ነገ በሊጉ ከሚከናወኑ ስምንት ጨዋታዎች መሀከል ጎንደር እና ሀዋሳ ላይ የሚደረጉት ሁለት ጨዋታዎች የክፍል ሶስት ቅድመ ዳሰሳችን ትኩረቶች ሆነዋል።
ፋሲል ከተማ ከ መከላከያ
በጎንደር ባለው ወቅታዊ የአየር ሁኔታ ምክንያት ፋሲል ከተማ ድሬዳዋን እንዳስተናገደበት ጨዋታ ሁሉ ከመከላከያ ጋርም ረፋድ 4፡00 ላይ ይጫወታል። በዋንጫ ፉክክሩ በራፍ ላይ ሆነው አመቱን የገፉት አፄዎቹ ከድል የራቁባቸው አራት ሳምንታት ይበልጥ ወደ ኃላ እንዲቀሩ አድርጓቸዋል። ከሊጉ መቋረጥ አስቀድሞ በሶስት ጨዋታዎች ዘጠኝ ነጥቦችን ያሳካው መከላከያም ከወራጅ ቀጠና ጣጣ እፎይ ይበል እንጂ ካለፉት ሁለት ጨዋታዎች አንድ ነጥብ ብቻ ማግኘቱ ሙሉ ለሙሉ ከስጋት እንዳይወጣ አድርጎታል። በመሆኑም ፋሲል ከተማ ከሚያዚያ መጀመሪያ በኃላ ማጣጣም ወዳልቻለው ድል ለመመለስ መከላከያም የነጥብ ስብስቡን ከ30 ከፍ አድርጎ በሊጉ ለመደላደል እንደሚፎካከሩ ይጠበቃል።
አወል አብደላ እስከ ውድድር አመቱ መጨረሻ ከማይኖሩት የፋሲል ከተማዎቹ ዓይናለም ኃይለ እና ያሬድ ባየህ እንዲሁም ከመከላከያው ቴዎድሮስ በቀለ በተጨማሪ በጉዳት በዚህ ጨዋታ የማይገኝ ተጨዋች ሲሆን አዲሱ ተስፋዬ እና ዳዊት እስጢፋኖስ ከመከላከያ በቅጣት ወደ ጎንደር አልተጓዙም።
ከፋሲል ከተማ በሜዳው የማሸነፍ ጫና በቀር በተሻለ የውጤት ነፃነት ወደሜዳ የሚገቡት ሁለቱ ቡድኖች ማጥቃትን መሰረት ያደረገ አጨዋወት እንደሚተገብሩ ይጠበቃል። ዋነኛ የጨዋታ አቀጣጣዩ ዳዊት እስጢፋኖስን የማያገኘው መከላከያ እንደወትሮው ሁሉ የመሀል ሜዳ የኳስ ቁጥጥር የበላይነትን መሰረት አድርጎ አምስት አማካዮችን በመያዝ ወደ ሜዳ እንደሚገባ ይገመታል። ፋሲል ከተማም ሶስት አጥቂዎቹን ከፊት በማሰለፍ እና በመስመር አጥቂዎቹ ለአማካይ ክፍሉ ድጋፍን በመስጠት መሀል ሜዳ ላይ እንደሚፋለም ይታሰባል። ከጀርባቸው በርከት ካሉ ተጨዋቾች እገዛን የሚያገኙት የሁለቱ ቡድኖች ብቸኛ አጥቂዎች የአጨራረስ ብቃት እንዳለ ሆኖ በጨዋታው መሀል ሜዳ ላይ የሚኖረው ፉክክር ይበልጥ ወሳኝ ይሆናል። በርካታ ዕድሎችን እየፈጠረ ግብ ለማስቆጠር በሚቸገረው ፋሲል ከተማ በኩል ከሶስቱ አማካዮች ወደ ፊት ተጠግቶ የመጫወት ሀላፊነት የሚኖረው ኤርሚያስ ሀይሉ ከመከላከያ የተከላካይ አማካዮች ፊት የሚኖረው የቅብብል ስኬት ከመስመር አጥቂዎቹ በቂ የቅብብል አማራጮችን የሚጠይቅ ሲሆን በመከላከያ በኩልም ቴዎድሮስ ታፈሰ ተመሳሳይ ሀላፊነት ይጣልበታል። ሆኖም መከላከያ በተፈጥሯዊ አማካዮች እንደመጠቀሙ የቁጥር ብልጫ ሊወስድ የሚችልበት ዕድል ሰፊ ይሆናል።
የእርስ በእርስ ግንኙነት እና እውነታዎች
– በሊጉ ለ4 ጊዜያት ተገናኝተው ፋሲል ሁለት ጨዋታ በማሸነፍ የበላይነቱን ሲይዝ መከላከያ አንድ ጨዋታ አሸንፎ በቀሪው አንድ ጨዋታ አቻ ተለያይተዋል። ፋሲል 6፣ መከላከያ 3 ጎሎቸን አስቆጥረዋል።
– መከላከያ ፋሲልን ያሸነፈበት ብቸኛ ጨዋታ በ2000 በተደረገው የመጀመርያ የእርስ በእርስ ግንኙነታቸው ወቅት ነው። (1-0)
– ጎንደር ላይ ለመጀመርያ ጊዜ የተገናኙት አምና ሲሆን ፋሲል 3-0 አሸንፏል።
ዳኛ
– ይህንን የሳምንቱ የመጀመሪያ ጨዋታ ፌደራል ዳኛ ቢኒያም ወርቅአገኘው እንደሚመራው ይጠበቃል።
