የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን የፕሬዝዳንታዊ እና ስራ አስፈፃሚዎች ምርጫ ከረጅም ጊዜያት መጓተት በኋላ ነገ በሰመራ ይከናወናል። በዚህ ምርጫ ላይ ለፕሬዝዳንተነት ከቀረቡ እጪ ተወዳዳሪዎች አንዱ አተ ተካ አስፋው ናቸው።
ከ2000 እስከ 2006 በአህመድ ያሲን እና ሳህሉ ገብረወልድ አስተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ፕሬዝዳንት ሆነው ፌዴሬሽኑን ያገለገሉት አቶ ተካ አስፋው በፕሬዝዳንትነት ለመወዳደር የወሰኑበትን ምክንያት ተናግረዋል። ” በመጀመርያ ወደ ፌዴሬሽኑ ለመመለስ የወሰንኩት አብዛኛው ነገር ባዘጋጀሁት አጭር መፅኄት ላይ ገልጫለሁ፤ እነሱን ለመተግበር ነው። ሁለተኛ ብዙ ጊዜ እንደተናገርኩት ጀምሬ ያልጨረስኳቸው የሚቆጩኝ ሁልጊዜ የሚያንገበግቡኝ “ምነው በጨረስኳቸው…” ብዬ የምቆጭባቸው ጉዳዮችን ለመጨረስ እና አዳዲስ እቅዶችን ለመጨመር ቢያንስ አደረጃጀቱን ለማስተካከል ፣ የማይነጥፍ ብሔራዊ ቡድን ወይም ዘላቂ ውጤት የሚያስመዘግብ ስራ ለመስራት ፤ በሌላ መልኩ በሴቶቹም በወንዶቹም ብሔራዊ ቡድን ለረጅም ጊዜ የጠማንን ውጤት ለመመለስ ቢያንስ እንኳ ለመለወጥ ካልሆነ ሽንፈቶችን መቀነስ አስቤ ነው የተነሳሁት። እቅዶቼ በርካታ ናቸው። ሁሉንም ዘርዝሬ ለመናገር ሰዓቱ አይበቃም። “ብለዋል።
አቶ ተካ አስፋው በምርጫው እንደሚወዳደሩ ካሳወቁበት እለት ጀምሮ ከክለብ ድጋፍ ጋር በተያያዘ የውይይት ርዕስ ሆነው ቆይተዋል። ሆኖም ሁሉም ከክለብ ድጋፍ ነፃ እንዳልሆነና ይህ ጉዳይም ጥርጣሬ ውስጥ ሊከት የሚገባ እንዳልሆነ ይገልፃሉ። ” ለምን ይጠራጠራሉ ክለብ እደግፋለው። ማንም ሰው መነሻው ክለብ ነው። ” እኔ የምደግፈው ክለብ የለም” ቢል ውሸታም ነው። ሁላችንም እዚህ ያለነው የተሰበሰበው ሁሉ የአንዱ ክለብ ደጋፊ ነው። ምንጩም እሱ ስለሆነ ፤ እንኳን እኔ አይደለውም የሀገር መሪዎች የክለብ ደጋፊዎች ናቸው። ትልቁ መለካት ያለበት ስራው ላይ ነው። ሰዉ የትኛውም ክለብ ደጋፊ ቢሆን በኢትዮዽያ እግርኳስ እና በፍህታዊነት ላይ የማይደራደር መሆን አለበት። ይህን ደግሞ ባለፉት አመታት በደንብ አሳይቻለው ፤ ታስታውሱ እንደሆነ ዋንጫ ከጊዮርጊስ ነጥቄ ለቡና አሰጥቻለው። የዛሬ አራት ዓመት ራሴን ከእጩነት ሳገል የኢትዮዽያ ቡና መሪ መቶ አለቃ ፍቃደ ማሞ ስለኔ ፍህታዊነት በግልፅ በጠቅላላ ጉባኤ ላይ የመሰከሩበት ነው። ስለዚህ ይህ ነገር እኔን አይገልፀኝም። በምንም ተዓምር ቢሆን በየትኛውም ክልል ክለብ ለእኔ እኩል ነው። ስለዚህ አማራ ስለሆንኩኝ ደቡብን፣ ትግራይን፣ ኦሮሚያን ለመበደል አለይደለም ። የጊዮርጊስ ደጋፊ ስለሆነ ቡናን ወይም ደደቢትን ለመበደል አይደለም። እኔ በእኩልነት ለማስተዳደር ነው የመጣሁት። ይሄን ደግሞ በተግባር ከዚህ ቀደም አሳይቻለው። አሁንም እደግመዋለው የእኔ አቋም ይሄ ነው።
አቶ ተካ በመጨረሻም ስለ ነገው ምርጫ እና ውስጥ ለውስጥ ስለሚወሩ ጉዳዮች ይህን ብለዋል።
” አለመታደል ነው ለምን እንዲህ እንደምንሆን አይገባኝም። የእውነት ለመናገር የሀገራችን ጠቅላይ ሚኒስተር ለመምረጥ አንድ ወር አልፈጀብንም የኢትዮዽያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ለመምረጥ ምን ያህል ጊዜ እንደፈጀብን አስቡት። በራሳችን ህግ መዳኘት አቅቶን ፈረንጅ በፃፈልን ህግ እየተመራን ነው እዚህ የደረስነው። ይህ እንደዜጋ በጣም ያሳፍረኛል። የምሰማቸው የሚወሩ ነገሮች አሉ። ትላንት በግልፅ አዲስ አበባ ላይ የተወሰኑ ሰዎች ተሰብስበው እከሌን ምረጡ አትምረጡ እያሉ ነበር ፤ ይሄ ያሳርፍራል። አንድ ሰው ከውድድር ከወጣ በኋላ ሌላውን ለማስመረጥ የሚያደርገው ትግል እኔ እንደዜጋ ኢትዮዽያን እና እግርኳስን የሚወድ ነው ብዬ አላስብም። ማንም ይምራ ሰው መለካት ያለበት በእልህ በቂመኝነት ሳይሆን ለሀገር የሚጠቅም ከሆነ ሰይጣንም ቢሆን ቢመረጥ ክፋት የለውም ይምራ። እግርኳስ በጥሩ መንገድ መምራት ከቻለ እኔ በዚህ ነው የማምነው ። ከሚወራው ነገር አንፃር ስጋት አለብኝ ጤናማ ይሆናል የሚል እምነት የለኝም። ጠቅላላ ጉባዔው የበሰለ የተረጋጋ እንደመሆኑ መጠን ረጋ ብሎ ሀገርን የሚጠቅም ሰው አስር ጊዜ አስቦ አንዴ መወሰን አለበት።”