ነገ በአርባምንጭ ፣ ሀዋሳ እና ዓዲግራት የሚደረጉትን ሶስት የ26ኛው ሳምንት የሊጉ ጨዋታዎች በክፍል ሁለት ቅድመ ጨዋታ ዳሰሳችን እንደሚከተለው ተመልክተናቸዋል።
አርባምንጭ ከተማ ከ ወላይታ ድቻ
ሁለቱ ቡድኖች በመሀከላቸው የሶስት ነጥብ ልዩነት ኖሮ እና ላለመውረድ በሚደረገው ፉክክሩ ውስጥ ተሳታፊ ሆነው ነው በ10ኛው የዳንጉዛ ደርቢ የሚገናኙት። በአሰልጣኝ ንጉሴ ደስታ ድንገተኛ ዕልፈት አዲስ አበባ ላይ ከደደቢት ጋር ሊያደርገው የነበረው ጨዋታ የተላለፈው አርባምንጭ የማይቀመስ ወደ ሆነበት ሜዳው ተመልሷል። አንድ ተስተካካይ ጨዋታ እያለው በወራጅ ቀጠና ውስጥ የሚገኘው አርባምንጭ በሁለተኛው ዙር ያገኛቸውን ድሎች በሙሉ ሜዳው ላይ ከማሳካቱ አንፃር ከዚህም ጨዋታ ሙሉ ነጥቦችን ስለማግኘት ያልማል። ከተከታታይ አቻ ውጤቶች በኃላ ሜዳው በኢትዮጵያ ቡና የተረታው ወላይታ ድቻም ቀስ በቀስ ወደ ወራጅ ቀጠናው ቀርቧል። 10ኛ ደረጃ ላይ ቢቀመጥም የነጥብ ልዩነቱ መጥበብ ግን ለሶዶው ክለብ ስጋትን የሚጭር ነው። በደረጃ ሰንጠረዡ ካለው ቅርርብ በተጨማሪ በመሀላቸው ባለው የደርቢ ስሜት ምክንያት ጨዋታው ከፍተኛ ፍልሚያ እንደሚያስተናግድም ይጠበቃል።
ባለሜዳው አርባምንጭ ከተማ ከጉዳት እና ቅጣት ነፃ ሆኖ ለነገው ጨዋታ ይቀርባል። በወላይታ ድቻ በኩል ደግሞ ኃይማኖት ወርቁ ለመጀመሪያ ጊዜ በጉዳት ከጨዋታ ውጪ ሲሆን ያሬድ ዳዊትም በተመሳሳይ ጉዳት ላይ ይገኛል። ከዚህ ውጪ ድቻዎች አምበላቸው ተክሉ ታፈሰን በ5 ቢጫ ካርዶች ቅጣት የማያሰልፉ ሲሆን ጃኮ አራፋትን ከጉዳት ወንደሰን ገረመውን ክለቡ አስተላልፎበት ከነበረው ቅጣት በይቅርታ የሚመለሱላቸው ይሆናል።
በሜዳው ተደጋጋሚ ጥቃቶችን በመሰንዘር ግቦችን በርከት አድርጎ የሚያስቆጥረው አርባምንጭ ከተማ በዚህ ጨዋታ ተመሳሳይ አቀራረብ እንደሚኖረው ይጠበቃል። በወልዲያው ጨዋታ ሶስት ግቦችን ያስቆጠረው ተመስገን ካስትሮም በድጋሜ ከመሀል ተከላካይነት ወደ ፊት አጥቂነት መምጣቱም የሚቀር አይመስልም። ተመስገን ከሌላኛው አጥቂ ብርሀኑ አዳሙ ወይም በረከት አዲሱ ጋር የሚኖረው ጥምረት ከድቻው ብቸኛ የተከላካይ አማካይ እና የተከላካይ መስመሩ መሀል በሚኖረው ክፍተት ላይ ወደ ኃላ እየተሳቡ በመንቀሳቀስ ከነእንዳለ ከበደ የሚነሱ ኳሶችን ለመቀበል የሚያደርጉት እንቅስቃሴ የቡድኑ ዋነኛ የማጥቃት ዕቅድ ሊሆን የሚችልበት ዕድል እንዳለ መናገር ይቻላል።
