቅ የሚታገል ህብረት እስከሆነ ድረስ በየጊዜው የማይመጡና ማህበሩን በበጎ ጎኑ የማይመለከቱ ባለሙያዎች ለምን ይካተታሉ? አንዳንዶቹ ህብረቱን የማይወዱት እነሱን የሚነካኩ ብዙ ነገሮች በስብሰባዎች ላይ ስለሚነሱና ይህን ማድመጥ ስለማይፈልጉ ነው፡፡ ተጫዋቾችም ጋር ጥፋት ቢኖርም ለመብታቸው ታጋይ መሆን ይጠበቅባቸዋል፡፡ “ለምን እሰጥሀለሁ? አልከፍልህም፤ በላቤ ያገኘሁት ነው፡፡” ማለት አለባቸው፡፡ የተጫዋቾች ማህበር ጠንካራ የሆነ መዋቅር እንዲኖረው ለማድረግ ከእኛ የሚጠበቀውን እገዛ ለማድረግ እያሰብን ነው፡፡ በዚህ መልኩ እያንዳንዱ ባለሙያ ጠንከር ያለ ህብረት ሲኖረው የጠራና ንጹህ አሰራር እናገኛለን፡፡



ብዙ አሰልጣኞች “የኢትዮጵያን ተጫዋቾች አዲስ ነገር ለማስተማር ብዙ ጊዜ ይወስዳል፡፡ ለዚያ ነው በተጫዋቾቹ ችሎታ ላይ ተመስርተን የምናሰለጥነው፡፡” ይላሉ፡፡ አንተ በምታስበው ደረጃ ተጫዋቾችን ለመግራት ብዙ ጊዜ ይፈልጋል?


★ ጊዜ የሚወስድባቸው መሰረታዊ ነገር ላይ በደንብ ሳይሰሩ ስለመጡ ይመስለኛል፡፡ እኔ የማሰራው ልጅ ነው ሌላው ጋር የሚሄደው፤ ሌላው ጋር የሚሰራው ደግሞ እኔ ጋር ይመጣል፡፡ ዘወትር ውድድር ላይ ስለምንሆን ተጫዋቾችን በፍጥነት ልንለውጥ የምችልበት ጊዜም የለንም፡፡ በጨዋታዎች ወቅት የቡድን ጊዜያዊ እቅድ አለ፤… እያንዳንዱን ልጅ ለብቻው የምታሰራበት ጊዜም የለህም፡፡ ያለችን ያቺው የዝግጅት ጊዜ ናት፤ እሷ ደግሞ ቡድን መገንቢያ እንጂ መሰረታዊ ለውጥ ማምጫ አትሆንም፡፡ ከታች እየተማሩ የመጡ ቢሆን ግን ትንሽ ማስተካከያ ስራና ጊዜ ብቻ ይበቃ ነበር፡፡ እላይ የምታገኛቸው ተጫዋቾች እድሜያቸው ገፍቶና በእድሜ እርከን የሚሰጥ ተገቢውን ስልጠና ሳያገኝ የመጣ በመሆኑ መሰረታዊና መለወጫ ስራ አትሰራም፡፡


ችግሩን ሁሉም አሰልጣኞች በስፋት ያነሱታል፡፡ ይህን ከተረዳችሁበት ጊዜ ጀምሮ እንኳ ለምን መፍትሄ ሊያስገኝ የሚያስችል ስራ አልተሰራም?


