ፕሪምየር ሊግ | የ25ኛ ሳምንት ጨዋታዎች ቅድመ ዳሰሳ – ክፍል 2

በዛሬው የክፍል ሁለት ቅድመ ዳሰሳችን ላለመውረድ በሚደረገው ፉክክር ውስጥ ከሚገኙ ክለቦች አራቱ የሚሳተፉባቸው ጨዋታዎች ላይ ትኩረት አድርገናል።

አዳማ ከተማ ከ ኢትዮ ኤሌክትሪክ

በሳምንቱ ከሚካሄዱ ጨዋታዎች መሀከል ለአንደኛው ተጋጣሚ እጅግ አስፈላጊ ከሁኑ ጨዋታዎች መሀከል ይህ የአዳማ አበበ ቢቂላ ስታድየም ጨዋታ ይጠቀሳል። በውድድር አመቱ ለመጀመሪያ ጊዜ ሁለት ተከታታይ ሽንፈት የደረሰበት አዳማ ከተማ ከዋንጫ ፉክክሩ ለመራቅ ተገዷል። ይህን ጨዋታ ማሸነፍ ወደ ፉክክሩ መልሶ ሊያስጠጋው ቢችልም ከዛ በላይ ግን ያለፉት ሳምንታት ውጤቶቹን ለመርሳት ይህን ጨዋታ በድል መወጣት ግድ የሚለው ይሆናል። ጥሩ መሻሻል እያሳየ የሚገኘው ኢትዮ ኤሌክትሪክ በበኩሉ ከበታቹ የሚገኙት ቡድኖች እርስ በእርስ እንደመጫወታቸው ከአዳማ ነጥብ ይዞ መመለስ እጅግ አስፈላጊው ነው። ይህ የማይሆን ከሆነ ግን ከሁሉም በላይ ከፍተኛ የግብ ዕዳ ያለበት ኤሌክትሪክ ከፍተኛ መጠጋጋት ባለበት የሰንጠረዡ የመጨረሻ ክፍል አሁንም ቢያንስ በአንድ ደረጃ ዝቅ ሊል የሚችልበት ዕድል ይፈጠራል።

አዳማ ከተማ ዳዋ ሆቴሳን በ5 ቢጫ ካርድ ቅጣት የማያሰልፍ ሲሆን ኤፍሬም ዘካሪያስ ከጉዳት ይመለሳል። ኢትዮ ኤሌክትሪክ ደግሞ ከጉዳት እና ቅጣት ነፃ የሆነ ስብስቡን ወደ አዳማ ይዞ ይጓዛል።

አዳማ ከተማ በሜዳው ዳግም ሽንፈትን ማስተናገድ እንደማይፈልግ እና ኢትዮ ኤሌክትሪክ ደግሞ አንድ ነጥብም ቢሆን ይዞ መመለስ ከሚጨምርለት ተስፋ አንፃር ስንመለከተው ጥንቃቄ አዘል የሜዳ ላይ እንቅስቃሴን ከጨዋታው እንጠብቃለን። ካለው የስብስብ ጥራት አንፃር አማካይ ክፍል ላይ ብዙም እጅ ሲሰጥ የማይታይ የነበረው አዳማ ከተማ አሁን ላይ ተዳክሟል። የነከንዐን ማርክነህ ፣ ሱራፌል ዳኛቸው እና በረከት ደስታ ጥምረትም በቅርብ ሳምንታት ኢትዮ ኤሌክትሪክ በአመዛኙ ጥቅም ላይ ካዋለው እና ውጤት እያሳየ ከሚገኘው የአዲስ ነጋሽ እና ኄኖክ ካሳሁን የተከላካይ አማካይነት ሚና ሲገናኝ የሚኖረው ፉክክር ተጠባቂ ነው። በሌላ በኩል የኢትዮ ኤሌክትሪክ የኃላ ክፍል የግል ስህትቶች እና በግራ ጎኑ ላይ የሚደረጉት ተደጋጋሚ ለውጦች ሲፈጥሩ የሚታዩት የመናበብ ችግሮች ለአዳማ ከተማ የቀኝ መስመር ማጥቃት የሚሰጠው ክፍተት ለቀይ ለባሽዎቹ ስጋት ይመስላል። በዛው መጠን ደግሞ በታታሪው ዲዲዬ ለብሪ የሚሸፈነው የኢትዮ ኤሌክትሪክ የግራ መስመር ጥቃት ለአዳማዎች ፈተና የመሆን አቅሙ ከፍ ያለ ነው። ከዚሁ መስመር በሚነሱ እንቅስቃሴዎች የአዲስ ነጋሽ የማጥቃት ተሳትፎ እና የካሉሻ አልሀሰን ብቃት ሲጨመርባቸው ከጠንካራ የተከላካይ ክፍል ጋር የሚገናኘው እና የቀድሞ ክለቡን ለሚገጥመው ታፈሰ ተስፋዬ በርከት ያሉ ዕድሎችን እንዲያገኝ የሚያስችልም ነው። ከዚህ ውጪ በሁለቱም ቡድኖች በኩል ወደ ሳጥን የሚጣሉ ረጃጅም ኳሶችም ውጤት የመቀየር አቅም ሊኖራቸው እንደሚችል ይታመናል።

