በ19ኛው ሳምንት የኢትዮጽያ ከፍተኛ ሊግ ምድብ ለ ትላንት እና ዛሬ በተደረጉ ጨዋታዎች ደቡብ ፖሊስ ወደ መሪነት ሲመለስ ሀላባ እና ጅማ አባቡና ነጥብ ተጋርዋል።
ሀላባ ከ ጅማ አባቡና ያደረጉት ተጠባቂው ጨዋታ በአቻ ውጤት ተጠናቋል። በመጀመሪያው አጋማሽ በሁለቱም በኩል ፈጣን እንቅስቃሴ የታየበት ሲሆን በ8ኛው ደቂቃ ሀላባ ከተማ በስንታየው መንግስቱ የመጀመሪያውን የግብ ሙከራ ባደረገበት ቅፅበት የፊት መስመሩን በብቸኝነት ሲመራ የነበረው ብዙዓየው በረጅሙ የተሻገረትን ኳስ ተቆጣጥሮ ሁለት ተከላካዮችን በማለፍ የሞከረው ሙከራ በተከላካይ ጥረት ወደ ማዕዘን ምት ሲቀየር የማዕዘን ምቱን ተመስገን ደረሰ በግንባሩ ገጭቶ የግንቡን ብረት ለትማ ወጥታለች። ሀላባዎች በቀጣይ 30 ደቂቃዎች በጨዋታ በእንቅሳቃሴ ሙሉ ለሙሉ በሚያስብል መልኩ ቢበልጡም ኢላማውን የጠበቀ የግብ ሙከራ ያደረጉት ግን ለሁለት ጊዜ ብቻ ነበር። በ27ኛው ደቂቃ ስንታየው አሸብር ከርቀት የመታውን ኳስ በግብ ጠባቂው እግሮች ማሀል በማለፍ የግቡን አግዳሚ ታካ ስትወጣ አቦነህ ገነቱ ከርቀት መትቶ ግብ ጠባቂው ያዳነበት አጋጣሚዎች የሚጠቀሱ ናቸው። በተቃራኒው ጅማ አባቡና በአጥቂው ብዙዓየው እንዳሻው አማካኝነት የሀላባን የተከላካይ መስመር ሲረብሹ የቆዩ ሲሆን በተለይም በ28ኛው ደቂቃ በቀኝ በኩል የግብ ጠባቂውን አቋቋም ተመልክቶ የመታው ኳስ የግቡ የግራ ቋሚ መልሳበታለች። በ44ኛው ደቂቃም ብዙዓየው እንዳሻው ወደ ግብ አክርሮ በመምታት ኳስ እና መረብ በማገናኘት የመጀሪያው አጋማሽ በጅማ አባቡና መሪነት ተጠናቋል።
ከዕረፍት መልስ ጨዋታ ከመጀመራቸው በፊት በኮሚሽነር ዳዊት አሰፋ አማካኝነት በድንገት ከዚህ አለም ለተለዩን አሰልጣኝ ንጉሴ ደስታ የህሊና ፀሎት የተደረገ ሲሆን ሀላባ ጎል ፍለጋ ፣ ጅማዎች ውጤታቸውን ለማስጠበቅ ተንቀሳቅሰዋል። ስንታየው መንግስቱ በ70ኛው እና በ76ኛው ደቂቃ ያገኛቸው ንፁህ የግብ እድሎችን ሲያመክን ተቀይሮ የገባው መሐመድ ናስርም በ82ኛው ደቂቃ ያገኘውን የግብ ዕድል ሳይጠቀምበት ቀርቷል። በ86ኛው ደቂቃ በቀኝ መስመር ጥሩ ሲንቀሳቀስ የነበረው ስንታየው አሽብር የአቻነቱን ግብ በማስቆጠር ባለሜዳዎቹ ሀላባዎች በሜዳቸው ያለመሸነፍ ጉዘሸቸውን ማስቀጠል ችሏል። ሆኖም ይህ ውጤት ሀላባ ከተማ መሪነቱን ለደቡብ ፖሊስ እንዲያስረክብ ያስገደደ ነበር።
ሌሎች ጨዋታዎች
ደቡብ ፖሊስ ጀ ድሬዳዋ አቅንቶ ድሬዳዋ ፖሊስን 1-0 በማሸነፍ የምድቡን መሪነት ተቆናጧል። የቡድኑን የማሸነፍያ ጎል በ31ኛው ደቂቃ በራሱ ግብ ላይ ያስቆጠረው ዳንኤል ሺበሺ ነው። ውጤቱን ተከትሎ ደቡብ ፖሊስ በ36 ነጥቦች ወደ መሪነት መመለስ ችሏል።
