ከ20 ዓመት በታች ፕሪምየር ሊግ ጨዋታ በኮሚሽነር መቅረት ምክንያት ተስተጓጉሏል

በኢትዮጵያ ከ20 ዓመት በታች ፕሪምየር ሊግ 13ኛ ሳምንት የምድብ ለ ዛሬ ከሚካሄዱ ጨዋታዎች መካከል ቦሌ በሚገኘው የቅዱስ ጊዮርጊስ የልምምድ ሜዳ ላይ ቅዱስ ጊዮርጊስ ከ አዲስ አበባ ከተማ በ05:00 እንደሚጫወቱ ቢጠበቅም ኮሚሽነሩ በመቅረቱ ምክንያት ሳይከናወን ቀርቷል።

ለጨዋታው ሁለቱም ቡድኖች ፣ የዕለቱ አራት ዳኞች ፣ ጨዋታውንም ለመከታተል ቀላል የማይባሉ ደጋፊዎች ቦታው በመታደም የጨዋታውን መጀመር እየተጠባበቁ ባለበት ሰዓት የጨዋታው ኮሚሽነር ሆነው የተመደቡት አቶ ወንድሙ ኃይሌ ቦታው ላይ ባለመገኘታቸው ምክንያት የጨዋታው ዳኞች የሁለቱም ቡድኖች የቡድን መሪዎች ጋር ተነጋግረው ቃለ ጉባኤ በመያዝ ከተፈራረሙ በኋላ ጨዋታው ሳይደረግ መሰረዙ አስገራሚ ሆኖል። ኮሚሽነሩም ” ስለመመደቤ የማውቀው ምንም ነገር የለም። አሁን የምገኘው ዲላ ከተማ ውስጥ ነው፤ ከዚህም አልተነሳውም። ” የሚል ምላሽ ሰጥተዋል።

 

ስለተፈጠረው ስህተት ምላሽ እንዲሰጡን በሊግ ኮሚቴ ከ17 እና 20 አመት በታችን በበላይነት የሚመሩት ፌ/ረዳት ዳኛ ዳንኤል ዘለቀ ለማናገር ያደረግነው ጥረት ስልካቸው ዝግ በመሆኑ ማግኘት ያልቻልን ሲሆን በኋላ ላይ ቡድኖቹ ቃለ ጉባኤ ይዘው ከተበተኑ በኋላ ለሁለቱም ቡድን አመራሮች ስልክ በመደወል ጨዋታውን ተመልሳችሁ መጫወት አለባችሁ ማለታቸውን ሰምተናል። የሊግ ኮሚቴ የውድድሮች ከፍተኛ ባለሙያ አቶ ከበደም ይህን እንደማያውቁ ገልፀውልን ጨዋታው እንዲደረግ ያደረጉት ጥረት ቡድኖቹ የተበተኑ በመሆኑ ሳይሳካ ቀርቷል።

ከ17 እና 20 ዓመት በታች የኢትዮዽያ ፕሪምየር ሊጎች በዚህ መልኩ ትኩረት ሳይሰጠው እየቀረ ውድድሮች የሚሰረዙበት፣ ከታሰበበት ሰዓት ዘግይተው የሚጀመሩበት እና ሌሎች ችግሮችም በተደጋጋሚ እየተከሰቱበት ይገኛል። በቀጣይ ፌዴሬሽኑ ለዚህ ውድድር በቂ ትኩረት በመስጠት ውድድሮቹ በወጣላቸው መርሃ ግብር መሰረት እንዲካሄድ ጥንቃቄ እንዲደረግ መልዕክታችን ነው።