በሳምንቱ አጋማሽ ከሶከር ኢትዮጵያ ጋር ቆይታ አርገው የነበሩት አሰልጣኝ ዘነበ ፍሰሀ የቡድናቸው ወቅታዊ የውጤት ማጣት ሂደት ከተጨዋቾቻቸው ታክቲካዊ ሀላፊነቶችን በሚገባ አለመተግበር ጋር እንደሚገናኝ ገልፀዋል። አሰልጣኙ ቡድኑ ችግሮቹን ለመቅረፍ እየተንቀሳቀሰ እንደሚገኝ ከመናገራቸውም አንፃር ድቻ ውጤታማ በነበረበት ወቅት በሚያደርገው መልኩ አርባምንጭን ይገጥማል ተብሎ ይገመታል። በመሆኑም ምንም እንኳን ኃይማኖት ወርቁ ባይኖርም በ4-1-4-1 አሰላለፍ ጃኮ አራፋት ፊት ላይ ቦታ እየቀያየረ ከሚያደርገው እንቅስቃሴ እና በመስመር አማካዮቹ ወደ ውስጥ የጠበበ ጥቃት አርባምንጭን እንደሚፈትኑ ይጠበቃል። የአብዱልሰመድ አሊ እና በዛብህ መለዮ የአማካይ ክፍል ጥምረትም ከአለልኝ አዘነ እና አማኑኤል ጎበና ጋር በመጋፈጥ በብቸኛው አጥቂ እና የተከላካይ አማካይ መሀል በመሆን የቡድኑን ሚዛን የመጠበቅ ሀላፊነት ይጣልበታል።
የእርስ በእርስ ግንኙነት እና እውነታዎች
– በእስካሁኖቹ 9 ግንኙነታቸው አርባምንጭ አንድ ጊዜ ብቻ (2007) ሲያሸንፍ 5 ጊዜ አቻ ተለያይተው ወላይታ ድቻ ሶስቱን አሸንፏል።
– የጎል ድርቅ በመታው የእርስ በእርስ ግንኙነት ታሪካቸው በ9 ጨዋታ 8 ጎል ብቻ ሲቆጠር አርባምንጭ 2 ፣ ወላይታ ድቻ 6 አስቆጥረዋል።
– አርባምንጭ ላይ 4 ጊዜ ተገናኝተው አርባምንጭ በአንዱም ድል ማስመዝገብ ሲሳነው ድቻ አንድ ጊዜ አሰሸንፏል። ሶስት ጨዋታዎች ደግሞ በአቻ ውጤት ተጠናቀዋል።
– ወላይታ ድቻ ከመጨረሻዎቹ ስድስት ጨዋታዎቹ መሀከል በሁለቱ ነጥብ ሲጋራ አራት ጊዜ ሽንፈት ገጥሞታል። ከነዚህ ሽንፈቶች ሶስቱ ከሜዳው ውጪ የገጠሙት ነበሩ።
– አርባምንጭ ከተማ በሁለተኛው ዙር ሜዳው ላይ ያደረጋቸውን አራት ጨዋታዎች በሙሉ ሲያሸንፍ 11 ግቦችን አስቆጥሮ አንድም ጊዜ መረቡን ሳያስደፍርም ጭምር ነበር።
ዳኛ
– ይህ ጨዋታ የሚመራው በኢንተርናሽናል ዳኛ አማኑኤል ሃ/ስላሴ አማካይነት ነው።
ሲዳማ ቡና ከ ድሬዳዋ ከተማ
አርብ ምሽት የተሰማው የአዳማ በፎርፌ ውጤት ወደ መሪነት መምጣት ዜና ሁለቱን ቡድኖች በዋነኝነት ደግሞ ሲዳማን የነካም ነበር። 