ብሄራዊ ሊጉ በድሬዳዋ ከነማ የበላይነት ተጠናቋል

የኢትዮጵያ ብሄራዊ ሊግ በደማቅ ሁኔታ ዛሬ ፍፃሜውን አግኝቷል፡፡ በ9፡00 በድሬዳዋ ስታድየም በተደረገው የፍፃሜ ጨዋታም ድሬዳዋ ከነማ ሆሳእና ከነማን 3-1 አሸንፎ የ2007 የውድድር ዘመን የኢትዮጵያ ብሄራዊ ሊግ ዋንጫ ባለቤት ሆኗል፡፡

ፍቃዱ ወርቁ ባስቆጠረው ግብ ድሬዳዋ ከነማ 1-0 እየመራ የመጀመርያው አጋማሽ ሊጠናቀቅ ጥቂት ሴኮንዶች ሲቀሩ ዱላ ሙላቱ ለሆሳእና ግብ አስቆጥሮ የመጀመርያው አጋማሽ 1-1 በሆነ አቻ ውጤት ተጠናቋል፡፡ ከእረፍት መልስ በ57ኛው ደቂቃ የሆሳእናው ተከላካይ ንጋቱ ዳሬ በራሱ ላይ ባስቆጠረው ግብ ድሬ 2-1 መምራት ሲችል የውድድሩ እና የጨዋታው ኮከብ ተብሎ የተመረጠው ይሆኔ እንዳሻው የማሳረግያዋን ግብ አስቆጥሯል፡፡ ድሬዳዋ ከነማም 3-1 በሆነ ውጤት አሸንፎ የውድድሩ ቻምፒዮን ሲሆን ወደ ፕሪሚር ሊጉም በድል ተሸጋግሯል፡፡

ከጨዋታው በኋላ አስተያየታቸውን የሰጡት የድሬዳዋ ከነማዋ አሰልጣኝ መሰረት ማኒ በከፍተኛ ደስታ ስሜት ውስጥ ሆነው ድሉን ለከተማው ህዝብ መታሰብያ አበርክተዋል፡፡

‹‹ በመጀመርያ ይህንን ስራ አምነውብኝ ለሰጡኝ ለከተማው ስፖርት ኮሚሽን እና ክለቡ ከፍተኛ ምስጋና ማቅረብ እፈልጋለሁ፡፡ ይህ ዋንጫ ለከተማው ህዝብ መታሰብያ ይሰጥልኝ፡፡ ለሚቀጥለው አመት ከወዲሁ ጠንክረን ተዘጋጅተን ወደመጣንበት ላለመመለስ ከፍተኛ ስራ እንሰራለን፡፡ ›› ብለዋል፡፡ ይርሳቸው ኮከብ ተጫዋች ማን እንደነበር የተጠየቁት መሰረት ሁሉም ተጫዋቾቼ ኮብ ነበሩ ብለዋል፡፡ ‹‹ ሁሉም ተጫዋቾቼ ምርጦች ነበሩ፡፡ ወደ ፕሪሚየር ሊግ ለማለፍ መስዋእትነትን ከፍለዋል፡፡ የምሰጣቸውን ትእዛዝም በሚገባ ሲተገብሩ ነበር፡፡ ›› ብለዋል፡፡ ‹‹ በብሄራዊ ሊጉ ዋንጫ ያነሳች የመጀመርያ ሴት በመሆኔ ደስታ ይሰማኛል፡፡ የዚህ ስኬቴ ምስጢር በራስ መተማመኔ እና ለስራዬ ያለኝ ክብር ነው፡፡ ›› ሲሉም አጠቃለዋል፡፡