ሀዋሳ ከተማ ከ ሲዳማ ቡና
ከሁለቱም የሊጉ ፉክክሮች ርቀው በ8ኛ እና 9ኛ ደረጃ ላይ የሚገናኙት ሀዋሳ እና ሲዳማ ተነሳሽነታቸውን ከፍ የሚያደርግላቸው ጨዋታቸው ከፍተኛ የደርቢ ይዘት ያለው መሆኑ ነው። ካለፉት ሶስት ጨዋታዎች አንድ ነጥብ ብቻ ያሳካው ሀዋሳ ከተማ በደረጃ ይብለጥ እንጂ በወቅታዊ አቋም ደረጃ ከሚያዚያ አጋማሽ ጀምሮ ሽንፈት ሳይገጥመው ከዘለቀው ሲዳማ ቡና አንፃር ውጤቱ ዝቅ ያለ ነው። በእርግጥ መሰል ጨዋታዎች ቡድኖች ከሚገኙበት ደረጃ ፣ ከያዙት ነጥብ እና ከሰሞንኛ አቋማቸው በላይ እርስ በእርስ መገናኘታቸው ብቻውን የሚፈጥረው የፉክክር ስሜት ከፍተኛ ነው። ከነዚህ ነጥቦች አንፃር የነገው ሩድዋ (የወንድማማቾች) ደርቢ ከፍተኛ ፍልሚያ የሚደረግበት እንደሚሆን ይጠበቃል።
በሀዋሳ ከተማ በኩል እስከ ውድድር ዘመኑ መጨረሻው የማይኖረው አዲስ አለም ተስፋዬን ጨምሮ አምበሉ ደስታ ዮሀንስ ፣ ዳንኤል ደርቤ ፣ ዮሀንስ ሴጌቦ ፣ ቸርነት አውሽ እንዲሁም ግብ ጠባቂው ተክለማርያም ሻንቆ በጉዳት ከነገው ጨዋታ ውጭ ሲሆኑ ጅብሪል አህመድ እና እስራኤል እሸቱ ደግሞ ከጉዳት ወደ ሜዳ እንደሚመለሱ ይጠበቃል። ሲዳማ ቡናም እንደተጋጣሚው ሀሉ አምበሉ ፍፁም ተፈሪን በጉዳት ሲያጣ በፌድሬሽኑ ወደ ክለቡ እንዲመለሱ የተወሰነላቸው አሺያ ኬኔዲ እና መሀመድ ኮናቴም ክለቡ ውሳኔውን አለመቀበሉን ለፌዴሬሽኑ በደብዳቤ በማሳወቁ ከቡድኑ ጋር አይገኙም።
የደርቢ ጨዋታ እንደመሆኑ የሜዳ ላይ የፉክክር መንፈስን ተከትሎ የሚኖሩ ጉሽሚያዎች የሚበረክቱበት እንዲሁም ፈጣን ሽግግሮች የሚታዩበት ጨዋታ ሀዋሳ ላይ ይጠበቃል። የሀዋሳ ከተማ የመስመር ተከላካዮች የማጥቃት ተሳትፎ ከፈጣኖቹ የሲዳማ የመስመር አጥቂዎች ጋር የሚገናኙባቸው አጋጣሚዎች ከሚያሳዩን ፍልሚያዎች በተጨማሪ መሀል ሜዳ ላይ ማን የበላይ ሆኖ ይወጣል የሚለውን ጥያቄ ለመመለስም ወሳኝ ይሆናሉ። መስመር ላይ የሚኖሩት እንቅስቃሴዎች በሽግግሮች ላይ ተጋጣሚዎች እንደሚኖራቸው ፍጥነት እና ቦታ አያያዝ ለአማካይ ክፍል ተሰላፊዎቹ የማጥቃት ተሳትፎ አማራጮችን ከመፍጠር አኳያ አስፈላጊ ጉዳዮች ናቸው። መሀል ሜዳ ላይ አጫጭር ቅብብሎችን በማድረግ ተጋጣሚዎች ላይ ብላጫ የሚወስደው በታፈሰ ሰለሞን የሚመራው አማካይ ክፍል በቅርብ ሳምንታት ጥሩ ጥምረትን ካገኘው የሲዳማ የመሀል ሜዳ ተሰላፊዎች ጋር የሚገናኝበት ሂደትም ተጠባቂ ነው። የፍፁም ተፈሪ ፣ ዮሴፍ ዮሀንስ እና ወንድሜነህ አይናለም ጥምረት ሲዳማን ባለፉት ሳምንታት ጥሩ ውጤት እንዲያገኝ ምክንያት የሆነ ሲሆን አሁን ደግሞ የፍፁም ጉዳት ታክሎበት በሊጉ ካሉ ጥሩ የመሀል ክፍል አደረጃጀት ካላቸው ቡድኑ ከአንዱ ጋር ተገናኝቶ የሚፈተን ይሆናል።
የእርስ በእርስ ግንኙነት እና እውነታዎች
– ለ17 ጊዜያት በሊጉ የተገናኙት ሁለቱ ቡድኖች እኩል 5 ጊዜ ተሸናንፈው 7 ጊዜ ነጥብ ተጋርተዋል። ሀዋሳ 18 ጎሎች ሲያስቆጥር ሲዳማ 20 ጎሎች ማስቆጠር ችሏል።
– ሀዋሳ ላይ በተካሄዱ 8 ጨዋታዎች ሀዋሳ ሁለት ጊዜ፣ ሲዳማ አንድ ጊዜ አሸንፈዋል። አምስቱ ቀሪ ጨዋታዎች በአቻ ውጤት የተጠናቀቁ ናቸው።
ዳኛ
– ፌደራል ዳኛ ሀይለየሱስ ባዘዘው ጨዋታውን በመሀል ዳኝነት ለመምራት ተመድቧል።