ፕሪምየር ሊግ | የ26ኛ ሳምንት ጨዋታዎች ቅድመ ዳሰሳ – ክፍል 1

26ኛው ሳምንት ላይ የደረሰው የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ነገ ከሚያስተናግዳቸው ስድስት ጨዋታዎች መሀከል ሶስቱ አዲስ አበባ ላይ ይደረጋሉ። የዛሬው ክፍል አንድ ቅድመ ጨዋታ ዳሰሳችንም ትኩረት የሚሆኑት እንዚህ ጨዋታዎች ናቸው። 

መቐለ ከተማ ከ ፋሲል ከተማ

በ25ኛው ሳምንት የተመሳሳይ 1-0 ሽንፈት የደረሰባቸው ሁለቱ ክለቦች አሁን ደግሞ በገለልተኛው አዲስ አበባ ስታድየም ነገ ረፋድ 4፡00 ሰዐት ላይ ይገናኛሉ። ወደ ድሬዳዋ አቅንቶ ያለውጤት የተመለሰው መቐለ ከተማ ሊጉን መምራት የሚችልበትን ዕድል አበላሽቷል። ከዚህ ጨዋታ ውጤት ካላገኘ ደግሞ መሪ ከሚሆነው ቡድን በሶስት ነጥብ ሊርቅ ይችላል። በመሆኑም ጨዋታው ከፋሲል ከተማም በላይ እስካሁን ሁለት ተከታታይ ሽንፈቶች ላልገጠሙት መቐለ ከተማ አስፈላጊው ይሆናል። ከመልካም የሁለተኛ ዙር አጀማመር በኃላ በውጤት ማጣት ውስጥ የሚገኙት አፄዎቹ ደግሞ በደረጃ ሰንጠረዡ ባላቸው ቦታ ላይ ከፍ ያለ ልዩነት ለመፍጠር የረፈደባቸው ቢሆንም ካሸነፉም ሆነ ግብ ካስቆጠሩ ሁለት ወራት ሊሆናቸው መቃረቡ ጨዋታውን በትኩረት እንዲያደርጉ ያስገድዳቸዋል።

መቐለ ከተማዎች ጉዳት ላይ ከሚገኘው አጥቂያቸው ቢስማርክ ኦፖንግ ውጪ ሙሉ ስብስባቸው ለነገው ጨዋታ ዝግጁ ነው። በፋሲል ከተማ በኩል ግን የግራ መስመር ተከላካዩ አምሳሉ ጥላሁን እና እስከ ውድድር ዘመን አመቱ መጨረሻ በጉዳት የሚቆየው አይናለም ኃይለ የማይኖሩ ቢሆንም ወሳኙ ተከላካይ  ያሬድ ባየህ ግን ከረጅም ጊዜ ጉዳት በኃላ ለነገው ጨዋታ የሚደርስ ይሆናል።

አሰልጣኝ ዮሀንስ ሳህለ ከድሬዳዋው ሽንፈት በኃላ በሰጡት አስተያየት የቡድናቸው የጨዋታ ተነሳሽነት ደክሞ መታዩትን አንስተው ነበር። በጨዋታው የተቆጠረበትም ግብ የቡድኑን የመከላከል ጥንካሬ ጥያቄ ውስጥ የከተተ ነበር። በመሆኑም በነገው ጨዋታ ቡድኑ በነዚህ ነጥቦች ላይ መሻሻልን አሳይቶ መገኘት ይጠበቅበታል። ከዚህ በተጨማሪም ጨዋታው ሁለት የመከላከል ባህሪ ያላቸው አማካዮችን ከሚጠቀም ቡድን ጋር የሚደረግ በመሆኑ መሀል ሜዳ ላይ በሚኖረው ፍልሚያ ተመሳሳይ ቅርፅ ካለው የመቐለ የአማካይ ክፍል በተለይ የሚካኤል ደስታ የማጥቃት ተሳትፎው አስፈላጊ ይሆናል። ዋነኛ የማጥቃት ሀላፊነት የሚጣልባቸው የፊተኞቹ አራት ተጨዋቾችም በተለይ በሁለቱ መስመሮች በኩል የሚሰነዝሩት ጥቃት ወሳኝነት ይኖረዋል።

