ሁሉም የ25ኛ ሳምንት ጨዋታዎች በነገው እለት በሚስተናገዱበት የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ በዋንጫ ፉክክሩ ውስጥ ቀጥተኛ ተሳታፊ የሆኑ ክለቦች የሚያደርጓቸውን ጨዋታዎች በክፍል አንድ ቅድመ ዳሰሳችን ተመልክተናቸዋል።
ጅማ አባ ጅፋር ከ ቅዱስ ጊዮርጊስ
በእኩል 41 ነጥቦች 2ኛ እና 3ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጡትን ሁለቱን ቡድኖች የሚያገናኘው ይህ ጨዋታ የ25ኛ ሳምንት ቁጥር አንድ ተጠባቂው ጨዋታ ሆኗል። ውጤቱ በተጋጣሚዎቹ ላይ ብቻም ሳይሆን በሊጉ መሪ መቐለ ከተማ እንዲሁም ተከታያቸው ኢትዮጵያ ቡና ላይ የሚኖረው ተፅዕኖም የብዙዎችን ትኩረት እንዲያገኝ ምክንያት ሆኗል። ከሶስት ተከታታይ ድሎች በኃላ ሊጉን መምራት ጀምሮ የነበረው ጅማ አባ ጅፋር በመቀጠል ያስመዘገባቸው ሶስት የአቻ ውጤቶች ወደ ሁለተኝነት ዝቅ እንዲል አድርገውታል። ቅዱስ ጊዮርጊስም እንዲሁ ባሳለፍናቸው ሶስት ሳምንታት ድል የቀናው በአንድ አጋጣሚ ነበር። በቀሩት ሁለት ጨዋታዎች ግን እንደተጋጣሚው ሁሉ ነጥብ ለመጋራት ተገዷል። በነገው የእርስ በእርስ ግንኙነታቸው ግን ማሸነፍ ብቸኛው ተጠቃሚ የሚያደርጋቸው ውጤት በመሆኑ እጅግ ከባድ የሜዳ ላይ ፉክክር እንደሚያደርጉ ይጠበቃል።
የጅማ አባ ጅፋሩ ሁለተኛ ግብ ጠባቂ ዳዊት አሰፋ ጉዳት ላይ ከመገኘቱ በቀር ቀሪው የባለሜዳዎቹ ስብስብ ለጨዋታው ብቁ እንደሆነ ተሰምቷል። በመከላከያው ጨዋታ አዳነ ግርማን በቀጥታ ቀይ ካርድ ባጣው ቅዱስ ጊዮርጊስ በኩል ግን ሳላዲን ሰይድ ፣ አማራ ማሌ እና ሪቻርድ አፒያ ጉዳት ላይ መሆናቸው የሚታወስ ነው። ከዚህ ጋር በተያያዘ ሌላው የቡድኑ አጥቂ አሜ መሀመድ ከጉዳት መልስ ቡድኑን የሚያገለግልበት ዕድል ይኖራል።
ለዋንጫው ግምት የሚሰጣቸው ቡድኖች የሚገናኙበት ጨዋታ ከመሆኑ አንፃር እና ከእርስ በእርስ ግንኙነቶች የሚሸመቱ ነጥቦች ካላቸው ወሳኝነት አንፃር ቡድኖቹ ለጨዋታው የሚዘጋጁበት አዕምሯዊ ሁኔታ ወሳኝ ይሆናል። በዚህ ረገድ ለአመታት በተመሳሳይ ጫና ውስጥ የማለፍ ልምድ ያለው ቅዱስ ጊዮርጊስ የተሻለ ቦታ የሚሰጠው ሲሆን የእስካሁኑ ስኬቱ እንዳለ ሆኖ አዲስ አዳጊው አባ ጅፋር ግን ሲቸገር ይታያል። በሜዳ ላይ ከሚጠበቀው እንቅስስሴ አንፃር ደግሞ ሁለቱም የግድ ግቦችን ማስቆጠር ስለሚኖርባቸው ጫና ፈጥረው የግብ ዕድሎችን ለመፍጠር እንደሚንቀሳቀሱ ይታሰባል። ሁለት የፊት አጥቂዎችን የሚጠቀመው ጅማ አባ ጅፋር አማካይ መስመር ላይ የተጋጣሚውን ቅብብሎች በማቋረጥ በመልሶ ማጥቃት ከግብ ክልላቸው ርቀው ሊጫወቱ ከሚችሉት የቅዱስ ጊዮርጊስ ተከላካዮች ጀርባ ለመግባት እንደሚሞክሩ ይጠበቃል። በዚህ ሂደት ውስጥ ደግሞ ከአጣቂ አማካዮቻቸው በተጨማሪ ከግራ እና ቀኝ የሚነሱት ሁለት አማካዮች የመጨረሻ ኳሶችን የማድረስ ብቃት እና የፊት አጥቂዎቹ ፍጥነት እንዲሁም ውሳኔ አሰጣጥ ትልቅ ቦታ ይኖረዋል። በቅዱስ ጊዮርጊስ በኩል ደግሞ በወልዋሎው ጨዋታ ላይ እንደተመለከትነው አምስት አማካዮችን በመጠቀም እና መሀል ላይ ያለውን ፈተና በርካታ የቅብብል አማራጮችን ፈጥሮ በመወጣት ከኳስ ቁጥጥር የበላይነት የተጋጣሚውን የኃላ ክፍል የመፈተን አማራጭ ቅድሚ የሚሰጠው ይመስላል። ፊት መስመር ላይ ደግሞ ለሚታየው ቅዱስ ጊዮርጊስ የአሜ መመለስ እፎይታ የሚሰጥ ሲሆን የመስመር አጥቂ ተፈጥሮ ያላቸው የመስመር አማካዮቹም ወደ አጥቂው ቀርበው የመጫወት ኃላፊነት ይኖርባቸዋል።
የእርስ በእርስ ግንኙነት እና እውነታዎች
– በመጀመርያ ዙር የአዲስ አበባ ስታድየም ግንኙነታቸው ቅዱስ ጊዮርጊስ 3-0 አሸንፏል። ይህ በሊጉ የሁለቱ ክለቦች የመጀመርያ ግንኙነት ነው።
– ቅዱስ ጊዮርጊስ አምና ወደ ጅማ አምርቶ ሌላው የከተማው ቡድን ጅማ አባ ቡናን 1-0 አሸንፎ ተመልሷል።
– በሁለተኛው ዙር ሶስት ጊዜ ከሜዳው የወጣው ቅዱስ ጊዮርጊስ ሁለት ነጥቦችን ሲያሳካ አባ ጅፋር ደግሞ ሜዳው ላይ ካስተናገዳቸው አራት ጨዋታዎች ሶስቱን አሸንፎ በአንዱ አቻ ተላለያይቷል።
ዳኛ
– በኢንተርናሽናል ዳኛ በአምላክ ተሰማ እንደሚመራ ምድባ ተደርጎለት የነበረው ይህ ጨዋታ በአምላክ የአለም ዋንጫ ዝግጅት ላይ በመሆኑ ለፌደራል ዳኛ ይርጋለም ወልደጊዮርጊስ ተላልፏል።
ድሬዳዋ ከተማ ከ መቐለ ከተማ
በዚህ ሳምንት ከሚደረጉ ጨዋታዎች ብቸኛው በሰንጠረዡ የላይኛው እና የታችኛው ክፍል የሚገኙ ቡድኖችን የሚያገናኝ ጨዋታ ነው። ወደ ጎንደር አቅንቶ አንድ ነጥብ ይዞ የተመለሰው ድሬዳዋ ከተማ ባለፉት አራት ጨዋታዎች 8 ነጥቦችን በማሳካት ከወራጅ ቀጠናው የመራቅ ህልሙን ለማሳካት እየተቃረበ ይገኛል። የነገውን ከባድ ፈተና በድል በመወጣት ነጥቡን 29 ማድረስ ከቻለ ወደ መሀል ሰፋሪዎቹ የሚጠጋበትን ውጤት ያሳካል። የሊጉ መሪ መቐለ ከተማ በበኩሉ በአንድ ነጥብ ልዩነት የሚከተሉት ቡድኖች እርስ በእርስ የሚያደርጉት ጨዋታ ከድሬዳዋ ሙሉ ነጥብ ይዞ እንዲመለስ የሚያስገድደው ይሆናል። ማሸነፍ ከተፎካካሪዎቹ የሚያርቀውን ያህል አቻ ወይም ሽንፈት መሪነቱን ሊያሳጣው የሚችል በመሆኑም ጨዋታው ከወዲሁ ከፍተኛ ትኩረትን አግኝቷል።
ዘነበ ከበደ ፣ ያሬድ ታደሰ እና ሀብታሙ ወልዴ ከጉዳት የሚመለሱለት ድሬዳዋ ከተማ ብቸኛው በጉዳት የሚያጣው ተጨዋች አማካዩ ሚካኤል አካፉ ብቻ ነው። በመቐለ ከተማ በኩል ደግሞ አቼምፖንግ አሞስ በአምስተኛ ቢጫ ካርድ ቅጣት እንዲሁም ቢስማርክ ኦፖንግ በጉዳት ከጨዋታው ውጪ መሆናቸው ታውቋል።