ሀዲያ ሆስዕና ከሀምበሪቾ ያደረጉት ጨዋታ 1-1 ተጠናቋል። የስፖርታዊ ጨዋነት መጓደል በተከሰተበት በዚህ ጨዋታ ሀምበሪቾ በ56ኛው ደቂቃ የመስቀሉ ለቲቦ ጎል መምራት ቢችልም ጎሉ በተቆጠረበት ቅፅበት በሁለቱ ደጋፊዎች ማካከል በተነሳው ፀብ ጨዋታው ለ22ደቂቃ ያህል ተቆርጦ የቀጠለ ሲሆን በ89ኛው ደቂቃ ዋቴሮ ኤልያስ ለሀድያ ሆሳዕና ግብ አስቆጥሮ አቻ መሆን ችለዋል። ከግቡ መቆጠር በኋላ በድጋሚ በተነሳው ውዝግብም ጨዋታው ለ8 ደቂቃ ተቆርጦ ነበር።
በጨዋታው ዙርያ የሁለቱ ቡድን መሪዎችን አስተያየት ይህን ይመስላል:-
ሀዲያ ሆሳዕና
“በ56ኛው ደቂቃ ጨዋታው ተቆርጦ ነበር። ይህ የሆነው ደሞ አንዳንድ ደጋፊዎች በፈጠሩት ጥቃቅን ችግር ነው። የፀጥታ ኃላፊ፣ ፖሊሶች፣ የእለቱ ኮሚሽነር እና እኔ ቦታው ድረስ በመሄድ ያጣራን ሲሆን ጨዋታውን ለማቆረጥ የሚያስችል ችግር ባለመሆኑ ጨዋታው ቀጥሏል። በመጨረሻ ደቂቃ የሆነው የሆሳዕና ግብ የገባው ግብ ሂደት በመቃወም የሀምበሪቾ ተጫዋቹች የፈጠሩት ከባባ ነው እንጂ ሌላ ችግር አልነበረም።”
ሀምበሪቾ
“ይህ ነገር መከሰቱ በጣም ያሳፍራል። ይባስ ብሎ የደቡብ ክልል ስፖርታዊ ጨዋነት ላይ ውይይት ካደረግን በኋላ ደጋፊዎቻችን ተደብድበዋል። እነሱ ካገቡ ባኋላ ክስ ለማስያዝ ብንሞክርም የዕለቱ ዳኛ ሊቀበለን አልፈለገም። በደረሰብን በደል በጣም አዝነናል።”
ለ26ደቂቃ ብቻ ተካሂዶ በዝናብ ምክንያት የተቋረጠው የቤንች ማጂ ቡና እና የነገሌ ከተማ ጨዋታ ዛሬ ላይ ቀጥሎ ፍፃሜውን ሲያገኝ በመጨረሻ ደቂቃ የተቆጠረችው የመሰረት ወልደሰማያት ግብ ለቤንች ማጂ የ2-1 ድል አስገኝታለች። ሻሸመኔ ከተማ 2-1 መቂ ከተማን በማሸነፍ ከወራጅ ቀጠና ለመውጣት የሚደርገውን ትግል ቀጥሎበታል። ይሁን ደጀን በ40ኛው ደቂቃ እንዲሁም አገኘው ሊኬሳ በ85ኛው ደቂቃ የሻሸመኔ ጎሎችን ያስቆጠሩ ተጫዋቾች ናቸው። ሌላው በምድቡ ተጠባቂ የነበረው የቡታጅራ ከተማ እና ዲላ ከተማ ጨዋታ ያለግብ ተጠናቋል።
በቅጣት ምክንያት በዝግ ስታድየም እንዲጫወት የተወሰነበት ወልቂጤ ከተማ ከ 2-1 መመራት ተነስቶ ወደ 3-2 መሪነት መመለስ ቢችልም ጨዋታው 73ኛው ደቂቃ ላይ ሲደርስ ካፋ ቡናዎች ከተፈቀደለት አካል ውጭ ስታዲየሙ ውስጥ ተግኝቷል በሚል ክስ አስምዝግበው አቋርጠው ወጥተዋል።
ዛሬ በተካሄደ ብቸኛ ሙሉ ጨዋታ ወደ ድሬዳዋ ያቀናው ስልጤ ወራቤ ድሬዳዋ ፖሊስን ገጥሞ በገብረመስቀል ዱባለ እና ሙሰፋ ነኪም ጎሎች 2-1 በሆነ ውጤት አሸንፏል።