በፋሲል ከተማ በኩል ደግሞ ከመከላከያ ሽንፈት በኃላ በአሰልጣኝ መሳይ ተፈሪ እንደተገለፀውም ቡድኑ በግብ ፊት የሚታይበት የአጨራረስ ችግር ከውጤት እንዲርቅ ምክንያት ሲሆነው ይታያል። በነገው ጨዋታ ይህን ችግር መቅረፍ የአፄዎቹ ዋነኛ ትኩረትም እንደሚሆን ይታሰባል። ተጋጣሚያቸው በመከላከል ወቅት በቁጥር ተበራክቶ በራሱ ሜዳ ላይ የሚገኝ እንደመሆኑ መጠን ደግሞ የመጨረሻ የግብ ዕድልምችን መፍጠርም ቀላል ላይህምንላቸው ይችላል። ወደ ማጥቃት በሚደረግ ሽግግር ውስጥም በመስመሮች በኩል ወደ ተጋጣሚው የግብ ክልል መድረስን ምርጫው የሚያደርገው ፋሲል በዚህ ሂደት ላይ ፍጥነትን መጨመር እና ተጋጣሚው የመከላከል ቅርፁን ከመያዙ በፊት በሶስተኛው የሜዳ ክፍል ላይ መገኘት መቻል ግዴታው ይሆናል።

የእርስ በእርስ ግንኙነት እና እውነታዎች

– በ11ኛው ሳምንት በዚሁ በአዲስ አበባ ስታድየም የተገናኙበት የክለቦቹ የመጀመሪያ ግንኙነት ያለግብ የተጠናቀቀ ነበር።

– መቐለ ከተማ እስካሁን በገለልተኛው አዲስ አበባ ስታድየም ካደረጋቸው ሶስት ጨዋታዎች ላይ አንድ ግብ አስቆጥሮ አምስት ነጥቦችን ሲያሳካ ሁለቱ ጨዋታዎችን ያለግብ ጨርሶ ነበር ነጥብ የተጋራው።

– ፋሲል ከተማ በበኩሉ በገለልተኛ ሜዳ ባደረጋቸው ሁለቱ የአዲስ አበባ ጨዋታዎች አንዴ አሸንፎ አንዴ ደግሞ ያለግብ በመለያየት ነጥብ ተጋርቷል።

– ፋሲል ከተማ ከመጨረሻዎቹ አምስት ጨዋታዎቹ ሁለት ነጥብ ብቻ ሲያገኝ እንድም ጊዜ ግብ አላስቆጠረም።

ዳኛ

– ፌደራል ዳኛ ተካልኝ ለማ ጨዋታውን በመሀል ዳኝነት ለመምራት ኃላፊነት ተሰጥቶታል።


ኢትዮ ኤሌክትሪክ ከ ሀዋሳ ከተማ

አምና ሀዋሳ ላይ የተደረገው እና ለብዙ ውዝግቦች መነሻ የነበረው የሁለቱ ቡድኖች የሁለተኛ ዙር ግንኙነት ዘንድሮ አዲስ አበባ ላይ ይደረጋል። በሊጉ ወገብ ላይ ሆኖ በርካታ ሳምንታትን ያሳለፈው ሀዋሳ ከሰበሰበው ነጥብ አንፃር በሊጉ የተደላደለ ይመስላል። መጠነኛ መሻሻል እያሳየ የነበረው ኢትዮ ኤሌክትሪክ አዳማ ላይ የደረሰበት የ 6-1 ሽንፈት እጅግ አሸማቃቂ ነው። የአምስት ጎሎች ልዩነቱም የኤሌክትሪክን የግብ ዕዳ ወደ 20 ከፍ አድርጎታል። ቡድኑ ጥሩ ውጤት እያስመዘገቡ ካሉት ተፎካካሪዎቹ ዝቅ ብሎ እንዲሁም ከሊጉ ግርጌ በአንድ ደረጃ ብቻ ከፍ ብሎ መቀመጡም የነገው የሀዋሳ ጨዋታ ላይ የሞት ሽረት ትግል እንዲያደርግ የሚያስገድደው ይሆናል። ከዋንጫ ፉክክሩ የራቀ መሆኑ ይህ ጨዋታ በቡድኑ የውድድር አመት ላይ ብዙ ልዩነት የሚፈጥር ባይመስልም ከሜዳው ውጪ ሶስት ነጥብ አሳክቶ ለማያውቀው ሀዋሳ ሌላ ዕድል እንደሚሆን ይታሰባል።

