ዛሬ ከተካሄዱ የሊጉ ጨዋታዎች መሀከል እጅግ ተጠባቂ የነበረው የጅማ አባ ጅፋር እና ቅዱስ ጊዮርጊስ ጨዋታ በአወዛጋቢ ክስተቶች እና በደጋፊዎች ረብሻ ታጅቦ 1-1 በሆነ ውጤት ተጠናቋል።
በስታድየሙ ከተገኘው እጅግ በርካታ ደጋፊ ቁጥር አንፃር ወደ ውስጥ ለመግባት በነበረው ግፍያ ምክንያት ስድስት ሰዎችን ለጉዳት በዳረገ አጋጣሚ የተጀመረው ጨዋታ አጨራረሱ ደግሞ ከዚህም በላይ የከፋ ነበር። ጃማ አባ ጅፋር ሳምንት ከወልዋሎ ዓ.ዩ ጋር ነጥብ በተጋራበት ጨዋታ የተጠቀማቸውን የመጀመሪያ ተሰላፊዎች ሳይቀይር የቀረበ ሲሆን ቅዱስ ጊዮርጊስም በመከላከያው ጨዋታ ላይ በቀይ ካርድ ከሜዳ በወጣው አዳነ ግርማ ምትክ አሜ መሀመድን ከማሰለፉ በቀር ሌላ ለውጥ አላደረገም።
ጨዋታው በመጀመሪያዎቹ 10 ደቂቃዎች በሁለቱም ቡድኖች በፈጣን የመስመር እቅስቃሴዎች ቶሎ ቶሎ ወደ ተጋጣሚ የግብ ክልል መድረስ ቢችሉም የሁለቱም የተከላካይ ክፍሎችን አለፈው ለግብ የቀረበ ኢላማውን የጠበቀ ሙከራ ማድረግ አልቻሉም ነበር። በ11ኛው ደቂቃ ኦኪኪ የአየር ላይ ኳስ በሚሻማበት ወቅት የተሰራበትን ጥፋት ተከትሎ የተሰጠውን ቅጣት ምት በፍጥነት በማስጀመር በአንድ ሁለት ቅብብል ዮናስ ገረመው እና ኄኖክ ኢሳይያስ ወደ ጊዮርጊስ ግብ ክልል በመግባት ሄኖክ ኢሳያስ የሞከረው ኳስ የግቡን ቋሚ ታኮ ወደ ውጭ ወጥቶበታል። ከዚህ ሙከራ በኋላ ጨዋታው በአብዛኛው በመስመር ላይ በሚደረጉ እቅስቃሴዎች እና ለአጥቂዎች በሚላኩ አድራሻ የሌላቸው የአየር ላይ ኳሶች አሰልቺ ሆኖ የቀጠለ ነበር። በዚህም ምክንያት የሁለቱ ቡድኖች የፊት መስመር ተጨዋቾች ኦኪኪ አፎላቢ እና አሜ መሐመድ ወደኋላ ተስበው ለአማካይ ክፍላቸው በመቅረብ ለመጫወት ተገደዋል። በ31ኛው ደቂቃ ኦዝቫልዶ ከቀኝ መስመር ያሻገረለትን አሜ በመቀስ ምት የሞከረው ኢላማውን ያልጠበቀ ሙከራ በእንግዶቹ በኩል ተጠቃሽ ነበር። ከ35ኛው ደቂቃ በኃላም የመሀል ሜዳ ላይ የኳስ ቁጥጥር ብልጫ ለመውሰድ ከሚደረጉ ፉክክሮች አልፎ አልፎ በመስመር የሚላኩ ኳሶች በተከላካዮች ሲጨናገፉ እንዲሁም ግብ ጠባቂዎች በተደጋጋሚ የሚለጓቸው ኳሶች ያለግብ የተጠናቀቀው የመጀመሪያው አጋማሽ ዋና ዋና ገፅታዎች ነበሩ።
ከእረፍት መልስ ከመጀመሪያው አጋማሽ በተሻለ መልኩ ጨዋታውን የጀመሩት ጊዮርጊሶች በ47ኛው ደቂቃ በፈጠሩት ዕድል አሜ ከበኃይሉ የተሻገረለትን ኳስ ወደ ግብ ሳይቀይረው ዳንኤል አጃዬ አውጥቶበታል። በሌላኛው ወገንም በተመሳሳይ በ52ኛው ደቂቃ ተመስገን ከዮናስ የተሻገለትን ኳስ ሳይጠቀምበት ቀርቷል። በ54 ደቂቃ ከማዕዘን ምት የተሻማውን ኳስ ኦኪኪ በግንባሩ ቢሞክርም ሮበርት አድኖበታል። በ61ኛ ደቂቃ ላይ ደግሞ በመልሶ ማጥቃት በሀይሉ ከቀኝ መስመር ያሻገረውን ኳስ ተቀይሮ የገባው አቡበከር ሳኒ በግንባሩ ሲሞክር ዳንኤል አጃዬ ያወጣበት አጋጣሚ አደገኛ ሙከራዎች ነበሩ። 