ኮ/ል አወል አብዱራሂም የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ምክትል ፕሬዝዳንት ሆነው ተመረጡ

የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ምርጫ ቀኑን ሙሉ ተካሂዶ እስከ ምሽት 05:00 ከዘለቀ በኋላ ምክትል ፕሬዝዳንቱን አውቋል። የቀድሞው የደደቢት ክለብ ፕሬዝዳንት ኮሎኔል አወል አብዱራሂምም በአብላጫ ድምፅ ተመርጠዋል።

በስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባልነት በተመረጡት 10 አባላት መካከል በሚካሄደው በዚህ ምርጫ 6 ተወዳዳሪዎች የቀረቡ ሲሆን ከነዚህ መካከል ኮ/ል አወል በ44 ድምፅ ተመርጠዋል። አቶ አበበ ገላጋይ 30 ድምፅ በማግኘት ሁለተኛ ደረጃን ሲይዙ አቶ ዮሴፍ ተስፋዬ በ27 ነጥብ ሶስተኛ ደረጃን ይዘዋል።

በኢትዮጵያ እግርኳስ የቅርብ አመታት ተፅእኖ መፍጠር ከቻሉ ግለሰቦች መካከል አንዱ የሆኑት ኮ/ል አወል በ1989 ደደቢትን በመመስረት ኦስከ 2005 በፕሬዝዳንትነት የቆዩ ሲሆን በ2002 ወደ ፕሪምየር ሊግ ካደገው ቡድን ጋር አንድ የሊግ እና አንድ የኢትዮጵያ ዋንጫን አሳክተዋል።