★ ማን ያደራጀንና? እኔ ብቻዬን እኮ ምንም ማድረግ አልችልም፡፡ በመጀመሪያ ቴክኒካል ክፍል ውስጥ ያለው አካል ስላንተ አያስብም፡፡ ስለመሰረትህ፣ እየተሰራ ስላለው ስራ፣ ደረጃቸውን ስለጠበቁ የስልጠና አካሄዶች የሚጠይቅልህ አካል መኖር አለበት፡፡ ይህ በማዕከል ደረጃ በግዴታ መደረግ ያለበት ነው፡፡ እድገት ለማምጣት ከተፈለገ አንድ ክለብ ጊዮርጊስ ብቻ አካዳሚ ከፍቶ አገራዊ ለውጥ አያመጣም፡፡ ሌሎችም ክለቦች የታዳጊዎች ማሰልጠኛና በየእድሜ እርከኖች ያላቸውን ቡድን የሚከታተል ሲኖር ጥሩ ነገር ታሳያለህ፡፡ አሁን ከታች ያለምንም ተገቢ ስልጠና የመጣውን በብሔራዊ ቡድን ኳስ ስለማቀበል ታስተምረዋለህ እንዴ! ትልቁ ችግራችን የቴክኒክ ዲፓርትመንት በመሆኑ እንደ አንድ ፓርላማ በቋሚነት መቀመጥ አለበት፡፡ ብሄራዊ ቡድን አንድ
የሚሆነው ለምንድነው? Shadow Teams ሊኖረን ይገባል፡፡ U17,U20,U23 እና ሌሎች የተለያዩ ተተኪ ቡድኖች ሲኖሩ ጠንካራ ፉክክር ይኖራል፡፡ ዋናውን ቡድን ባትፈልገው ሌላውን ታመጣለህ፡፡ ከታች ጀምሮ መዋቅራዊ በሆነ መንገድ ደረጃውን በጠበቀ ስርዓት ሁሉን እየተማረ የመጣ ስታገኝ እኮ ከአሰልጣኙ የሚጠበቀው የማዋሀድና ገዘፍ ያሉ የታክቲክና የመሰካካት ስራዎች ይሆናል፡፡


በቆይታችን በተደጋጋሚ “ከማጥቃት እንቅስቃሴ ጋር ለሚገናኝ የትኛውም አይነት የአጨዋወት ፍልስፍና ተጫዋቾች በአካል ብቃቱ ረገድ እጅግ የበቁ መሆን አለባቸው፡፡” የሚል አስተያየት ሰጥተኸናል፡፡ በአገራችን በ<ፊትነስ> ጉዳይ በአንዳንድ የእግርኳስ ሚዲያና የስፖርት ቤተሰብ ዘንድ የተዛባ አመለካከት ያለ ይመስለናል፡፡ ብዙውን ጊዜ “ዝም ብለው ተራራ
ያስሮጧቸዋል፤ የሚሰጣቸው የአካል ብቃት ስልጠናም ከተጫዋቾቹ ተፈጥሮአዊ ተክለ ሰውነት ጋር የማይመጣጠን ነው!” የሚሉ ሀሳቦች ይነሳሉ፡፡ዘወትር በሜዳ ላይ የሚታየው ደግሞ እጅጉን የተዳከመ የአካል ብቃት ደረጃ ነው፡፡ በዚህ የአመለካከት ልዩነት ምን የምትለው ነገር አለ?


★ በዚህ ዘመን ከውጪው እግርኳስ የምንወስደው ትምህርት ምስክርነት ሊሆነን ይችላል፡፡ የጥያቄያችሁን ትክክለኛ ምላሽም ይሰጡናል፡፡ የባርሴሎናን ጨዋታ እንወዳለን አይደል? ተጫዋቾቹ Endured ናቸው፡፡ ሁሉም ሰው ይህን መሰል አጨዋወት ይፈልጋል፡፡ እኛ አገር ተጫዋቾች ላይ Agility እና Flexibility የሚባል ነገር የለም፡፡ እኔ አሰልጣኙ እንኳን -/ እጄን ወደ ታች በማውረድ እግሬን እነካለሁ፡፡/የተጫዋቾቻችን ቀልጣፋነት ወይም ሰውነታቸውን እንደፈለጉ የማዘዝ ነገር ጥያቄ የሚነሳበት ነው፡፡ ሲወድቁ እንኳ እንደ ዛፍ ነው፤ በፍጥነት አይነሱም፡፡ እነሱ (የውጪዎቹ) Standard የሆነውን ስልጠና አግኝተዋል፡፡ ጥሩ እግርኳስና Endurance የማይነጣጠሉ ናቸው፡፡ ውበት ስላለው እግርኳስ እያወራን የአካል ብቃት ጉዳይን ወደ ጎን ማለት አይችልም፡፡ ይህንን ተገደንም ቢሆን መቀበል አለብን፡፡ ብልጫ ኖሮህ ለምታካሂደው ጨዋታ ጥሩ የአካል ብቃት ደረጃ ሊኖርህ ይገባል፡፡ 15 እና 30 ደቂቃ የሚያቆይ ትንፋሽ ይዞ በኳስ ቁጥጥር የበላይነት ለማሳየትም አዳጋች ነው፡፡


ወደ ግለሰብ ተፅዕኖዎች እንምጣና በአገራችን እግርኳስ የክለብ አመራሮች በአሰልጣኞች ስራ ጣልቃ የሚገቡት በየትኞቹ ዘርፎች ነው?


