“የምንወዳደር ከሆነ ጭብጥ ላይ መሆን አለበት” አቶ ኢሳያስ ጅራ

በኢትዮጵያ እግርኳስ ፌደሬሽን ምርጫ ከሚወዳደሩ የፕሬዝደንታዊ  እጩዎች መካከል አቶ ኢሳያስ ጅራ ይገኛሉ፡፡ የፕሪምየር ሊግ ተሳታፊውን ጅማ አባ ጅፋርን በስራ አስኪያጅነት ያስተዳድራሉ እያስተዳደሩ የሚገኙት አቶ ኢሳያስ ከሶከር ኢትዮጵያ ጋር በምርጫው ጉዳይ ቆይታ አድርገዋል፡፡

በኢትዮጵያ እግርኳስ ላይ ከሁለት አስርት አመታት በላይ ቆይታ አድርገሃል፡፡ በክለብ አስተዳዳሪነትም ትታወቃለህ፡፡ አሁን ላይ ለፕሬዝደንተነት ለመወዳደር የወሰንክበት ምክንያት ብታስረዳን?

እንዳነሳኸው ላለፉት 22 ዓመታት እና ከዚያ በላይ ስፖርት ላይ ነው ስሰራ የነበረው ክለብ ብቻ ላይ አይደለም፡፡ በአመራር፣ በወረዳ ቢሮ ሃላፊ፣ በጅማ ከተማ ቢሮ ሃላፊነት በዛው የስፖርት ሂደት ሃላፊ እና ሰበታም በስፖርት ሃለፊ ከዛም ከእነኝህ ጎን ለጎን የክለብ ፕሬዝደንት በብሄራዊ ሊግ ውስጥ በሚወዳደር በፕሪምየር ሊግ ውስጥ በሚወዳደር ክብ ውስጥ ፕሬዝደንትም ስራ አስኪያጅም ሆኞ ነው ስሰራ የነበረው፡፡ እነኚህ ሁሉ የረጀም ግዜ ልምዶች ነው ያሉኝ፡፡ ከመነሻው የእኔ የውስጥ ፍላጎቴ አልነበረም የክልል ፍላጎት ነው የነበረው፤ የክልል ክለቦች ፍላጎት ነው የነበረው፡፡ የኦሮሚያ ክልል ክለቦች ፍላጎት ነው የነበረው እና ጥያቄው ሲቀርብልኝ ግን ከራሴ ጋር ከተነጋገርኩ በኃላ የዚህ ውጥንቅጥ የመፍትሔ አካል መሆን እችላለው የሚል ሃሳብ ውስጤ ስለተፈጠረ ያንን ደግሞ አደርጋለው ብዬ ስለማምን ነው፡፡ አሁን አሁን ሲታይ እግርኳሱ በአንድ ምሽት የሚለወጥ አይደለም ነገርግን ቢያንስ ምቹ ሁኔታ ፈጥሮ ወደ ተሻለ ቦታ መውሰድ ይቻላል የሚል እምነት ነው ያለኝ፡፡ እኔ የጠቅላላ ጉባኤው አባል ነኝ ላለፉት 12 ዓመታት፡፡ ወደ 3 ምርጫ ሲካሄድ እያየሁ ነው፡፡ ነገር ግን ሰዉ ፓሽን የሚኖረው ምርጫ ሲደርስ ብቻ ነው፡፡ ሲጀመር በኢትዮጵያ እግርኳስ ፌደሬሽን ፕሬዝደንታዊ ምርጫ ምንአልባትም እኔ የመጀመሪያው ሰው ልሆን እችላለው ከአቶ ይድነቃቸው በኃላ ከሙያ ውስጥ የመጣ ሰው ሲወዳደር፡፡ በተለያዩ ሴክተር መስሪያ ቤቶች ላይ የነበሩ የተለያየ ልምድ ያላቸው ነገር ግን ስፖርቱን ከገባን በኃላ ልምድ አገኘን በሚሉ ሰዎች ነው የሚመራ የነበረው እና እሱ ነገር ያሳምማል፡፡ እኛ እዚህ ውስጥ ሆነን ስራውን ማስተካከል እየተቻለ በ4 ዓመቱ ሌላ ሰው መጥቶ እኔ ፓሽን ስላለኝ መወዳደር እፈልጋለው የሚለው፡፡ ለእዛ ነው እውቅና ስንሰጥ የከረምነው፡፡ ከቀረብኩ በኃላ ደረኩት ነገር ብዙ ሳይንቲፊክ የሆነ ነገሮች ሙያውን አመላካች ነገሮችን ሰርቼ ነው ወደዚህ ውድድር የመጣሁት፡፡

እግርኳሱ በባለፈው ዓመታት በብዙ ችግሮች የተተበተበት እና የተዘፈቀበት ግዜ ላይ ተገኝተናል….