ሁለት ጠንካራ የመከላከል መሰረት ያላቸውን ቡድኖች የሚያገናኘው ይህ ጨዋታ በማጥቃት ላይ ተሳታፊ ለሆኑ ቡድኖች ፈተና የሚሰጥ ይሆናል። ሁለት በመከላከል ላይ የሚያመዝኑ የአማካይ ክፍል ተጨዋቾችን በጥቅም ላይ የሚያውሉ ቡድኖች እንደመሆናቸውም የማጥቃት አማካዮቻቸው መሀል ለመሀል በሚሰነዘሩ ጥቃቶች ላይ የሚያደርጉትን ተሳትፎ ከባድ ያደርገዋል። በመሆኑም ክፍተትን ለማግኘት በመስመር አማካይነት እና ተከላካይነት የሚሰለፉ ተጨዋች ሀላፊነት ከፍ ያለ ይሆናል። የቡድኖቹ ከተከላካይ አማካዮች ፊት ያለ የሶስትዮሽ ጥምረት ከአጥቂ ጀርባ ቦታ ላይ የሚደረግ የተጠና እንቅስቃሴ የግብ ዕድሎችን ለመፍጠር ወሳኝ ይሆናል። በድሬዳዋ በኩል ዮሴፍ ዳሙዬ እና ሱራፌል ዳንኤል እምብዛም በማጥቃት ላይ የማይሳተፉትን የመቐለን የመስመር ተከላካዮች ቦታ አያያዝ በእንቅስቃሴ ለማስከፈት መሞከር እና በተለይም በቀኝ በኩል የአህመድ ረሺድንም እገዛ መግኘት እንደሚያስፈልገው ይገመታል። መቐለዎች በበኩላቸው በኢማኑኤል ላርያ እና ሳውሬል ኦልሪሽ ሁለት ጎኖች የሚያደርጉት እንቅስቃሴ ወሳኝ ይሆንላቸዋል። ቡድኑ ከሚታወቅበት የግራ መስመር አማካይ ክፍሉ ጥንካሬ ባለፈ የአህመድ የማጥቃት ተሳትፎ በቀኝ በኩልም ጥሩ የማጥቃት አማራጭን ሊሰጠው ይችላል።
የእርስ በእርስ ግንኙነት እና እውነታዎች
– ሁለቱ ቡድኖች በሊጉ ለመጀመርያ ጊዜ የተገናኙት ዘንድሮ ሲሆን በመጀመርያው ዙር መቐለ ላይ ባደረጉት ጨዋታ መቐለ 2-0 አሸንፏል።
– መቐለ ከተማ ወደ ፕሪምየር ሊጉ በታሪኩ ለመጀመርያ ጊዜ ማደጉን ያረጋገጠው ነገ ጨዋታውን በሚያደርግበት ድሬዳዋ ስታድየም ነበር ፤ ሀዲያ ሆሳዕናን በመለያ ጨዋታ 2-1 በማሸነፍ።
– አምስት ጨዋታዎችን በሁለተኛው ዙር ያስተናገደው ድሬደዋ ሶስቱን ሲያሸንፍ በሁለቱ ነጥብ ተጋርቷል። መቐለ ከተማ በበኩሉ ከሜዳው ከወጣባቸው አራት ጨዋታዎች ሁለቴ ሽንፈት ሲገጥመው አንዴ በማሸነፍ አንዴ አቻ በመውጣት ተማልሷል።
ዳኛ
– ፌደራል ዳኛ ወልዴ ንዳው ይህን ጨዋታ በመሀል ዳኝነት ለመምራት ተመድቧል።
ወላይታ ድቻ ከ ኢትዮጵያ ቡና
በዚህ ጨዋታ የሚገኙ ነጥቦች አስፈላጊነት ከወላይታ ድቻ ይልቅ ለኢትዮጵያ ቡና እጅግ አስፈላጊ ይመስላሉ። በርግጥ ባለፉት ሁለት ሳምንታት የአቻ ውጤቶችን ያስመዘገቡት ድቻዎች ከዚያ አስቀድሞ የደረሱባቸው ሶስት ሽንፈቶች በጥቂቱ ላለመውረድ ወደሚደረገው ፉክክር ቢያስጠጋቸውም የከፋ ስጋት ውስጥ ግን አይገኙም። ከበላዩ ያሉት ቡድኖች እርስ በእርስ በሚገናኙበት ቀን ወደ ሶዶ የሚያመራው ኢትዮጵያ ቡና በአንፃሩ ያሳለፍነው ሳምንታት ውጤቶቹ መሪዎቹን በአራት ነጥቦች ልዩነት እንዲከተል ያስገደደው በመሆኑ ውጤት ይዞ የመመለስ ግዴታ ውስጥ ገብቷል። በተለይ ቢያንስ ከበላዩ ካሉት ቡድንምች ሁለቱ በዚህ ሳምንት ካሸነፉ ጨዋታው የአሰልጣኝ ዲዲዬ ጎሜስ ቡድን በዋና ተፎካካሪነት ለመቀጠል የሚያገኘው የመጨረሻው ዕድል ሊሆን ሲችል ወላይታ ድቻ በበኩሉ የግንቦትን ወር ያለድል ላለማጠናቀቅ የሚፋለምበት እንደሚሆን ይጠበቃል።
