ጥረት ኮርፖሬት በዛሬው እለት አዲስ አበባ ከተማን አስተናግዶ 2-0 በማሸነፍ የ2010 የውድድር ዘመን የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪምየር ሊግ 2ኛ ዲቪዝዮን ቻምፒዮን መሆኑን አረጋግጧል። ከጨዋታው በኋላ የቡድኑ አሰልጣኝ የሆነችው ሰርካዲስ እውነቱ ለሶከር ኢትዮጵያ የሰጠችውን አስተያየት እንደሚከተለው አቅርበነዋል።
ስለ ውድድር ዓመቱ
“ዓመቱ በጣም ጥሩ ነበር፡፡ ጥሩ እና ደስ የሚል ጊዜያትን አሳልፈናል፡፡ በተለይ ደግሞ እንደ ዋነኛ እቅድ የያዝነውን ነገር በማሳካታችን ደስተኞች ነን፡፡ቡድኔ በጣም ጥሩ ስብስብ ያለው ቡድን ነው፡፡ጥሩ ጥሩ ወጣት እና ታዳጊ ተጨዋቾችን ይዣለው። ይህ ደግሞ የምፈልገውን የጨዋታ እቅድ በቀላሉ ነግሬያቸው እንዲተገብሩት እና ጥሩ ውጤት እናድናመጣ አድርጎናል፡፡
“ሁልጊዜ ስላለብን ጨዋታ እና ተጋሚያችን ስናስብ ምንም አንረበሽም። እንደውም እኛ እንደ መመሪያ አድርገን የምንቀሳቀሰው ተጋጣሚ አንንቅም በተጋነነ ሁኔታም አናከብርም ብለን ነው፡፡ይህ ደግሞ ምንም ሳንፈራ ለሁሉም ቡድኖች እኩል ዝግጅት እያደረግን ለጨዋታ እንድንቀርብ አድርጎናል፡፡”
ስለ ቻምፒዮንነታቸው
“አሸናፊ መሆናችን ይገባናል፡፡ ምክንያቱም በጣም ለፍተን ነበር እኛ በምንወዳደርበት ሊግ ላይ ካሉ ክለቦች የተሻለ የመጫወቻ ከባቢ ያለው የኛ ክለብ ነው፡፡ ተጫዋቾችን ለመጥቀም በሚከፈል ክፍያም ሆነ የተስማማ የመጫወቻ ሜዳ በማዘጋጀት የተሻለ ስራዎችን ቀድመን ሰርተን ነበር። ስለዚህ ቻምፒዮን መሆናችን ያንስብናል እንጂ አይበዛብንም፡፡”
የድል ምስጢር
“እዚህ ደረጃ እንድንደርስ ያደረገን ጠንክረን በህብረት መስራታችን ነው፡፡ ከላይ እንደጠቀስኩት ታዳጊ ተጨዋቾች ስለሆኑ ቡድኔ ውስጥ ያሉት የምፈልገውን ነገር በቀላሉ እንድናደርግ ረድቶናል። ውድድሩን ከመጀመራችን በፊት ዓመታዊ የክለቡን እቅድ ስናወጣ ያለምንም ጥርጥር ቻምፒዮን ለመሆን ነበር። ያንን ደግሞ ለማሳካት ተጨዋቾችን ከማስፈረም ጀምር የተለያዩ ስራዎችን ሰርተናል። ይሄ ደግሞ እንድናሸንፍ ረድቶናል፡፡”
ፈታኝ ጉዳዮች
“ውድድሩ ብዙ ፈታኝ ነገሮች ነበሩበት፡፡ ሁለተኛ ዲቪዝዮን ይባል እንጂ ከስሙ በላይ አድካሚ ነገሮች ነበሩበት፡፡ በክለቦች የቁጥር ብልጫም ሆነ ፉክክር አስቸጋሪ ነገሮች ነበሩበት፡፡ በተደጋጋሚ ጨዋታዎችን ማድረግ፣ አድካሚ ጉዞዎችን ማድረግ እና የመሳሰሉት እኛን እንደ ቡድን ፈትኖን ነበር ። ከምንም በላይ ግን ለሴቶች እግር ኳስ አሁንም የሚሰጠው ትኩረት አሁንም ዝቅተኛ ነው፤ ይህ ደግሞ ብዙዎቻችንን ያስከፋናል፡፡ የሴቶች እግር ኳስ አሁን አሁን መነቃቃቶች እያየንበት እንገኛለን ነገር ግን ይህንን እድገት በሚገባ ማስቀጠል እያልቻልን እንደሆነ እየተሰማኝ፡፡”
ቀጣይ እቅድ
“በሚቀጥለው ዓመት እንደ ክለብ የምናቅደው ተፎካካሪ ለመሆን እንጂ ተሳታፊ ቡድን ላለመሆን ነው፡፡ ቡድኔ ብዙ ክፍተቶች አሉበት ፤ ብዙ ልናሻሽላቸው የምንፈልጋቸው ነገሮች አሉን። ያንን ደግሞ በሚገባ እናውቃለን። ስለዚህ በቀጣይ አመት በውድድሩ ላይ ለመሳተፍ ሳይሆን ለዋንጫ ተፎካካሪ ቡድን ይዞ ለመቅረብ እንጥራለን፡፡