★የመጀመሪያው በተጫዋቾች ምርጫ ነው፡፡ በማያገባቸው ዝም ብለው ይገባሉ፡፡ በብሄራዊ ቡድንም ይሁን በክለቦች በተጫዋቾች ምርጫ ጉዳይ የሚመለከታቸው የቴክኒክ ሰዎች ናቸው፡፡ በክለቦች ውስጥ እየታየ ያለው አካሄድ ግን ከንጽህና ወይም ታማኝነት የራቀ ስለሆነ በሙያችን ውስጥ ንጽህና እየጠፋ ነው፡፡ ይህን ስል ምክንያት ኖሮኝ ነው፡፡ እኔ ብዙ ተጫዋቾችን አፍርቻለሁ፡፡ እነዚያ ተጫዋቾች በአውሮፓ በአሜሪካና በተለያዩ የአለም ክፍሎች ይገኛሉ፡፡ በዩናይትድ ስቴትስ የሚገኙ የእግርኳስ ቤተሰቦች ከሳንፍራንሲስኮ፣ ሎስ አንጀለስና ዋሽንግተን ዲሲ በክብር እንግድነት ለሶስት ጊዜያት ያህል ጥሪ አድርገውልኝ የአሜሪካ ኤምባሲ ቪዛ ከለከለኝ፡፡ በ2005 ዓ.ም አካባቢ ከአውሮፓ በሲውዘርላንድ እንዲሁ ጥሪ ደረሰኝና ተሳክቶልኝ ሄድኩ፡፡ ይህን ሁሉ የሚያደርጉልኝ የቀድሞ ተጫዋቾች ያኔ በስልጠናው ጊዜ ለራሳቸው እድገት በንጽህና በማገልገሌ ነው፡፡ አንድም ተጫዋች ከጥቅም ጋር በተገናኘ ጥያቄ ቢያነሳብኝ በቀጥታ እጄን እሰጣለሁ፡፡ ማንም በዚህ ጉዳይ አንስቶኝ አያውቅም፤ ወደፊትም ቢሆን ምንም አይለኝም፡፡ በዘርፉ ያለን ባለሙያዎች ጥቅም ከለመዱ የክለብ ሰዎች ጋር በምናደረጋቸው ግንኙነቶች ንጽህና እያጣን ነው፡፡አንዳንድ የክለብ ሰዎች፣ የድለላ ስራ የሚሰሩና ተጫዋቾች እየተገናኙ በአሰልጣኙ ስራ ጣልቃ ይገቡብሀል፡፡ ብቁ ያልሆነው ተጫዋች ገንዘብ ሊያስገኝ በሚያስችል ሁኔታ ውስጥ ወደ ክለቡ ይገባል፡፡ ትልቁ እምነትን እያጓደለና ንጽህናን እያጠፋ ያለ ነገር ይህ ነው፡፡ ክለቦችን እንዲያስተዳድሩ ሐላፊነት የተሰጣቸው አመራሮች ጋርም ታማኝነት ጠፋ፡፡ በአስተዳደር ዘርፍ የሚቀመጡት ሰዎች በሚሰጣቸው ቦታ ላይ ተገቢ የሆነ እውቀት ሳይኖራቸው ስለሚመጡ በቀላሉ ለዚህ የተበላሸ አሰራር ተጋላጭ ይሆናሉ፡፡ ተጫውተው ያለፉና ስራውን በጥሩ ሁኔታ መምራት የሚችሉ አካላትም ጥቅም ከለመዱ ይህን ከማድረግ ወደ ኋላ አይሉም፡፡ እንደምንሰማውም በዚህ ጉዳይ ስማቸው የሚነሱ ሰዎችን እያስተዋልን ብንገኝም ዋናው መፍትሄ ያለው ተጫዋቾች ጋር ነው፡፡ ጠንካራ በመሆን ‘የላቤ ገንዘብ ነው፤ በችሎታዬ መግባት አለብኝ፡፡’ ብሎ መከራከርና በአቋም መጽናት አለበት፡፡ በዚህ አጋጣሚ ልናገር የምፈልገው የክለብ ተመክሮዬን ነው፡፡ በክለቦች የስልጠና ስራ ስጀምር በመጀመሪያው ስብሰባዬ የቡድን መሪዬን፣ ከክለቡ አመራሮች አንድ ሰውና የአሰልጣኞች ቡድን አባላትን እሰበስብና ተጫዋቾችን ጠርተን ” እዚህ ውስጥ ካለነው እናንተ ወደዚህ ቡድን ስትቀላቀሉ ‘ገንዘብ አምጡ!’ ያላችሁ ሰው ካለ ዛሬውኑ አውጡትና እንገላገለው” በማለት እንጠይቃቸዋለን፡፡ ‘በሌላ ጊዜ ይህን ጉዳይ በምክንያትነት እንድታነሱ አልፈልግም፡፡’ እላቸውና ሁሉንም ነገር ግልጥልጥ አድርገንና ተማምነን ስራ እንጀምራለን፡፡


