ሪፖርት | መከላከያ ፋሲል ከተማን በሜዳው አሸንፏል

ከ25ኛው ሳምንት የሊጉ ጨዋታዎች መሀከል በቅድሚያ የተደረገው የጎንደሩ የ4፡00 ጨዋታ በመከላከያ 1-0 አሸናፊነት ተጠናቋል።

በጨዋታው መጀመሪያ የፋሲል ከተማ  ደጋፊዎች ፍፁም ገ/ማሪያም በውልዋሎ ዓ.ዩ አና መከላከያ ጨዋታ በተፈጠረው ግጭት ለፌደራል ዳኛ እያሱ ፈንቴ ከለላ በመስጠቱ ‘ስለሳየኸው ስፖርታዊ ጨዋነት ከጎንደር  ስፖርት ወዳድ ቤተሰብ የተበረከተ’ የሚል መልዕክት ያለው የራሱን ምስል የያዘ የፎቶ ፍሬም ከወጣት አቢዮት ጥላሁን እጅ ሽልማት ተበርክቶለታል ።

ፋሲል ከተማ ባለፈው ሳምንት ድሬዳዋን ሲገጥም ከነበረው  አሰላለፍ ኄኖክ ገምቴሳን  በሙሉቀን አቡሃይ ፣ ሰይድ ሁሴንን በፍፁም ከበደ እንዲሁም አብዱራህማን ሙባረክን በመሀመድ ናስር ተክቷል። በመከላከያዎች በኩል ደግሞ ከቅዱስ ጊዮዮርጊስ አቻ ከተለያየበት ጨዋታ በቀይ ካርድ በተሰናበቱት አዲሱ ተስፋዬ እና ዳዊት እስጢፋኖስ ምትክ ከቅጣት የተመለሰው ሽመልስ ተገኝ እና አማኑኤል ተሾመን በመጀመሪያ አሰላለፍ ውስጥ አስገብተው ጨዋታውን ጀምረዋል።

አፄዎቹ የመጀመሪያዎቹን 15 ደቂቃዎች የተሻለ የመሀል ሜዳ ብልጫ በመውሰድ ረጃጅም ኳሶችን ወደፊት መጣል ችለው የነበረ ቢሆንም ከጨዋታ ውጭ በሆኑ እንቅስቃሴዎች ምክንያት ጥረታቸው አልተሳካም። በ12ኛ ደቂቃ በቀኝ መስመር ፍፁም ከበደ ይዞት የገባውን ኳስ ለኤፍሬም አለሙ አቀብሎ ኤፍሬም ያደረገው ኢላማውን የጠበቀ ሙከራ ለባለሜዳዎቹ የመጀመሪያ የሚያስቆጭ አጋጣሚ ነበር። በ17ኛው ደቂቃ ፍሊፕ ዳውዝ ከአምሳሉ ጥላሁን በተላከለት ኳስ ከግብጠባቂ ጋር ተገናኝቶ ያልተጠቀመበት እና 20ኛው ደቂቃ ላይ መሀመድ ናስር  ከፍፁም ቅጣት ክልል ውጭ አክርሮ ሞክሮት ወደ ውጪ የወጣበት ኳስም ሌሎች ተጠቃሽ ሙከራዎች ነበሩ። ከዚህ ውጪ የመከላከያው ግብ ጠባቂ ይድነቃቸው ኪዳኔ የ34ኛ ደቂቃውን የሰንደይ ሙቱኩ የግንባር ኳስ እንዲሁም የ36ኛ ደቂቃ የፍሊፕ ዳውዝ ሌላ ሙከራ ማዳን ችሏል። ፍሊፕ 42ኛው ደቂቃ ላይ በጨዋታው ድንቅ እንቅስቃሴ ሲያሳይ የነበረው ኤፍሬም አለሙ የሻማው ኳስ በጭንቅላቱ ለመግጨት ተቃርቦ የነበረበትም ሂደት አደገኛ ይመስል ነበር።

በመከላከያዎች በመጀመሪያው አጋማሽ የጨዋታ ብልጫ ቢወስድባቸውም ኳስን ከኃላ መስርተው በመጀመር የተወሰደባቸውን ብልጫ ለማስመለስ  ጥረት ሲያደርጉ የነበረ ሲሆን አልፎ አልፎ በመልሶ ማጥቃት  ጥሩ ሙከራዎችንም አድርገዋል። በ4ኛው ደቂቃ ቴዎድሮስ ታፈሰ የሰንደይ ሙትኩን ስህተት  ተጠቅሞ ያገኝውን ኳስ ወደግብ ቢሞክርም ሚኬሌ ሳማኬ በቀላሉ አድኖበታል። ቡድኑ በ17ኛው ደቂቃ በፈጠረው አጋጣሚ ደግሞ ፍፁም ከበደ ወደ ውጭ ሊወጣ ያለን ኳስ በሚያቆምበት ወቅት ፍፁም ገ/ማርያም ተቀብሎ ወደግብ ሲሞክር ወደ ውጭ የወጣበት አኳኃን ለመከላከያ የሚያስቆጭ ነበር። በ23ኛ ደቂቃ ደግሞ ከፍፁም ገ/ማርያም የተላከለትን ኳስ ቴውድሮስ  ታፈሰ አክርሮ ወዱ ግብ ቢልክም በግብጠባቂው ድኖበታል።

