ፊፋ የወሩ በሚያወጣው የካኮ ኮላ የዓለም የሃገራት ደረጃ ዛሬ ይፋ ሆኗል፡፡ በዚህው ደረጃ ላይ እየተንሸራተተች የምትገኘው ኢትዮጵያም ከዓለም 150 ደረጃዎች ውስጥ ካሉ ሃገራት መካከል ሳትሆን ቀርታለች፡፡
የወዳጅነት ጨዋታ እያደረገ የማይገኘው ብሄራዊ ቡድኑ በታህሳስ ወር ኬንያ አስተናግዳ ከነበረው የሴካፋ ሲኒየር ቻሌንጅ ዋንጫ የምድብ ጨዋታ በኃላ ዋልያዎቹ ያለአሰልጣኝ እና ጨዋታ ቆይተዋል፡፡ ባሳለፍነው ወር በ165 ነጥብ 146ኛ የነበረችው ኢትዮጵያ በአሁኑ ወር 151ኛ ለመቀመጥ ተገዳለች፡፡
ግንቦት 26 በተደረገው የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌደሬሽን ፕሬዝደንታዊ እና የስራ-አስፈፃሚ ምርጫ ተከትሎ ብሄራዊ ቡድኑ አዲስ አሰልጣኝ እንደሚቀጠርለት ይጠበቃል፡፡ የቀድሞ የፌደሬሽኑ ፕሬዝደንት አቶ ጁኒየዲ ባሻ ከዚህ ቀደም በእሳቸው አመራር ስር የነበረው ፌደሬሽን አሰልጣኝ ለመቅጠር እንቅስቃሴ ላይ ነው ቢሉም የተለየ ነገር ሳይታይ የስልጣን ዘመናቸው አብቅቷል፡፡
የዓለምን ደረጃ አሁንም ጀርመን የበላይነቷን ስታስጠብቅ የአፍሪካ ደግሞ ቱኒዚያ እየመራች ትገኛለች፡፡