በአጨዋወት ስልት፣ በተጫዋቾች ቋሚ ተሰላፊነትና ሌሎች የሜዳ ላይ ጉዳዮችስ?


★ይህና ሌሎችም የአሰልጣኙ ብቻ የሆኑ ስራዎች ላይማ በደንብ ነው ጣልቃ የሚገባው፡፡ ቅያሪዎች ላይ ሳይቀር በማያገባቸው የሚገቡ አሉ፡፡ እዚህ ጋር አንድ ነገር ልንገራችሁ- አቶ ተስፋሚካኤልን ታውቁታላችሁ፤ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር እግርኳስ ክለብ ስራ አሰኪያጅ እያለ እኔን በአሰልጣኝነት መርጦ ቀጥሮኛል፡፡ በአንድ ወቅት በጨዋታ ቡድኔ በኮልፌ ቀራኒዮ 1-ለ-0 እየተመራ በእረፍት ሰዓት ወደ መልበሻ ክፍል ስገባ ገርበብ ባለው የክፍሉ በር ወደ እኛ ሲመጣ አየሁት፡፡ ምክትሌ የነበረውን ንጉሴ ገብሬን በሩን እንዲዘጋው ነገርኩት፡፡ ተስፋሚካኤልም በሩ መዘጋቱን ሲያውቅ ተመልሶ ሄደ፡፡ የዕለቱ ዕለት አኮረፈኝ፤ በሌላ ቀን ስንገናኝ ግን ፊትለፊት ነገርኩት፡፡ ‘አንተ ምንም ነገር አያገባህም፤ አሰልጣኝ እኔ ነኝ! ይሄን እንድታምን እፈልጋለሁ፡፡’ አልኩት፡፡ በዚህ አቋምህ የምትባረር ከሆነ እንኳ ተባረር! እኛም አሰልጣኞች ይሄ ድፍረት የለንም፡፡ ያቺን መተዳደሪያችንን ለማግኘት ስንል የምናልፈው ብዙ ነገር አለ፡፡ መደረግ ግን የለበትም፡፡ ሙያችንን ለማስከበር ትንሽ ደፈር ማለት አለብን፡፡


ከዚህ ቀደም በነበረው አሰራር ውድድሮች በክልሎች የተያዙ ነበሩ፡፡ በእያንዳንዱ ክልል ያሉት ስፖርት መምሪያዎች ጥሩ ክትትል ያደርጉበት ስለነበርም የተሻሉ መሆን ችለዋል፡፡ አሁን ሁሉም ነገር በፌዴሬሽኑ ስር በመሆኑ ያሉት ችግሮች ላይ ግምገማ ማድረግን እንዲዘነጋ አድርጓል ብለህ ታስባለህ?