በእረፍት ሰዐት ላይ በፋሲል ከተማ ክለብ አመራሮች ላይ ጠንከር ያለ ተቃውሞ ታይቷል። ደጋፊዎች ”ክለቡን የሚመጥን ስራ አስኪያጅ ያስፈልገናል ” የሚል መፈክር ይዘው ስታድየሙን በመዞር የጀመሩት ተቃውሞ ለውጥ ማይታይ ከሆነ ተቃውሞው እንደሚቀጥል ጠንከር ያለ መልእክትንም ጭምር ያስተላለፉበት ነበር።

ማራኪ ወርቁን እና አማኑኤል ተሾመን በምንይሉ ወንድሙ እና ሳሙኤል ሳሊሶ በመተካት ወደ ሜዳ የተመለሱት መከላከያዎች እንደመጀመሪያው አጋማሽ ጨዋታው አልከበዳቸውም። በባለሜዳዎቹ ተጨነው መጫወት በቀጠሉበት ሁለተኛ ረጋማሽ 48ኛ ደቂቃ ከግራ ጠርዝ ኳስ ይዞ በገባው ኤፍሬም አማካይነት ኢላማውን የጠበቀ ሙከራ ሲያደርጉ 66ኛው ደቂቃ ላይ ደግሞ አብዱራህማን ሙባረክ  ከፍሊፕ ዳውዝ የተላከለትን ኳስ አምክኗል። ከመከላከያ በኩል በ53ኛው ደቂቃ  ከፍፁም የተሠጠውን ኳስ ሳሙኤል ሳሊሶ ሳይጠቀምበት ሲቀር ፍፁም ገ/ማርያም በ60ኛ ደቂቃ ላይ በቀኝ መስመር ይዞ ገብቶ የሞከረው ኳስ በጥሩነቱ የሚነሳ ነበር። ሆኖም ጦሩ ጨዋታውን ያሸነፈበት ጎል ያገኘው 80ኛው ደቂቃ ላይ ነበር። ፋሲሎች ኤፍሬም አለሙ ላይ ጥፋት ተሰርቷል ብለው በተዘነናጉበት ሰዓት በመልሶ ማጥቃት ከሳሙኤል ሳሊሶ የተሻገረለትን ኳስ ምንይሉ ወንድሙ በቀኝ የፍፁም ቅጣት ምት ክልል ይዞ በመግባት ወደግራ በመሬት አክርሮ የመታው ኳስ ከሳማኬ መረብ ላይ አርፏል።

መከላከያ ከጎሉ በኃለ ውጤቱን ለማስጠበቅ ሲከላከል  ፋሲል ከተማ ይበልጥ ተጭኖ በማጥቃት ተጫውቷል።  የመሀመድ ናስር  የ90ኛ እና 93ኛ ደቂቃ ሙከራዎች በዚህ ረገድ ተጠቃሽ ነበሩ። ሆኖም የጦሩ ግብ ጠባቂ ይድነቃቸው ኪዳኔ ድንቅ በቃቱን በማሳየት የቡድኑን መሪነት አስጠብቆ ወጥቷል። በሜዳቸው ባደረጓችው ሁለት ተከታታይ ጨዋታዎች ላይ አንድ ነጥብ ማግኘት የቻሉት አፄዎቹ በ34 ነጥብ 8ኛ ደረጃ ላይ ሲቀመጡ  መከላከያ በ32 ነጥብ ወደ 10ኛነት መምጣት ችሏል።

በጨዋታዉ ፍፃሜ የፋሲል ከተማው ምክትል አምበል የከድር ኸይረዲን ”የተቆጠረብን ግብ አግባብ  አይደለም  ጥፋት ተፈፅሞ ስለነበር ጨዋታ መቆም ነበረበት” የሚል ክስ አስመዝግቧል ።

አሰልጣኞች አስተያየት

አሰልጣኝ መሳይ ተፈሪ – ፋሲል ከተማ

ለማሸነፍ ጥረት አድርገን ብዙ የጎል አጋጣሚውችንም መፍጠር ችለን ነበር።  ያው እንዳሰብነው አልሆነም። ጨዋታውን ተቆጣጥረናል ፤ ግብ ማስቆጠር ነው ያልቻልነው። ያሉብንን ችግሮች ወደፊት እናስተካክላለን ። በመከላከያ በኩል  ከእረፍት በኃላ አጥቂዎችን በማስገባት የማጥቃት መከራ አድርገዋል። ያው እግር ኳስ በመሆኑ አንድ ግብ ተቆጥሮብን ያሰብነውን ሳናሳካ ወጥተናል።

አሰልጣኝ ስዩም ከበደ – መከላከያ

ጨዋታው ጥሩ ነበር ከሜዳው ውጭ ነጥብ ማግኝትታችን ከወራጅ ቀጣና ተስፈንጥረን እንድንወጣ ረድቶናል ። የነበረው ፉክክር በጣም ደስ ይል ነበር። በፋሲል በኩል ጥሩ ጥሩ አጋጣሚዎች ተፈጥረዋል ፤ በተለይ በመጀመሪያ አጋማሽ ድነቃቸው ያዳናቸው ኳሶች አሸንፈን እንድንወጣ አድርገውናል። ዛሬ በጣም ጥሩ አቋም ላይ ነበር። ተጨዋቾቼ ጥሩ መነቃቃት እና ሞራል ላይ ስለነበሩም መጨረሻ ላይ ያገኝነውን ዕድል ተጠቅመንበታል።