ኤሌክትሪክ ተከላካዩ ተስፋዬ መላኩን እና ግብ ጠባቂው ዮሀንስ በዛብህን በ5 ቢጫ ካርድ ምክንያት የማያሰልፍ ሲሆን አዳማ ላይ ጉዳት የገጠመው ሱሊማን አቡ መሰለፍም አጠራጣሪ ሆኗል። በርካታ ተጨዋቾቹን በጉዳት በሚያጣው ሀዋሳ ከተማ በኩል እስከ ውድድር ዘመኑ መጨረሻው የማይኖረው አዲስ አለም ተስፋዬን ጨምሮ  አምበሉን ደስታ ዮሀንስ ፣ ዳንኤል ደርቤ እና ዮሀንስ ሴጌቦ እንዲሁም አጥቂው ቸርነት አውሽ ጉዳት ላይ ይገኛሉ። በሲዳማ ቡናው ጨዋታ ቀይ ካርድ የተመለከተው  ግብ ጠባቂው  ሱሆሆ ሜንሳ እና 5 ቢጫ ካርዶች ያሉበት ጅብሪል አህመድ ደግሞ ቅጣት ላይ ይሚገኙ ተጨዋቾች ናቸው። በሌላ በኩል ግብ ጠባቂው ተክለማርያም ሻንቆ ከጉዳት መልሱ ለሀይቆቹ ጥሩ ዜና ሆኗል።

በኢትዮ ኤሌክትሪክ ተጨዋቾች ላይ ይታይ የነበረው ተነሳሽነት ከፍ ማለት ከአዳማው ጨዋታ በፊት ቡድኑ በሜዳ ላይ እስከመጨረሻው ደቂቃ ድረስ የመታገልን መልክ ሰጥቶት ነበር። በእንቅስቃሴ ረገድ እንዲሻሻልም ምክንያት የሆነው ይህ ነበር። በመሆኑም ነገ በአዳማው ጨዋታ ሙሉ ለሙሉ ያጣውን ይህን ጥንካሬውን መልሶ ማግኘት ይጠበቅበታል። በ4-2-3-1 ከተከላካይ ፊት ከሚጣመሩት ሁለቱ ተጨዋቾች መሀል አዲስ ነጋሽ ወደ ፊት ተጠግቶ ማጥቃቱን ማገዝ እንዲሁም የጨዋታ አቀጣጣይነት ሚና ያለው ካሉሻ አልሀሰን በተሻለ ነፃነት ከመስመር አማካይምቹ ጋር በቀላሉ ሊገናኝ የሚችልበትን ሁኔታ መፍጠርም ቡድኑን የተሻለ ጥቃት ለመሰንዘር ዕድል ይሰጠዋል። የተጋጣሚው የመስመር ተከላካዮች የማጥቃት ተሳትፎም ዲዲዬ ለብሪን ለያዘው ኤሌክትሪክ የመስመር ጥቃት የሚኖረው እገዛ የጎላ ይሆናል።

በኳስ ቁጥጥር የበላይነት ላይ ለሚያተኩረው እና የተሳኩ ቅብብሎችን ማድረግ በተጋጣሚው ላይ ብልጫን እንዲወስድ አስፈላጊው የሆኑት ሀዋሳ ከተማ የሜዳው ሁኔታ ይበልጥ ሊጎዳው እንደሚችል መናገር ይቻላል። ኢትዮ ኤሌክትሪክ ከተከላካይ መስመሩ ፊት ኄኖክ ካሳሁንን እና አዲስ ነጋሽን የሚያጣምር በመሆኑም የሀዋሳ አማካዬች መሀል ለመሀል ጥቃት ለመሰንዘር የሚሞክሩበትን ሂደት ቀላል ላያደርገው ይችላል። ይህም ቡድኑ የመስመር አጥቂዎቹን እገዛ በእጅጉ እንዲያገኝ ያስገድዳል። ተደጋጋሚ ስህተት ሲሰራ ከሚታየው የኤሌክትሪክ የኃላ ክፍል ጀርባ ለመገኘት በአንድ ለአንድ አጋጣሚዎች ወቅት የተሻለ ሆኖ መገኘት እና ከኳስ ውጪም ጫናን ማሳደር መቻል ከሀይቆቹ የፊት መስመር ተጨዋቾች የሚጠበቅ ይሆናል።