★ አዎን! አሁን ትኩረትና ክትትል የሚደረገው የየቀን ስራ ላይ ብቻ ሆነ፡፡ ለምሳሌ የአዲስ አበባ ክልል ምክር ቤት የራሱ ቡድኖች አሉት፤ ሆኖም አንድም ቀን ሰብስቦ ግምገማ ሲያደርግ አልያም ጠርቶ ሲያወያይ አይቼ ወይም ሰምቼ አላውቅም፡፡በየክልሎቹም ቢሆን ያለ አይመስለኝም፡፡ የየክልሎቹ ስፖርት መምሪያ ቴክኒካል ዲፓርትመንት ስራው ይሄ ነበር፤ ግን የወረዳ ውድድሮችን ከማዘጋጀት የዘለለ ነገር ሲከውን አይታይም፡፡ ክለቦችን ሰብስቦ ባሉት አሉታዊም ሆነ አዎንታዊ ለውጦች ዙሪያ ማወያየት እና ጥያቄዎችን እንዲመልሱ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ ለቀጣይ ውድድሮችም የተሻለ የውድድር ዝግጅት፣ ጥሩ ተጫዋችና ብቁ አሰልጣኝ ለማግኘትም ይረዳል፡፡ በዚህ ሰበብ አሰልጣኞችም ዘላቂ ውጤትን በተመለከተ ተጠያቂ ይሆናሉ፡፡ አሁን ግን አሰልጣኙ የፈለገውን ቢሰራ ማንም “ለምን?” ብሎ አይጠይቀውም፡፡ ምክር የሚሰጠውም አካል ስለሌለ ሁሉም የየራሱን በተናጠል ይሰራል፡፡ በእግርኳስ ደግሞ እድገት በተናጠል አይመጣም፡፡


በኢትዮጵያ እግርኳስ የክለብ ደጋፊዎች ተጫዋቾችን እስከመግዛት የሚደርስ የስልጣን አቅም ሲኖራቸው ይስተዋላል፡፡ ይህኛው መንገድ ከአለም አቀፋዊ የተጫዋቾች ዝውውር ስርዓት ወጣ ያለ አካሄድን የሚያሳይ ይመስላል፡፡ ሁኔታው እግርኳሱ ላይ በአሉታዊነት የሚያሳድረው ተጽዕኖ ምንድን ነው?


★ Exactly! አካሄዱ እግርኳሱን በደንብ ይጎዳዋል፡፡ ደጋፊው ማን ነው? ደጋፊዎችም ልክ እንደ ቴክኒክ ባለሙያዎችና አስተዳደር አካላት የራሳቸው የሆነ ትልቅ የስራ ድርሻ አላቸው፡፡ አሁን እየተሰራ ባለው ሁኔታ ግን ደጋፊው፣ አመራሩና ቦርዱ ቴክኒክ ጉዳይ ውስጥ ይገባል፡፡ በዚህ አይነት ሁኔታ በተለያዩ ሰዎች ፍላጎት ላይ በሚመሰረት ሒደት <የተለያዩ ቡድኖች> እንጂ <ቡድን> አትሰራም፡፡ የቴክኒክ ጉዳይ በቃ ለቴክኒክ ባለሙያዎች የሚተው ስራ ነው፡፡ በክለቡ የቴክኒክ ዳይሬክተር ካለ ከአሰልጣኞች ቡድን ጋር በመሆን ሐላፊነት ወስዶ የተጫዋቾች ዝውውርን ያስፈጽማል፡፡ በሁሉም ክለቦች ይህ ችግር ይስተዋላል፡፡ በተለይ ዝውውር ላይ ሁሉን የሚመለከተው ቦርዱ ሆኗል፡፡ ከውጭ ተጫዋቾችን ያስመጣል፤ ተጫዋቾችን ይመርጣል፤ ተጫዋቾችን ያሰናብታል፤…..እውነት ለመናገር ወደ ባህርማዶ ለንግድ አምርቶ ተጫዋቾችን ገዝቶ የሚመጣ ደጋፊ አለ፡፡ ሙያን ለባለሙያ መተው ያስፈልጋል፡፡ በዚህ ነው የማምነው።


በዘንድሮው የውድድር ዘመን ከፕሪምየር ሊጉ 16 ክለቦች ከግማሽ በላዩ አሰልጣኞቻቸውን አሰናብተዋል፡፡ ሁለት ጊዜ የቀየሩ ቡድኖችም አሉ፡፡ በአሰልጣኞች የክለብ ቆይታ ዙሪያ እየታየ ያለውን አለመረጋጋት እንዴት ታየዋለህ?