የእርስ በእርስ ግንኙነት እና እውነታዎች

– ከ1993 የሚጀምረው የሁለቱ ግንኙነት 31 ጨዋታዎች ላይ ደርሷል። ከእነዚህ መካከል አዳማ 17 ጨዋታ በማሸነፍ የበላይነቱን ሲይዝ ኤሌክትሪክ 8 ጊዜ አሸንፏል። በቀሪዎቹ 6 ጨዋታዎች ደግሞ አቻ ተለያይተዋል። አዳማ 23፣ ኤሌክትሪክ 15 ግቦችን ማስቆጠር ችለዋል።

– አዳማ አበበ ቢቂላ ስታድምየ ላይ 16 ጨዋታዎች ሲከናወኑ አዳማ 11 ፣ ኤሌክትሪክ 2 አሸንፈው በሶስት አጋጣሚዎች አቻ ተለያይተዋል።

– ኤሌክትሪክ ባለፉት ሶስት ተከታታይ የአዳማ ጉዞው ነጥብም ሆነ ግብ ሳይዝ ተመልሷል። ለመጨረሻ ጊዜ በሊጉ አዳማን ሜዳው ድረስ ተጉዞ ያሸነፈውም በ2005 የውድድር ዘመን ነው።

– በሁለተኛው ዙር ስድስተኛ ጨዋታውን ሜዳው ላይ የሚያደርገው አዳማ አንድ ሽንፈት እና አራት ድሎች ሲገጥሙት በዚሁ ጊዜ ውስጥ ሁለቴ ብቻ ከአዲስ አበባ የወጣው ኢትዮ ኤሌክትሪክ ማሳካት የቻለው 1 ነጥብ ነው።

ዳኛ

– ፌደራል ዳኛ ዳንኤል ግርማይ ይህን ጨዋታ በመሀል ዳኝነት ለመምራት ሀላፊነት ተሰጥቶታል።

ወልዲያ ከ ወልዋሎ ዓ.ዩ

ላለመውረድ በሚደረገው ፉክክር ውስጥ ትልቅ ቦታ የሚኖረው ይህ ጨዋታ ቀደም ብሎ እንደተወሰነው ሁሉ በገለልተኛ ሜዳ አዲስ አበባ ላይ ይደረጋል። በአራት ነጥቦች ልዩነት የሊጉ ግርጌ ላይ የሚገኙት ሁለቱ ቡድኖች እርስ በእርስ መገናኘታቸው ጨዋታውን በከፍተኛ ትኩረት እንዲያደርጉት የሚያስገድድ ነው። በተለይ በሁለተኛ ዙር አንዴም ድል ያልቀናው ወልዲያ ነገም ነጥብ ማግኘት ከተሳነው ከበላዩ ካሉት ቡድኖች ጋር በቀላሉ የማያጠበው ክፍተት ይፈጠራል። ለወልዋሎ ዓ.ዩም ሽንፈት ከወልዲያ ጋር በነጥብ የሚያቀራርበው ከመሆኑ ባሻገር ቀሪዎቹ ተፎካካሪዎቹ ድል ከቀናቸው የመውረድ ስጋቱ መባባሱ አይቀርም። ይህ ሁኔታ ሲታሰብ ጨዋታው ሶስት ነጥብ ለማሳካት የሞት ሽረት ትግል የሚደረግበት እንደሚሆን መገመት ይቻላል።

