‹‹የብሄራዊ ሊግ ሩጫችንን ጨርሰናል›› በላይ አባይነህ

የድሬዳዋ ከነማው አጥቂ በግቦቹ ብርቱካናማዎቹን ወደ ፕሪሚየር ሊጉ መልሷቸዋል፡፡ ውድድሩ ሲጀመር በተጠባባቂ ወንበር ላይ ተቀምጦ የጀመረው አጥቂ ከአርሲ ነገሌ ጋር በተደረገው የመክፈቻ ጨዋታ በመጨረሻዎቹ 10 ደቂዎች ባሳየው ብቃት አሰልጣኝ መሰረትን አሳምኖ በቋሚነት ግብ ማምረቱን ቀጥሏል፡፡ ከዛሬው ጨዋታ ፍፃሜ በኋላም በደስታ ስሜት ውስጥ ሆኖ አስተያየቱን ሰጥቷል፡፡

‹‹ ውድድሩ ሲጀመር ቋሚ ተሰላፊ አልነበርኩም፡፡ ጠንክሬ ሰርቼ ቦታዬን አግኝቻለሁ፡፡ ሁልጊዜም ክለቤ ከእኔ የሚፈልገውን ለማበርከት እተጋለሁ፡፡ ይህም ለስኬቴ አስተዋፅኦ አበርክቷል፡፡ ›› ብሏል፡፡ በላይ በቀጣይ አመት ስለሚገጥማቸው ፈተናም አስተያየቱን ሰጥቷል፡፡

‹‹ የብሄራዊ ሊግ ሩጫችንን ጨርሰናል፡፡ አሁን ደግሞ በፕሪሚየር ሊጉ ጠንካራ ተፎካካሪ ለመሆን እንሰራለን፡፡ በፕሪሚየር ሊጉም ክለቤ ከእኔ የሚፈልገውን ለመስጠት ተዘጋጅቻለሁ፡፡ ›› ሲል አጠቃሏል፡፡

በላይ አባይነህ በ6 ግቦች የከፍተኛ ግብ አግቢነቱን ሰንጠረዥ እየመራ ሲሆን የብሄራዊ ሊግ ኮከብ ግብ አግቢ የሚመረጠው በማጠቃለያው ውድድር ላይ ያስቆጠረው ግብ ተቆጥሮ በመሆኑ በከፍተኛ ግብ አግቢነት የማጠናቀቅ እድሉ ሰፊ ነው፡፡

ያጋሩ