★ አንዱ ምክንያት ከላይ የጠቀስኩት ነው፡፡ የተሰናበቱት አሰልጣኞች አንዳንዶቹ አዲስና በማያውቁት ቡድን ስራ የጀመሩ ናቸው፡፡ አልፎአልፎ እንደ <ፋሽን> በሚታዩት ነገሮች አዝናለሁ፡፡ አሰልጣኝ መቀየር እንደ ፋሽን ሆነ፡፡ አውሮፓ ያሉት የራሳቸውን ነገር አመቻችተው ነው አሰልጣኝ የሚተኩት፡፡ ምንም ምክንያታዊ ማስረጃም ሆነ መረጃ ሳይኖርና ባልተስተካከለ ሁኔታ የክለብ አመራሮች ይነሱና አሰልጣኝ ይቀይራሉ፡፡ ‘እነሱ እነማን ናቸው?’ ካልን ደግሞ ምንም አይነት እግርኳሳዊ የሌላቸው ግለሰቦች ሆነው እናገኛቸዋለን፡፡ “እገሌ አሰልጣኝ ስለቀየረ እስቲ እኛም ቀይረን እንየው፡፡” በማለት የአሰልጣኝ ለውጥ ማድረግ ምን ማለት ነው? ይህን መሰል አሰራር የሚመጣው ደግሞ በክለቦች አደረጃጀት ምክንያት ነው፡፡ አንድ አሰልጣኝ በቡድኑ ውስጥ ሙሉ የመስሪያ ጊዜ ተሰጥቶት መታየት አለበት፡፡ ዛሬም ተነስተህ አሰልጣኝ ትቀይራለህ፤ ነገም እንዲሁ ታደርጋለህ- ግን ለውጥ የለም፡፡ የምታተርፈው የፋይናንስ፣ የጊዜና የሰው ኃይል ብክነትን ብቻ ነው፡፡ በዚህም የክለቦችን የአቋም መወዠቅ ትፈጥራለህ፡፡


በመጨረሻም ከእኛ የቀረና አንተ ማለት የምትፈልገው ነገር ካለ…?


★ እውቅና መስጠት ቀላል ነገር አይደለም፡፡ በአንድ ሳምንት ውስጥ ለሁለተኛ ጊዜ ይህ ነገር አጋጠመኝ፡፡ የእናንተ እንዲያውም ቀደም ብሎ የተያዘ ቀጠሮ ነበር፡፡ ሁኔታዎች ባለመመቻቸታቸው ነው በታሰበው ጊዜ ቃለ መጠይቁ ያልተደረገው፡፡ በቀደምም (ቃለ ምልልሱ ከተደረገበት ጥቂት ቀናቶች ቀደም ብሎ) እንዲሁ ለቀድሞዎቹ አሰልጣኞች እውቅናን የሰጠን አካል ነበር፡፡ በእለቱ የተናገርኩት አስተያየትም “እውቅና ክብር ነው፤ አክብሮህ የሚመጣ ደግሞ የሚከበር መሆን አለበት፡፡ ስለእውነት ለመናገር በጣም ነው የማከብራችሁ፤ በጣም አመሰግናለሁ፡፡ አንድ ነገር እንዳገኘሁ እቆጥረዋለሁ፤ ውስጤ ያለውን እንድናገርና እንዳወጣ እንዲሁም ለሌላው ትምህርት መሆን እንዲችል ስላደረጋችሁ በጣም አመሰግናለሁ፡፡ ይህ ለኔ ከገንዘብ የበለጠ ነው፡፡ ከዚህ ቀደም ተናግሬያለሁ፤ ያሰለጠንኳቸው ክለቦችና ብሄራዊ ቡድን አንድም ቀን እውቅና ሰጥቶኝ አያውቅም፡፡ ትናንትናና ከትናንት ወዲያ ምንም የማታውቁኝ እናንተ ግን መጥታችሁ ያኔ ስለሰራሁት አንስታችሁ እና ስለ አጠቃላይ እግርኳስ ጉዳዮች እኔን ስትጠይቁኝ ደስ ነው ያለኝ፤ ቤተሰቦቼም ገርሟቸዋል፡፡ በዮድ አቢሲኒያ ጥሪ ተደርጎልን የተሰጠንንን የእውቅና ሰርተህፍኬት ” ግድግዳ ላይ ለጥፈው! በእግርኳሱ ሙያ በቆየህባቸው ሰላሳና ከዚያ የሚበልጡ አመታት ያገኘኸው ይሄን ነውና፡፡” ብለውኛል፡፡ ከእናንተ ጋር የቃለ መጠይቅ ፕሮግራም እንዳለኝ ስነግራቸውም በጣም ነው የተገረሙት፡፡