ለታዳጊዎች እድል አይሰጥም ተብሎ በሚተቸው የጣሊያን እግርኳስ ከሌሎች ክለቦች በተሻለ ጠንካራ የታዳጊዎች የስልጠና ስርዓት የዘረጋው አታላንታ ነው፡፡ ትውልደ ኢትዮጵያዊያን ተጫዋቾች በሚገኙበት በዚህ ክለብ ውስጥ አዲስ አበባ የተወለደው እዮብ ዛምባታሮ ይጠቀሳል፡፡
የ19 ዓመቱ እዮብ እ.ኤ.አ. ነሃሴ 18 1998 ነበር አዲስ አበባ ላይ የተወለደው፡፡ በ2007 እዮብ መኖሪያቸውን ሞንዛ ባደረጉት የዛምባታሮ ቤተሰብ በጉዲፈቻ ተሰጥቶ ወደ ጣሊያን አመራ፡፡ “ለ6 ወራት ያህል በህፃናት ማሳደጊያ ውስጥ ቆይታ አድርጌ በጉዲፈቻ ለማደግ ወደ ጣሊያን ሄድኩ፡፡ እግርኳስን በተወለድኩበት አዲስ አበባ ብጀምርም በክለብ ታቅፌ መጫወት የቻልኩት ወደ ጣሊያን ከመጣሁ በኃላ ነው፡፡”
በችግሮች የታመሰው የልጅነት ህይወቱ እግርኳስ እንደአብዛኛው ኢትዮጵያው ታዳጊ በባዶ እግሩ በመጫወት ነበር የጀመረው፡፡ በቀኝ እና ግራ መስመር ተከላካይነት መጫወት የሚችለው እዮብ ወደ አታላንታ አካዳሚ ከመግባቱ በፊት በኦራቶሪዮ እና ሳን ፍሩቶሶ የታዳጊዎች ቡድኖች ውስጥ አሳልፏል፡፡ “በእግርኳስ ጉዞዬ መጀመሪያ ኦራቶሪዮ ነበር፡፡ ከግማሽ ዓመት የኦራቶሪዮ ቆይታ በኃላ ወደ አከባቢ የነበረ ቡድን (ሳን ፍሩቶሶ) አመራው፡፡ በዛም እስከ2009 ቆይታ አድርጌ የተለያዩ የሙከራ ግዜያትን በሞንዛ እና ኢንተር ሚላን ካሳለፍኩ በኃላ ወደ አታላንታ ከታናሽ ወንድሜ አክሊሉ ጋር ልመጣ ችያለው፡፡”
የእዮብ ውሳኔ ትክክለኛ ይመስላል፡፡ የቤርጋሞው ክለብ የዓለም ዋንጫ አሸናፊዎቹ ጌአታኖ ሲሬያ፣ አንቶኒዮ ካቢሪኒ፣ ዝነኛውን የቀድሞ የሚላን እና ዩቬንቱስ ግብ አዳኝ ፊሊፖ ኢንዛጊ፣ የአሁን ቦሎኛ አሰልጣኝ ሮቤርቶ ዶናዶኒ፣ ሪካሪዶ ሞንቶሊቮ፣ ዝነኛውን የአዙሪ እና ኢንተር ግብ አዳኝ ክሪስቲያን ቪየሪ፣ ጂያኮሞ ቦናቬንቱራ እና ሌሎችም የእግርኳስ ህይወታቸው ስኬታማ እንዲሆን ያነፀ ነው፡፡ እዮብ እስከ ነሃሴ 2017 በአታላንታ ቆይታ ካደረገ በኃላ የጨዋታ ልምድ ለማግኘት ወደ ሴሪ ሲ (ሶስተኛው የሊግ እርከን በጣሊያን) ፓዶቫ ካሊቺዮ በውሰጥ ተሰጥቶአል፡፡ በሁለት ዓመት የአታላንታ የወጣት ቡድን ቆይታው በ46 ጨዋታዎች ላይ ተሰልፎ አንድ ግብ ማስቆጠር ችሏል፡፡
“እውነት ለመናገር የመጀመሪያዎቹ ጨዋታዎች ላይ ትንሽ ደቂቃዎች ብቻ በመሰለፌ ክለቡን ለመልቀቅ እያሰብኩ ነበር፡፡ ከወኪሌ ጋር ሞክሬ ነበር ሆኖም በፓዶቫ ለመቆየት ወስኜ በመጨረሻም በጨዋታዎች ላይ ለመሰለፍ በቅቻለው፡፡”
ለፓዶቫ በውድድር ዓመቱ ላይ በተሰለፈባቸው ግጥሚያዎች ላይ በግራ መስመር መልካም እንቅስቃሴን በማሳየቱ የአሳዳጊው ክለብ አታላንታን ቀልበ መሳብ ችሏል፡፡ ከሁለት ሳምንት በፊት ፓዶቫ ሊቼን 1-0 በማሸነፍ የሴሪ ሲ ዋንጫን ሲያሸንፍ እዮብ ተቀይሮ በመግባት መጫወት ችሏል፡፡ አታላንታ ወጣት ቡድን በሚቀጥለው አመት ዳግም እዮብን ለማግኘት አጥብቆ ቢፈልግም የወጣቱ ተጫዋች ምርጫ ግን አሁንም በፓዶቫ ያለውን የውሰት ውል ማራዘም ነው፡፡ ፓዶቫ በ2018/19 የውድድር ዓመት በሴሪ ቢ የሚካፈል ሲሆን በ1996 ከወረደ በኃላ ወደ ዋናው ሊግ ሴሪ አ አድጎ አያውቅም፡፡
ከተወለደባት ኢትዮጵያ ጋር ያለውን የባህል ቁርኝነት የዘነጋ የማይመስለው እዮብ ባደገበት እና በተወለደበት ሃገራት መካከል ያለው ልዩነት ሰፊ እንደሆነ ያስረዳል፡፡ ልጅነቱን ወዳሳለፈባት ኢትዮጵያ ተመልሶ እርዳታ የማድረግ ህልሙን ገልጿል። “ሲበዛ ሰፊ ልዩነት አለ፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ሀብታምም ደሃም አልነበርኩም፡፡ የምበላው ነገር ቢያንስ ነበረኝ፡፡ እዚህ ነገሮች ይለያሉ የፈልግኩትን የማግኝበት እድል የሰፋ ነው፡፡ ለወደፊት ወደ ኢትዮጵያ ተመልሼ ለሌሎች አርዓያ ሆኜ የተወለድኩበትን ሃገር ብረዳ ደስተኛ እሆናለው፡፡”
የሪያል ማድሪድ እና ብራዚል ተጫዋች የሆነው ማርሴሎን እንደሚያደንቅ የሚናገረው እዮብ በጣሊያን የታዳጊዎች ማሰልጠኛ ውስጥ የተገኘ ብቸኛው ትውልደ ኢትዮጵያዊ ተጫዋች አይደለም፡፡ ከእሱ በተጨማሪ ታናሽ ወንድሙ እክሊሉ ዛምባታሮ እና ኢሳያስ ማቴሎ በአታላንታ፣ የቀድሞ የኢንተር ከ18 ዓመት በታች አምበል የአሁኑ የአራዜንቻ አማካይ መልካሙ መለስ ታውፍር፣ በሚላን ቆይታ ያደረገው አብርሃም ሚቲን እና ሰዒድ ቪሲን ከብዙ በጥቂቱ የሚጠቀሱ በጣልያን የሚገኙ ትውልደ ኢትዮጵያዊያን የእግርኳስ ተጫዋቾች ናቸው፡፡