5 ቢጫ የነበረበትን አዲስ ግደይን በተሸነፈበት የሀዋሳው ጨዋታ አሰልፎ ክስ የተመሰረተበት ሲዳማ 1-0 ባሸነፈበት የአዳማውም ጨዋታ ተጨዋቹን መጠቀሙ ለፎርፌ ዳርጎታል። ሁኔታውም ነጥቡን ወደ 29 ዝቅ በማድረጉ በነገ ተጋጣሚው በግብ ልዩነት ተበልጦ ወደ 12ኝነት ዝቅ እንዲል አድርጎታል። በመሆኑም ሰባተኛው የመውረድ ስጋት ያለበት ቡድን ሆኖ ወደ ታችኛው ሰንጠረዥ ፉክክር መጥቷል። ከ22ኛው ሳምንት ጀምሮ ከሽንፈት የራቀው ድሬዳዋ ከተማ ያለበት ደረጃ ወቅታዊ አቋሙን አይገልፀውም። ካለፉት አምስት ጨዋታዎች የሰበሰባቸው 11 ነጥቦችም ወደ 11ኛ ደረጃ ያመጡት ቢሆንም የነጥብ ቅርርቡ አሁንም ከስጋት ነፃ አላደረገውም። ከዚህ አንፃር በነገው ጨዋታ ነጥብ ማግኘት ካለው ዋጋ አንፃር ሁለቱም ቡድኖች ከባድ ፍልሚያ የሚያደርጉ ይሆናል።
የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ ለፍቼ ጨምበላላ በዓል ድምቀት እንዲሆን በማሰብ ሀዋሳ ላይ እንዲካሄድ ተወስኗል። በተያያዘ ዜና ድሬዳዋ ከተማዎች ሀዋሳ በገቡበት ሰዐት ከሲዳማ አቻቸው አቀባበል እንዳልተደረጋለቸው እና ከአየር ማረፊያ ወደ ከተማ የሚገቡበት ትራንስፖርትም ሆነ ልምምድ የሚያደርጉበት ሜዳ ሳይዘጋጅላቸው በመቅረቱ ለከፍተኛ እንግልት መዳረጋቸውን የቡድን መሪው አቶ ቶፊቅ ሀሰን ገልፀዋል።
ፍፁም ተፈሪ በጉዳት ፣ ወንድሜነህ አይናለም ደግሞ በሀዋሳው ጨዋታ በተመለከተው ቀይ ካርድ በቅጣት ከሲዳማ ቡና የነገው ስብስብ ውጪ ሆነዋል። በድሬዳዋ ከተማ በኩል ደግሞ ሚካኤል አካፉ በጉዳት እንዲሁም ሱራፌል ዳንኤል በአምስተኛ ቢጫ ካርድ የማይሰለፉ ተጨዋቾች ናቸው።
ሲዳማ ቡና በመጨረሻ የፈጠረው የፍፁም ተፈሪ ፣ ዮሴፍ ዮሀንስ እና ወንድሜነህ አይናለም ውጤታማ የመሀል ሜዳ ጥምረት በጉዳት እና ቅጣት ምክንያት መፍረሱ እንዲቸገር ሊያደርገው ይችላል። ቡድኑ ለመልሶ ማጥቃት ወደ ሚጠቀምባቸው ፈጣን የመስመር አጥቂዎቹ ኳሶችን የሚያደርስበት መንገድ ዕክል እንዳይገጥመውም ሀዋሳ ላይ የተሰለፍ ዕድል ያገኘው ትርታዬ ደመቀ እና ወንድሜነህ ዘሪሁንን የሚጠቀምበት ሁኔታ ሊፈጠር ይችላል። በአጨዋወት ደረጃ ግን አሁንም በፈጣን የማጥቃት ሽግግር ከአማካይ ክፍሉ በቶሎ በሚለቀቁ ኳሶች ወደ ድሬዳዋ የሜዳ ክልል ለመግባት እንደሚሞክር ይጠበቃል።
ግቦችን በርከት አድርጎ የማያስቆጥረው ድሬዳዋ ከተማ በዚህም ጨዋታ የኃላ ክፍል ጥንካሬው በእጅጉ ያስፈልገዋል። ቡድኑ ሱራፌል ዳንኤልን የማይጠቀም በመሆኑም ወደ 4-2-3-1 አሰላለፍ ተመልሶ ኢማኑኤል ላርያ እና ሳውሬል ኦልሪሽን ሊያጣምር ይችላል። ይህ የሚሆን ከሆነ ደግሞ አትራም ኩዋሜ ወይም ሀብታሙ ወልዴ በብቸኛ አጥቂነት ቡድኑን የሚመሩበት ዕድል ይኖራል። በዚህ ሁኔታም ሶስቱ አማካዮች ኳሶችን ወደ አጥቂው ከማድረሳቸው በፊት ከሲዳማ የመሀል ክፍል ጋር በሚጠብቃቸው ፍልሚያ የመስመር ተከላካዮቻቸውን እገዛ መሻታቸው የግድ ይሆናል። ይህ ሁኔታ ደግሞ የመስመር ተከላካዬቹ ከሲዳማ የመስመር አጥቂዎች ጋር የሚናራቸውን ፉክክር ከወዲሁ ተጠባቂ ያደርገዋል።