ወላይታ ድቻ አጥቂው ጃኮ አራፋትን በጉዳት የሚያጣ ሲሆን ክለቡ ያስተላለፈበት የአንድ አመት ቅጣት ይቅርታ ተቀባይነት ቢያገኝም ወደ ሜዳ ያለተመለሰው ወንደሰን ገረመውም ለዚህ ጨዋታ አይደርስም። በኢትዮጵያ ቡና በኩል አስናቀ ሞገስ ከስድስት ጨዋታ ቅጣት በኃላ ወደ ሜዳ ሲመለስ ሌላ የጉዳትም ሆነ የቅጣት ዜና በቡድኑ ውስጥ የለም።
የሶዶ ስታድየም የመጫወቻ ሜዳ ጥራት እንዳለ ሆኖ የቡድኖቹ የአማካይ ክፍል የበላይነት ለውጤታቸው ያለው አስተዋፅኦ ሊጠቀስ ይገባል። ወላይታ ድቻ በተከላካይ አማካዩ እና በፊት አጥቂው መሀል የሚያሰልፋቸው አራት አማካዮች የቡድኑን ሚዛን በመጠበቁ ቁልፍ ሚና ይኖራቸዋል በተለይም በመስመር በኩል የሚንቀሳቀሱት ዮናታን እና እዮብ ቦታ አያያዝ ለቡድኑ የማጥቃት ሽግግር ወሳኝነት ይኖረዋል። ከፊት በአራፋት ጃኮ ምትክ የመሰለፍ ዕድል የሚያገኘው አጥቂም የሚሸፍነውን ሰፊ ቦታ ከመጋራት አንፃር አራቱ አማካዮች ተመጣጣኝ የመማጥቃት እና የመከላከል ተሳትፎ እንዲያደርጉ ይጠበቃል። ከነዚሁ አማካዮች ብርቱ የመከላከል መስመር የሚጠብቀው የኢትዮጵያ ቡና የመሀል ክፍል ደግሞ በሁለቱ መስመሮች እና በመሀል ተገማች ያልሆነ ተመጣጣኝ ጥቃት መሰንዘር ግድ ይለዋል። የሜዳውን ስፋት ለመጠቀም ጥሩ አቋቋምን ሲይዙ የሚታዩት ሳኑሚ እና ሚኪያስም ከመስመር ተከላካይምች ጋር የሚኖራቸው መናበብ እና ወደ ማጥቃት በሚደረጉ ሽግግሮች ውስጥ ፍጥነት የታከለባቸውን ውሳኔዎች በማሳለፍ ተጋጣሚያቸው የመከላከል ቅርፁን ሳይዝ በፊት ሳጥን ውስጥ የመድረስ ሀላፊነት ይኖራባቸዋል።
የእርስ በእርስ ግንኙነት እና እውነታዎች
– ሁለቱ ቡድኖች ለ9 ጊዜያት በሊጉ ተገናኝተው እኩል ሁለት ጊዜ ተሸናንፈዋል። በቀሪዎቹ 5 ጨዋታዎች ደግሞ አቻ ተለያይተዋል። ድቻ 5 ሲያስቆጥር ቡና 7 ጊዜ ኳስ እና መረብን አገናኝቷል።
– በወላይታ ድቻ ሜዳ ላይ በተካሄዱ 4 ጨዋታዎች ድቻ ሁለት አሸንፎ በቀሪዎቹ ሁለት ጨዋታዎች አቻ ሲለያዩ ኢትዮጵያ ቡና ድል አላስመዘገበም።
– ወላይታ ድቻ በሁለተኛው ዙር ከሰበሰባቸው ነጥቦች ሳምንት ከኢትዮ ኤሌክትሪክ አቻ ከተለያየበት ውጪ ቀሪዎቹን 9 ነጥቦችን ያገኘው ሶዶ ላይ ነበር። ኢትዮጵያ ቡና ደግሞ ሰበታ ላይ ከተደረገው የወልዲያ ጨዋታ በቀር ሁለቴ ከአዲስ አበባ ወጥቶ ከሲዳማ በድል ከአርባምንጭ ደግሞ በሽንፈት ተመልሷል።
ዳኛ
– ይህን ጨዋታ የመዳኘት ሀላፊነት የተሰጠው ለኢንተርናሽናል ዳኛ ብሩክ የማነብርሀን ነው።