69ኛው ደቂቃ ላይ በግራ መስመር ሳልሀዲን በርጌቾ በኦኪኪ ላይ በሰራው ጥፋት የተሰጠውን ቅጣት ምት ከማሻማት ይልቅ በአንድ ሁለት ቅብብል ለመጀመር የመረጡት አባ ጅፋሮች ኳሱን በመነጠቃቸው በመልሶ ማጥቃት በሀይሉ እና አብዱልከሪም ተቀባብለው በመሄድ በመጨረሻም አብዱል ከሪም በጥሩ መረጋጋት ከአስራ ስድስት ካምሳ ውጭ በማስቆጠር ፈረሰኞቹን ቀዳሚ ማድረግ ችሏል።
ከግቧ መቆጠር በኃላ የቅዱስ ጊዮርጊስ ደጋፊዎች ደስታቸውን በሚገልፁበት ቅፅበት ከአባ ጅፋር ደጋፊዎች ጥቃት የተሰነዘረባቸው በመሆኑ በሽሽት የሜዳውን አጥር ጥሰው ወደ ሜዳ ገብተዋል። በዚህም ምክንያት በርካታ የጊዮርጊስ ደጋፊዎች ላይ የመፈንከት አደጋ ደርሷል። በተፈጠረው ግርግር የተረጋገጡ ደጋፊዎች ቁጥርም ቀላል አልነበረም። ሁኔታው በሜዳ ከተኙት የቀይ መስቀል አባላት አቅም በላይ ሆኖ የጊዮርጊስ ቡድን የህክምና ቡድን አባላት የህክምና እርዳታ ሲሰጡም ተመልክተናል። የእለቱ ኮሚሽነር ፍቃዱ ጥላሁን ሁኔታዎችን አረጋግቶ ጨዋታውን ለመጀመር የጊዮርጊስ ደጋፊዎችን ከአባ ጅፋር ግብ ክልል ጀርባ እንዲሆኑ በማድረግ ጨዋታው ለ30 ደቂቃ የህል ከተቋረጠ በኋላ እንዲቀጥል ሆኗል።
በቀሩት ደቂቃዎች ጊዮርጊሶች ወደ ኃላ አፈግፍገው ለመጫወትና በመልሶ ማጥቃት አደጋ ለመፍጠር ሲሞክሩ አባጅፋሮች ተጭነው በመጫወት ግብ ለማስቆጠር ጥረት አድርገዋል። በተለይ ተቀይሮ የገባው አሮን አሞሀ ጥሩ ሲቀሳቀስ እና ተከላካዮችን የሚያጨንቁ ዕድሎችን ሲፈጥር ቢታይም ጥረቶቹ ኦዶንካራን አልፈው ግብ መሆን አልቻሉም። በዚህ መልኩ በቀጠለው ጨዋታ 88ኛው ደቂቃ ላይ ተቀይሮ የገባው አቡበከር ኄኖክ አዱኛ ላይ በሰራው ጥፋት በቀይ ካርድ ከሜዳ ወጥቷል። አቡበከር በዘንድሮው አመት ሁለተኛ ቀይ ካርዱን ነው የተመለከተው።
መደበኛው የጨዋታ ክፍለ ጊዜ አልቆ የተጨመረው አምስት ደቂቃ ከተጠናቀቀ በኋላ ተጨማሪ ደቂቃዎችን የተጫወቱ ሲሆን በጨዋታው መገባደጃ ላይ ለአባጅፋሮች አጨቃጫቂ የፍጹም ቅጣት ምት ተሰጥቷል። በፍፁም ቅጣት ምቱ ደስተኛ ያልነበሩት እና በአባጅፋር ግብ ጀርባ የነበሩት የቅዱስ ጊዮርጊስ ደጋፊዎች ወደ ሜዳ በመግባታቸውም ጨዋታው በድጋሚ ለ6 ደቂቃ ተቋርጦ ሁኔታው ከተረጋጋ በኋላ በተሰጠው ፍፁም ቅጣት ምት ቀጥሎ ኦኪኪ ግቡን ካስቆጠረ በኋላ ጨዋታው 1-1 በሆነ ውጤት ተጠናቋል።