የሆሳዕና ከነማው አሰልጣኝ ግርማ ታደሰ በበኩላቸው ለድሬዳዋ ህዝብ ምስጋናና እና የእንኳን ደስ አላችሁ ንግግር አድርገዋል፡፡

‹‹ በ20 ቀናት ውስጥ ያደረግናቸው 7 ጨዋታዎች አቅማችንን እንድንጨርስ አድርጎናል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ዋና አላማችን የነበረው ሆሳዕናን ወደ ፕረሚየር ሊጉ ማሳደግ ነበር፡፡ ወደ ፕሪሚር ሊጉ በማደጋችን የተደሰተውን ደጋፊ በዋንጫ የበለጠ ለማስደሰት ያልቻልነው ዛሬ ድሬዋች በጣም ጥሩዎች በመሆናቸው ምክንያት ነው፡፡ ለድሬዳዋ ከተማ ህዝብ እና ለክለቡ እንኳን ደስ አላችሁ ማለት እፈልጋለሁ፡፡ የከተማው ህዝብ ‹‹ የብሄራዊ ሊጉ ባርሴሎና›› እስከማለት የደረሰ ድንቅ ድጋፍ አድርገውልናል፡፡ የነሱ ማበረታቻ ምን ያህል ጥሩ እግርኳስ እንደምንጫወት ማሳያ ነበር፡፡ የድሬዳዋ ህዝብ ለሰጡን ማበረታቻ ከፍተኛ ምስጋና እናቀርባለን፡፡ ››

ከጨዋታው ፍፃሜ በኋላ የእለቱ የክብር እንግዶች ለኮከቦች ሽልማት የሰጡ ሲሆን የሽልማት ስነስርአቱ በጣለው ዝናብ ምክንያት መጠነኛ መስተጓጎል አጋጥሞታል፡፡

ሽልማቶች

1ኛ- ድሬዳዋ ከነማ – 50 ሺህ ብር ፣ ወርቅ ሜዳልያ እና ዋንጫ

2ኛ- ሆሳዕና ከነማ -20 ሺህ ብር እና ብር ሜዳልያ

3ኛ – ሃላባ ከነማ- 10 ሺህ ብር እና ነሃስ ሜዳልያ

all stars

የውድድሩ ኮከቦች (ሁሉም ዋንጫ ተሸልመዋል)

ኮከብ ተጫዋች – ይሁኔ እንዳሻው (ድሬዳዋ ከነማ)

ኮከብ ግብ አግቢ – በላይ አባይነህ (ድሬዳዋ ከነማ) – 6 ግብ

ኮከብ ግብ ጠባቂ – ተ/ማርያም ሻንቆ (ሃላባ ከነማ)

ኮከብ አሰልጣኝ – መሰረት ማኒ (ድሬዳዋ ከነማ)

ኮከብ ዳኛ – ጌቱ ተፈራ 6ሺህ ብር ሽልማት

ኮከብ ረዳት ዳኛ – አስቻለው ወርቁ 5ሺህ ብር ሽልማት

የፀባይ ዋንጫ – ሼር ኢትዮጵያ ሆነው ተመርጠው የተዘጋጀላቸውን የዋንጫ እና የገንዘብ ሽልማት ተቀብለዋል፡፡

የውድድሩ አሸናፊ ድሬዳዋ ከነማ እና ሁለተኛው ሆሳዕና ከነማ ወደ ፕሪሚየር ሊጉ ሲያልፉ ጅማ አባ ቡናን በመለያ ምቶች 4-2 ያሸነፈው ሃላባ ከነማ በ3ኝነት ውድድሩን አጠናቋል፡፡

ከዚህ የውድድር ዘመን በኋላ ብሄራዊ ሊግ የሚለው ስያሜ በሊግ እርከን 3ኛ ደረጃ ላይ የሚገኝ ሊግ ስያሜ ይሆናል፡፡ ከፕሪሚር ሊጉ ቀጥሎ በሚገኘው ሊግ 32 ክለቦች የሚሳተፉበት ሱፐር ሊግ ሲኖር ከሱፐር ሊጉ ቀጥሎ በበርካታ ዞኖች የሚከፈል የብሄራዊ ሊግ ውድድር ይኖራል፡፡

ያጋሩ