እግርኳሱ ከመውረዱ በላይ የጎጠኝነት ነገር አርፎበታል፡፡ የዘርኝነት እየሆነ መጥቷል፡፡ በእርግጠኝነት ስሜቴን የሚነካው እና የሚያመኝ ይሄ ክፍል ነው፡፡ እግርኳሱ ከዚህ ችግር መውጣት አለበት የሚል ፅኑ አቋም ነው ያለኝ፡፡ የመጀመሪያ እና የአጭር ግዜ እቅድ አድርጌ የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት ላይ እሰራለው፡፡ እያንዳንሱ ሰው ይሄን እሰራለው ይሄን እሰራለው ሲል ነው የቆየው እኔ ግን ይሄን ህመም ስመለከት ነው የቆየሁት፡፡ የመጀመሪያ ስራዬ አንድነትን መፍጠር ነው፡፡ ሰው እየሰጋ ወደ እግርኳስ ሜዳ መሄድ የለበትም፡፡ ስብሰባ ስላደረግ በአንድ ምሽት ለውጥ ሊመጣ ይችላል ማለት አይደለም፡፡ ለእግርኳስ ለውጥ ግዴታ ይሄን እንቅፋት ማስወገድ አለብን፡፡ በኢትዮጵያ ውስጥ 40% ከ15-29 ዓመት ውስጥ ያሉ ወጣቶች ናቸው የሚኖሩት፡፡ ይሄን ወጣት የሚጠቅም ስራ ለመስራት እና ይሄንን ውሳኔ ለመወሰን 9 ወር እኮ ነው የቆየነው፡፡ 40% የኢትዮጵያ ህዝብ ላይ ነው እየቀለድን ያለነው፡፡ ይሄ የሚመነጨው ከግለኝነት ነው፡፡ እኔ በእርግጠኝነት ይሄ ከተፈታ ትኩረቱን ወደ እግርኳስ ያደርጋል፡፡

ድጋፍ የሰጠህ ክልል ለእግርኳሱ ልማት ይጠቅማል በሚል ስትራቴጂ መቅረፁ ይታወቃል፡፡ በምርጫው አሸናፊ መሆን እና አለመሆናቹሁ ገና ሳይታወቅ በትረ ስልጣኑን ሰትጨብጥ ይህንን ስትራቴጂ መቅረፁ ልክ ነው ትላለህ? ስትራቴጂው የሚሳድራቸው የማህበራዊ፣ ፓለቲካዊ እና ኢኮኖሚያዊ ተፅዕኖዎች በዚህ አጭር ግዜ በስትራቴጂው ላይ ለመስራት አይከብድም?

አንድ ነገር ስትሰራ እንድትሰራው የሚገፋፋህ ሌላ ነገር አለ፡፡ የስትራቴጂ እቅዱ መነሻ ሃሳብ ነው፡፡ ጋዜጣዊ መግለጫ እየሰጠን በባለሙያም እያስተቸን ነው የነበረው፡፡ ሶት አናሊሲስ ተሰርቶበታል፡፡ እኔ ይሄን በማድረጌ ደስተኛ ነኝ፡፡ እኔ ካልገባሁ ካልተመረጥኩ ለሚሰራ ሰው እንደመነሻ ሃሳብ ይጠቀምበታል፡፡ ከገባሁ ደግሞ እኔ ራሴ እንደገና ከልሼ ሰርቼ ባለሙያ ጨምሬበት ነው ያቀረብኩት፡፡ ጣጣው ያለቀለት ዶክመንት አልነበረም፡፡ ነገር ግን አሁን የምታየው ነገር ለምርጫ ስራ ተብለው የሚሰሩ ታምፕሌቶችን ታያለህ፡፡ በእውነት ነው የምልህ እንደትናንት እና እንደዛሬ አፋር ውስጥ እንደሚደረገው ሩጫ በዚህ ሙቀት እንደምንሮጠው ሩጫ ብንሮጥ ኖሮ  31 ዓመት አይደለም ሁለት ዙር አያልፈንም ነበር የአፍሪካ ዋንጫ፡፡ ስትራቴጂውን ሳወጣ ተፎካካሪዎቼን፣ በዩኒቨርሲቲ ደረጃ የሚያስተምሩትን ጠርቼ የሚጨመር እና የሚቀነሱ ነገሮችን አስለይቿለው፡፡ የመጡልን አስተያየቶች ተቀብለናል፡፡ አሁንም ይዳብራል፡፡ የምንወዳደር ከሆነ ጭብጥ ላይ መሆን አለበት፡፡ የአንተን ስም አጥፍቼ ድምፅ ማግኘት አልፈልግም፡፡ አላደረገውም! የጠቅላላ ጉባኤ አባላት አስካሁን ለእንግዳ ነው ድምፅ ስንሰጥ የነበረው፡፡ በእንግድነት መጥቶ የይለፍ ካርድ እንሰጠዋለን ከአራት ዓመት በኃላ ውጥንቅጣችን ወጥጦ ሌላው ደግሞ ወደ ራሱ ቢዝነስ ይመለሳል፡፡ እኔ ጥሩ ደሞዝ ተከፋይ ነኝ፡፡ እኔ የግል ጥቄሜን አጥቼ ነው ክልሌም ስላመነብኝ ነው ይሄን የማደርገው፡፡ ይሄን የሚያነብ ተፎካካሪ ካለም ዶክመንቱን ለመስጠት በሬ ክፍት ነው፡፡ እግርኳስ ፌደሬሽን በጣም የተከፋፈለ ነው፡፡ እግርኳስ ውስጥ ስለሰራው ሁሉን ነገር እመራለው ማለት አይደለም፡፡ የማርኬቲንግ፣ የህክምና፣ የቴክኒክ እና አስተዳደር ስራ አለ፡፡ ይሄንን በእውቀት መምራት ያስፈልጋል፡፡