ወልዲያ በረጅም ጊዜ ጉዳት ካጣው ሰለሞን ገብረመድህን ወልዋሎ ዓ.ዩ ደግሞ ቅጣት ከተወሰነባቸው በረከት አማረ አሳሪ አልመሀዲ ውጪ ያሉ ተጨዋቾቻቸውን እንደሚጠቀሙ ይጠበቃል።

የጨዋታው አስፈላጊነት ሁለቱም ነገሮችን በጥንቃቄ እንዲያዩ የሚያስገድድ ነው። የተከላካይ መስመርን የማያጋልጡ ጥቃቶችን መሰንዘር ግብ ቀድሞ ባስቆጠረ ቡድን በኩል ደግሞ ውጤትን ለማስጠበቅ ጥረት የማድረግ ሂደት እንደሚኖር ይገመታል። የወልዲያ የተከላካይ ክፍል አምስት ግቦችን ባስተናገበደት ሳምንት ለዚህ ጨዋታ የግል እና የቡድን ስህተቶችን ላለመፈፀም በስነልቦናው ራሱን አስተካክሎ መቅረብ ይኖርበታል። በሌላ በኩል ቡድኑ መሀል ሜዳ ላይ ሊወሰድበት ከሚችለው የበላይነት አንፃር ፊት ላይ ለሚገኙ አጥቂዎች የሚያደርሳቸው ቀጥተኛ ኳሶች ጥራት ላይ በሚገባ መስራት ይጠበቅበታል። ወልዋሎ ዓ.ዩ ሶስቱን የፊት አጥቂዎቹን ብቃት አሁንም በሚገባው መልኩ አውጥቶ እየተጠቀመ አይመስለም የፕሪንስ እና ፉሰይኒ ታታሪነት እንዲሁም የኦዶንጎ አጨራረስ ብቃት ከአማካይ ክፍሉ ጋር በተጣጣመ መልኩ መቃኘት ከቻለ ተደጋጋሚ የግብ ዕድሎችን ለመፍጠር የሚቸገር አይመስልም። ሆኖም ተጋጣሚያቸው ከተከላካይ መስመር ጀርባ ብዙ ክፍተት የሚተው ባለመሆኑ በተለይም ሁለቱ የመስመር አጥቂዎች በጥልቀት ወደ ኃላ የሚመለሱበት የጨዋታ ሂደት ለቡድኑ አስፈላጊ ይሆናል።

የእርስ በእርስ ግንኙነት እና እውነታዎች

– በፕሪምየር ሊጉ ያደረጉት የመጀመርያ የእርስ በእርስ ግንኙነት ያለ ግብ በአቻ ውጤት ተፈፅሟል።

– ሁለቱ በድኖች በገለልተኛው አዲስ አበባ ስታድየም ካደረጓቸው ሁለት ጨዋታዎች እርስ በእርስ ካደረጉት ጨዋታ አንድ ነጥብ ሲያገኙ ወልዲያ በመቐለ ወልዋሎ ዓ.ዩ ደግሞ በፋሲል ከተማ ተሸንፈዋል።

ዳኛ

– የሁለቱን ቡድኖች ጨዋታ ለመምራት በመሀል ዳኝነት የተመደበው ፌደራል ዳኛ አሸብር ሰቦቃ ነው።

ደደቢት ከ አርባምንጭ ከተማ

በሳምንቱ የመጨረሻ ጨዋታ አዲስ አበባ ስታድየም ላይ የዋንጫ ግስግጋሴው የተገታ የሚመሰለው ደደቢት እና ከወራጅ ቀጠናው ለመውጣት ጥረት ላይ የሚገኘው አርባምንጭ ከተማ ይገናኛሉ። ጨዋታው ከማሸነፍ ከራቀ ሰባት ሳምንታት ካለፉት ደደቢት ይልቅ የአመቱን ከፍተኛ ድል ላስመዘገበው አርባምንጭ ከተማ ዋጋ ያለው ነው። ሁለቱ ቡድኖች የሌሎቹን ውጤት አውቀው ወደ ሜዳ የሚገቡ በመሆኑ የጨዋታው አስፈላጊነት ከፍ ሊል የሚችል ቢሆንም ደደቢትን ዳግም ወደ ዋንጫ ፉክክሩ ለመመለስ የሚያስችል መሆኑ ያጠራጥራል። ለአርባምንጭ ከተማ ግን በዚህ ጨዋታ መሸነፍ በአንድ ነጥብ ልዩነት ወደ ወጣበት የወራጅ ቀጠና ሊመልሰው የሚችል በመሆኑ ወሳኝነቱ ከፍተኛ ነው።