የእርስ በእርስ ግንኙነት እና እውነታዎች

– የነገው ጨዋታ ሊጉ በአዲስ መልክ ከተጀመረ ወዲህ 40ኛ ግንኙነታቸው ይሆናል። ባለፉት 39 ግንኙነቶች ኤሌክትሪክ 16 ሲያሸንፍ ሀዋሳ 13 አሸንፏል። 10 ጨዋታዎች ደግሞ በአቻ ውጤት ተጠናቀዋል።
– አዲስ አበባ ላይ ባደረጓቸው 20 ጨዋታዎች ኤሌክትሪክ 12 ሲያሸንፍ ሀዋሳ ከተማ 5 ጨዋታ አሸንፏል። በ3 አጋጣሚዎች ደግሞ አቻ ተለያይተዋል።
– በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የእርስ በእርሰ ግንኙነቶች ታሪክ ከፍተኛ ጎል የተቆጠረበት እና 100 ጎሎችን የተሻገረ የመጀመርያው ግንኙነት ነው። በ39 ጨዋታዎች 105 ጎሎች ሲቆጠሩ ኤሌክትሪክ 60 ፣ ሀዋሳ 45 ጎሎችን አስቆጥረዋል።
– ባለፉት 7 ተከታታይ የአዲስ አበባ ስታድየም ጨዋታዎች ሁሉንም ኢትዮ ኤሌክትሪክ አሸንፏል። በተለይ በ2007 የውድድር ዓመት 6-0 ያሸነፈበት ከፍተኛው ነው።

– በሁለተኛው ዙር ኢትዮ ኤሌክትሪክ በሶስት አጋጣሚዎች የክልል ቡድኖችን ሲያስተናግድ ያለሽንፈት 7 ነጥቦችን ሰብስቧል። በዚሁ ሁለተኛ ዙር ሀዋሳ አራት ጊዜ ከሜዳው ሲወጣ አንድ ሽንፈት ገጥሞት ሶስት ጊዜ ደግሞ በተመሳሳይ 1-1 ውጤት ነጥብ ተጋርቷል።

ዳኛ

– ይህን ጨዋታ በመሀል ዳኝነት የሚመራው ፌደራል ዳኛ ኢብራሂም አጋዥ ነው።


ቅዱስ ጊዮርጊስ ከ ወልዲያ

የነገው የመጨረሻ ጨዋታ በደረጃ ሰንጠረዡ ላይ እና ታች ባሉት ፉክክሮች ውስጥ ተሳታፊ የሆኑት ሁለቱን ቡድኖች የሚያገናኝ ነው። ቅዱስ ጊዮርጊስ በአወዛጋቢዋ የኦኪኪ አፎላቢ የጭማሪ ደቂቃ ጎል ጅማ ላይ ነጥብ በመጣሉ ምክንያት ሊጉን መምራት የሚችልበት ዕድል መክኗል። ከበላዩ ካሉት ሶስት ቡድኖች ጋር እኩል 42 ነጥብ ላይ የሚገኘው የአምናው ሻምፒዮን የግብ ልዩነቱ ማነስ 4ኛ ደረጃ ላይ እንዲቀመጥ አድርጎታል። ሆኖም ተጋጣሚው ባለፉት ሶስት ጨዋታዎች 9 ግቦችን ያስተናገደ መሆኑ ግቦችን በብዛት አስቆጥሮ ለማሸነፍ እንዲያልም የሚያደርገው ነው። የሊጉ ግርጌ ላይ የተቀመጠው ወልዲያ ከበላዩ ካለው ኢትዮ ኤሌክትሪክ ጋር እንኳን የአምስት ነጥቦች ልዩነት ተፈጥሮበታል። በዚህ ሰዐት ከቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር መገናኘቱ ደግሞ ይበልጥ ፈተናውን ከፍ ያደርገዋል። ወልዲያ በሊጉ የመቆየት ተስፋው ከዚህም በላይ እንዳይመነምን ከዚህ ጨዋታ ሙሉ ነጥብ ይዞ መውጣት ይጠበቅበታል።

ቅስዱ ጊዮርጊስ አሁንም ሶስቱ አጥቂዎቹን አማራ ማሌ ፣ ሪቻርድ አፒያ እና ሳልሀዲን ሰይድን በጉዳት ሲያጣ አዳነ ግርማ በመከላከያው ጨዋታ እንዲሁም አቡበከር ሳኒ ጅማ ላይ ባይዋቸው ቀይ ካርዶች ምክንያት በቅጣት ጨዋታው ያልፋቸዋል። በወልዲያ በኩል ግን ከሠለሞን ገብረመድህን ጉዳት እና ከብሩክ ቃልቦሬ በቀር ቀሪዎቹ ተጨዋቾች ሙሉ ጤንነት ላይ እንደሚገኙ ሰምተናል።

