በ25ኛው ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ወራጅ ቀጠናው ውስጥ የተገኙትን ወልዲያን እና ወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርስቲን ያገናኘው ጨዋታ በወልዋሎ 1-0 አሸናፊነት ተጠናቋል፡፡ የጋናዊው አጥቂ ሪችመንድ አዶንጎ የሁለተኛ አጋማሽ የፍፁም ቅጣት ምት ግብ የሁለቱ ቡድኖች ልዩነት ነበረች፡፡
ከጨዋታው መጀመር አስቀድሞ የወልዋሎ ተጫዋቾች በድንገት ህይወታቸውን ላጡት የደደቢቱ አሰልጣኝ ንጉሴ ደስታ መታሰቢያ ባነር ይዘው ወደ ሜዳ የገቡ ሲሆን የአንድ ደቂቃ የህሊና ፀሎትም ለአሰልጣኙ ተደርጓል፡፡
በውጤት ቀውስ ውስጥ የሚገኘው ወልዲያ ባሳለፍነው ሳምንት በአርባምንጭ ከተማ በሰፊ ግብ ልዩነት ከተሸነፈው ቡድኑ ውስጥ የሶስት ተጫዋቾች ቅያሬ አድርጎ ጨዋታውን ሲጀመር ተጋጣሚው ወልዋሎ በበኩሉ ከጅማ አባ ጅፋር ጋር ነጥብ ከተጋራው ቡድኑ ውስጥ የአንድ ተጫዋች ለውጥ አድርጓል፡፡
በፈጣን እንቅስቃሴ በተጀመረው የሁለቱ ክለቦች ጨዋታ ወልዲያ ግብ ለማስቆጠር የሚችልበትን ግልፅ እድል ያገኘው ገና በሁለተኛው ደቂቃ ነበር፡፡ ከግራ መስመር የተሻገረውን ኳስ መስፍን ኪዳኔ ቢያገኝም በማይታመን መልኩ ግብ ማስቆጠር ሳይችል ቀርቷል፡፡ መስፍን ከደቂቃ በኃላ የጨረፈውን ኳስ የወልዋሎ ግብ ጠባቂ ዩሃንስ ሽኩር አድኖበታል፡፡ በአራተኛው ደቂቃ ዋለልኝ ገብሬ እና በ15ኛው ደቂቃ አለምነህ ግርማ ከሞከሯቸው ሁለት ኢላማቸውን ያልጠበቁ ሙከራዎች ውጪ ወልዋሎዎች የግብ አጋጣሚ ሲፈጥሩ አልተስተዋለም፡፡ የመሃል ሜዳ ብልጫን ለመውሰድ በሚደረጉ ትግሎች እና በሚቆራረጡ የቅብብል ስኬቶች የቀጠለው ጨዋታው ወልዋሎች ወደ ግራ መስመር ተከላካዩ አለምነህ አድልተው የማጥቃት እንቅስቃሴያቸውን ሲያደርጉ ወልዲያዎች በበኩላቸው አንዱአለም ንጉሴን መሰረት ያደረገ እንቅስቃሴን ይከተሉ ነበር፡፡ በደቂቃ ልዩነቶች ውስጥ ወልዲያዎች ግብ ለማስቆጥ ከጫፍ ደርሰው ሳይሳካለቸው ቀርቷል፡፡ በ27ኛው ደቂቃ ተስፋዬ አለባቸው ከርቀት የመታውን ቅጣት ምት ዩሃንስ ሲያወጣበት ከደቂቃ በኃላ ከማዕዘን ምት የተሻገረውን ኳስ የወልዋሎ ተከላካዮች ከግቡ መስመር ላይ ወደ ወጪ አውጥተዋል፡፡ የአጋማሹ መገባደጃ ላይ ወልዲያዎች ይበልጥ ጫና ፈጥረው ቢጫወቱም ለእረፍት ግን ቡድኖች ያለግብ ነበር ያመሩት፡፡
ከእረፍት መልስ በአዲስ አበባ ስታዲየም የጣለውን ከባድ ዝናብ ተከትሎ የመጫወቻ ሜዳው ውሃ በመቋጠሩ እና በመጨቅየቱ ሁለቱ ቡድኖች በጨዋታው እንዲቸገሩ አድርጓል፡፡ እምብዛም የግብ ማግባት እድሎች ባልተፈጠሩበት ይህ አጋማሽ በቅብብል ወቅት ውሃ ባዘለው ሜዳ ላይ ኳስ ለተፈለገው ተጨዋች አለመድርሷ በቀላሉ የሁለቱ ቡድኖች የማጥቃት እንቅስቃሴ ላይ እክልን ፈጥሯል፡፡ የወልዲያ ተከላካዮች በ52ኛው ደቂቃ ኳስን ለግብ ጠባቂው ደረጄ አለሙ በመመለስ ላይ ሳሉ ኳስ በመሃል ቀርታ የወልዋሎው አዶንጎ ሞክሮ ወደ ውጪ ወጥቶበታል፡፡ በ56ኛው ደቂቃ አማረ በቀለ ዋለልኝ ላይ የሰራውን ጥፋት ተከትሎ የተሰጠውን ፍፁም ቅጣት ምት አዶንጎ አስቆጥሮ ወልዋሎን መሪ ማድረግ ችሏል፡፡ የአቻነት ግብ ፍለጋ አደም ኮድዞን ቀይረው ያስገቡት ወልዲያዎች አንዱአለም በቶጓዊው ጋር በማጣመር የወልዋሎን የኃላ መስመር ለመፈተን ጥረት አድርገዋል፡፡ በ83ኛው ደቂቃ አዴም ሞክሮ በግቡ አናት ከወጣበት እና አዶንጎ በተመሳሳይ ወደ ውጪ ከሞከረው ሙከራ ውጪ ጨዋታው ይህ ነው የሚባል የግብ እድል ሳይፈጠርበት በወልዋሎ 1-0 አሸናፊነት ተገባዷል፡፡
ድሉን ተከተሎ ወልዋሎ በ27 ነጥብ 13ኛ ደረጃ ላይ ሲቀመጥ ተከታታይ ጨዋታዎች ላይ ነጥብ እየጣለ የሚገኘው ወልዲያ በበኩሉ በ20 ነጥብ የሊጉ ግርጌ ላይ ተቀምጧል፡፡