በታሂ ሊግ 1 ለሚወዳደረው ቻይናት ሆርንቢል ለመጫወት የሙከራ ግዜ እያሳለፈ የሚገኘው ሚኪያስ ግርማ ዛሬ የመጨረሻውን ልምምድ ከክለቡ ጋር እንደሚያደርግ ይጠበቃል፡፡ የባህርዳር ከተማ ተጫዋች የሆነው ሚኪያስ እስካሁን በቆየባቸው ግዜያቶች ላይ ጀርመናዊውን የቻይናት አሰልጣኝ ቀልብ መግዛቱን ተነግሯል፡፡
ሚኪያስ ከክለቡ ጋር በውል ጉዳይ ከስምምነት ባለመድረሱ ወደ ኢትዮጵያ ይመለሳል የሚሉ ሃሳቦች ትክክል አለመሆናቸውን የተጫዋቹ ወኪል ስቲቨን ሄኒንግ ለሶከር ኢትዮጵያ በአስተያየቱ ጠቁሟል፡፡ “የሙከራ ግዜው በመልካም ሁኔታ ነው ያለፈው፡፡ ዛሬ ነው የሚጠናቀቀው፡፡ የክለቡ አሰልጣኝ የሚኪያስ ለእግርኳስ ያለውን ጥልቅ ስሜት በደንብ ተረድቷል ያለውን አቅምም አይቷል፡፡ ቻይናት ሊያስፈርመው ይፈልጋል ነገር ግን የውጪ ሃገራት የተጫዋቾች ኮታቸው አሁን ላይ ሙሉ ነው እና አንድ ተጫዋች እስኪለቁ የውል ስምምነት ሊኖረን አይችልም፡፡”
ሄኒንግ ሲቀጥል እስከፈረንጆቹ ሰኔ 30 በሚቆየው የዝውውር መስኮት ላይ ቻይናንት አንድ የውጪ ሃገር ተጫዋች በውሰት ከለቀቀ ሚኪያስ ከሐምሌ ወር ጀምሮ በታሂ ሊግ የመጫወት እድል እንደሚኖረው ገልጿል፡፡ “ሚኪያስ በክለቡ ቦታ እንዲኖረው በውሰት አንድ ተጫዋች መልቀቅ አለባቸው፡፡ ይህንንም እንደሚደርጉ ተስፋ አለኝ፡፡ ይህ እስኪሆን ድረስ ሚኪያስ ወደ ኢትዮጵያ ተመልሶ ከባህርዳር ጋር የውድድር ዓመቱን ይጨርሳል፡፡”
ሚኪያስ ወደ በባህርዳር ከተማ መልካም ግዜያትን ሲያሳልፍ የቆየ ሲሆን ከተፈጥሯዊ የአማካይ ስፍራው ይልቅ በመስመር ተከላካይነት በክለቡ በመጫወት ይታወቃል፡፡ ወደ ፕሪምየር ሊጉ ለማደግ ግስጋሴያቸውን የቀጠሉት የጣናው ሞገዶች የሊግ ጨዋታዎች ባልተጠናቀቁበት ሁኔታ ላይ የተጨዋቹን ወደ ታይላንድ መሄድ አልተስማሙበትም፡፡ በዚህም የተነሳ ወደ ክለቡ በአፋጣኝ እንደሚለስ በደብዳቤ መጠየቃቸው ይታወቃል፡፡
ፈረንሳዊው የቻምፒየንስ ሊግ አሸናፊ የቀድሞ የሊቨርፑል እና አትሌቲኮ ማድሪድ አጥቂ ፍሎሮ ሲናማ ፖንጎ (ከታች በፎቶ ላይ አብረው ይታያሉ) እየተጫወተ የሚገኝበት ቻይናት በ2017 ወደ ዋናው የታይላንድ ሊግ 1 ማደግ የቻለ ሲሆን በውድድር ዘመኑ 18 ክለቦች በሚተፉበት የቶዮታ ታሂ ሊግ በ21 ነጥብ 13ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል፡፡