ቅዱስ ጊዮርጊስ መሀል ሜዳ ላይ የሚጠቀምበት የሙሉአለም መስፍን እና የናትናኤል ዘለቀ ጥምረት በተጋጣሚዎቹ የመሀል ለመሀል ጥቃት እንዳይሰነዘርበት እንዲሁም ከኃላ ኳስን መስርቶ ሲወጣም በቀላሉ ቅብብሎችን እንዲያደርግ እያገዘው ይገኛል። በነገው ጨዋታ ግን ተጋጣሚው ወደ ኃላ ሊያፈገፍግ የሚችል በመሆኑ የተጨዋቾቹ ጥምረት እንደወትሮ በጎን ከሚሆን ይልቅ በቁመት እንደሚሆን ይጠበቃል። በዚህም ናትናኤል ለኒኪማ ቀርቦ በመጫወት ማጥቃቱን የማገዝ ሀላፊነት ይኖረዋል። የመስመር አማካዮቹ ደግማ ለኒኪማ እና ናትናኤል ከተጠጋ ቦታ አያያዝ ይልቅ የወልዲያን የመስመር ተከላካዮች በማፈን እንዲሁም ከጀርባቸው ለመገኘት በሚደረግ ጥረት ላይ ትኩራት እንደሚያደርጉ ይገመታል። እዚህ ላይ የቡድኑ የመስመር ተከላካዮች በተለይም ድንቅ አቋም ላይ የሚገነው አብዱልከሪም መሀመድ የማጥቃት ተሳትፎ የወልዲያን የመከላከል አደረጃጀት ሰብሮ ለመግባት ጠቃሚ ይሆናል።

ወልዲያ ቢያንስ በጨዋታው መጀመሪያ ወደ ራሱ የግብ ክልል ያፈገፈገ እና ጥንቃቄ ላይ መሰረት ያደረገ አቀራረብ እንደሚኖረው ይጠበቃል። ከአራቱ የኃላ መስመር ተሰላፊዎች ባለፈ ቀሪዎቹ አራት አማካዮችም ለተከላካይ ክፍሉ በመቅረብ እና በመሀል ያለውን ክፍትተ በመዝጋት ተጋጣሚያቸው የቅብብል አማራጮችን እንዳያገኝ ያለኳስ የሚያደርጉትን እንቅስቃሴ በትኩረት እንዲከውኑ ይጠበቃል። በዚህ ሂደት ውስጥ ኳስ የሚቀሙባቸውን አጋጣሚዎች ለፊት አጥቂዎቻቸው የመጣል አካሄድም ግብ እንዲያገኙ የሚረዳቸው አማራጭ ነው።  ይህን በአግባቡ ለመከውን ግን ጊዜያቸውን የጠበቁ እና ለመሀል ሜዳው ቀርቦ ከሚጫወተው የተጋጣሚያቸው የኃላ ክፍል ጀርባ ያለውን ሰፊ ታሳቢ ያደረጉ ኢላማቸውን የጠበቁ ተሻጋሪ ኳሶችን ማድረስ ይጠበቅባቸዋል።

የእርስ በእርስ ግንኙነት እና እውነታዎች

– ሁለቱ ቡድኖች እስካሁን በሊጉ 5 ጊዜ ተገናኝተው ቅዱስ ጊዮርጊስ 4 ጊዜ ሲያሸንፍ አንድ ጊዜ (ዘንድሮ) አቻ ተለያይተዋል። ወልዲያ ቅዱስ ጊዮርጊስን አሸንፎ አያውቅም። ቅዱስ ጊዮርጊስ 9 ጎሎች ሲያስቆጥር ወልዲያ አንድ ብቻ አስቆጥሯል።

– አዲስ አበባ ላይ 2 ጊዜ ተገናኝተው ቅዱሰ ጊዮርጊስ 4-1 (በ2007) እና 1-0 ( በ2009) አሸንፏል።

– ቅዱስ ጊዮርጊስ ካለፉት አራት ጨዋታዎች ሶስቴ አሸንፎ አንዴ አቻ የወጣ ሲሆን በነዚህ ጊዜያት በጨትታ ከአንድ በላይ ጎል ማስቆጠር አልቻለም

– የወልድያ የመጨረሻ አምስት ጨዋታዎች በሙሉ በሽንፈት የተጠናቀቁ ሲሆን ቡድኑ አንድም ጊዜ ግብ ማስቆጠር አልቻለም።

ዳኛ

– ይህ ጨዋታ የሚመራው በኢንተርናሽናል ዳኛ ብሩክ የማነብርሃን አማካይነት ይሆናል።