የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ዛሬ በአፋር ሰመራ ባከናወነው ምርጫ አቶ ኢሳይያስ ጂራ አዲሱ ፕሬዝዳንት ሆነው በአብላጫ ድምፅ ተመርጠዋል።
ከምርጫው 144 ድምፆች ከቀረቡት አራት እጩዎች መካከል አቶ ተስፋይ ካሕሳይ 3፣ የቀድሞው ፕሬዝዳንት አቶ ጁነይዲ ባሻ 28፣ የቀድሞው ም/ፕሬዝዳንት አቶ ተካ አስፋው 47 ሲያገኙ አቶ ኢሳይያስ ጂራ 66 ድምፅ በማግኘት ቀዳሚ መሆን ችለዋል። ሆኖም የአስመራጭ ኮሚቴው የምርጫ ውጤቱን ይፋ አድርጎ አቶ ኢሳይያስ ፕሬዝዳንት መሆናቸውን ከገለፀ በኋላ በምርጫ ህጉ ላይ የተቀመጠው የአብላጫ ድምፅ ሳይሆን የ50+1 ህግ ነው በሚል ድጋሚ ምርጫ እንዲካሄድ ተወስኗል።
በድጋሚ ምርጫው አቶ ጁነይዲ እና አቶ ተስፋይ ከምርጫው ራሳቸውን ሲያገሉ በአቶ ኢሳይያስ እና አቶ ተካ መካከል በተደረገው ምርጫ አቶ ኢሳይያስ ጂራ 87-58 በማሸነፍ ፕሬዝዳንትነታቸው ተረጋግጧል።
በምዕራብ ወለጋ ዞን ጊምቢ ወረዳ በ1964 የተወለዱት አቶ ኢሳይያስ በባዮሎጂ የመጀመርያ ዲግሪ ያላቸው ሲሆን ባለፉት 22 ዓመታት የሠቃ ወረዳ ስፖርት ቢሮ ኃላፊ፣ የሰበታ ስፖርት ቢሮ ኃላፊ፣ የጅማ ከተማ ክለብ ፕሬዝዳንት፣ የሰበታ ከተማ ክለብ ስራ አስኪያጅ እንዲሁም የጅማ ስፖርት ቢሮ ኃላፊ ሆነው ሰርተዋል። ከ2009 ጀምሮ አሁን እስካሉበት ጊዜ ድረስም የጅማ አባጅፋር ስራ አስኪያጅ ሆነው እየሰሩ ቆይተዋል።