ደደቢት ኩዌኪ አንዶህን በቀጥታ ቀይ ካርድ ቅጣት ሲያጣ የብርሀኑ ቦጋለ እና ክሌመንት ረዞንቶን አገልግሎት  ከጉዳት መልስ እንደሚያገኝ ይጠበቃል። በአርባምንጭ በኩል ገዛሀኝ እንዳለ ከቅጣት ቢመስለም ከቡድኑ ጋር አብሮ ያልተጓዘ ሲሆን ሌላ የጉዳትም ሆነ የቅጣት ዜና ግን የለም።

ዳግም አሸናፊነትን ለማግኝት በጥረት ላይ የሚገኘው ደደቢት በኢትዮጵያ ቡናው ጨዋታ ያደረገው የአሰላለፍ እና የተጨዋቾች ለውጥ በብዙ ጎድቶታል። በዛ ጨዋታ ላይ ወደ 4-4-2 ተመልሶ የነበውረ ቡድኑ የአማካይ ክፍል ላይ የተወሰደበት ብልጫ ሁለቱ አጥቂዎች ለብቻቸው እንዲነጠሉ ያደረገ ነበር። የአቤል እንዳለ እና የአብስራ ተስፋዬ መግባት ከፈጠረው ለውጥ አንፃርም በነገው ጨዋታ ወደ ቀደመው ቅርፁ እንደሚመለስ ይጠበቃል። በመልሶ ማጥቃት ዕቅድ ወደ ሜዳ የሚገባው ተጋጣሚውን ከራሱ ሜዳ ለማራቅም ለቅብብሎች ወሳኝ የሆነው ይህን የአማካይ ክፍሉን ጥንካሬ መልሶ ማግኘት ያስፈልገዋል። በአርባምንጭ በኩል ሁለቱን የደደቢትን የማጥቃት አማካዮች እንቅስቃሴ የሚቆጣጠሩ ሁለት የተከላካይ አማካዮችን በመያዝ በመልሶ ማጥቃት መጫወት ዋነኛ ዕቅዱ ይመስላል። በዚህ ውስጥ ግን እጅግ የመከላከል ተሳትፎ እንዳለ ሆኖ ወሳኝ በሆነው የማጥቃት ሽግግር የመስመር አጥቂዎቹ ቦታ አያያዝ በቶሎ ወደ ተጋጣሚ የሜዳ አጋማሽ ለመግባት የተመቸ እንዲሆን ያስፈልጋል። በዚህም ከደደቢት የመስመር ተከላካዮች ጋር የሚኖሮው ፍልሚያ ተጠባቂ ነው። አርባምንጭ በተደጋጋሚ ከሜዳው ውጪ የሚያስተናግዳቸው በርካታ ግቦችም ከኃላ ጥንቅቄ እንዲወስድ የሚያደርጉት ናቸው።

የእርስ በእርስ ግንኙነት እና እውነታዎች

– በበርካታ አቻዎች የታጀበው የሁለቱ ግንኙነት 13 ጊዜያት በሊጉ ሲስተናገድበት ደደቢት 4 በማሸነፍ የበላይነት ይዟል። አርባምንጭ ሁለት ጊዜ ሲያሸንፍ በ7 አጋጣሚዎች አቻ ተለያይተዋል። ደደቢት 19፣ አርባምንጭ 13 ጎሎች ማስቆጠር ችለዋል።

– በአዲስ አበባ ስታድየም 6 ጊዜ ተገናኝተው ደደቢት ሁለት ጊዜ አሸንፎ አራት ጊዜ አቻ ሲለያዩ አርባምንጭ ምንም አላሸነፈም።

– ያለፉት ሶስት ተከታታይ የአዲስ አበባ ስታድየም ግንኙነቶች በአቻ ውጤት ተጠናቀዋል። በተለይ ባለፈው ዓመት 24ኛ ሳምንት ላይ አርባምንጭ 2-0 ከመመራት ተነስቶ በመጨረሻዎቹ ደቂቃዎች በተቆጠሩ ጎሎች አቻ የተለያየበት ተጠቃሽ ነው።

ዳኛ
– ኢንተርናሽልና ዳኛ አማኑኤል ሀይለስላሴ ይህን ጨዋታ በመሀል ዳኝነት እንደምመራው ይጠበቃል።