የእርስ በእርስ ግንኙነት እና እውነታዎች
– ከ11 ግንኙነታቸው ሲዳማ 4 ጊዜ ሲያሸንፍ 6 ጊዜ አቻ ተለያይተው ድሬዳዋ አንድ ጊዜ ብቻ አሸንፏል። ሲዳማ 9 ሲያስቆጥር ድሬዳዋ 5 አስቆጥሯል።
– የድሬዳዋ ብቸኛ ድል የተመዘገበው በመጀመርያ የእርስ በእርስ ግንኙነታቸው ሲሆን ይርጋለም ላይ በተደረገው ጨዋታ 1-0 አሸንፎ ነበር።
– ሲዳማ ቡና ፎርፌ የተሰጠበትን የአዳማ ከተማ ጨዋታ ጨምሮ ባለፉት ሶስት ሳምንታት ማግኘት የቻለው ሁለት ነጥቦችን ብቻ ነው።
– ድሬዳዋ ከተማ ከመጨረሻዎቹ አራት ጨዋታዎች 10 ነጥቦችን የሰበሰበ ሲሆን ከጎንደሩ የ0-0 ውጤት በቀር ባሸነፈባቸው ሶስት ጨዋታዎች አንድ አንድ ግቦችን ነበር ያስቆጠረው።
ዳኛ
– ፌደራል ዳኛ አዳነ ወርቁ ጨዋታውን በመሀል ዳኝነት ለመምራት ተመድቧል።
ወልዋሎ ዓ.ዩ. ከ ደደቢት
በዚህ ሳምንት መጀመሪያ ላይ ከሰማነው የአሰልጣኝ ንጉሴ ደስታ ድንገተኛ ህልፈት በኃላ ደደቢት የመጀመሪያ ጨዋታውን ዓዲግራት ላይ ያደርጋል። ባለሜዳዎቹ ወልዋሎዎች ከመቐለ ከተማ ጋር የነበራቸውን ቀሪ 45 ደቂቃ በውጤት ካጠናቀቁ በኃላ ከአባ ጅፋር አንድ ከወልዲያ ደግሞ ሶስት ነጥብ ማግኘታቸው ወደ 27 ነጥብ አድርሷቸዋል። ሆኖም የሶስት ጨዋታ አለመሸነፍ ጉዞው ብቻ ከስጋት አላራቃቸውም። ከወራጅ ቀጠናው በአንድ ደረጃ ከፍ ቢሉም ከዚህ ጨዋታ ሙሉ ነጥብ መሰብሰብ ግን አሁንም አስፈላጊያቸው ነው። በሁለተኛው ዙር በውጤት ማጣት ውስጥ የቆየው ደደቢት ወደ ዋንጫ ፉክክሩ በመጠኑም ቢሆን ለመጠጋት አርባምንጭን ለመግጠም በሚዘጋጅበት ወቅት የተሰማው የአሰልጣኝ ንጉሴ ደስታ ህልፈት ጨዋታው በይደር እንዲያዝ አድርጎታል። የነገው ጨዋታም ቡድኑ ከዚህ አስደንጋጭ እና ከባድ ሀዘን በኃላ በምን አይነት አኳኃን ወደ ሜዳ ይመለሳል ይሚለውን ጥያቄ መልስ የምናይበትም ይሆናል።
በጨዋታው ከበረከት ተሰማ እና አሳሪ አልመሀዲ ቅጣት ውጪ ወልዋሎ ዓ.ዩ ሙሉ ስብስቡን ይዞ የሚቀርብ ሲሆን ደደቢትም በኢትዮጵያ ቡናው ጨዋታ በቀይ ካርድ ካጣው ጋናዊ ተከላካይ አንዶህ ኩዌክ ውጪ ሌላ የጉዳትም ሆነ የቅጣት ዜና አልተሰማበትም።
በሚከተሉት የ4-3-3 አሰላለፍ እንዲሁም በአጨዋወታቸውም ጭምር ሁለቱ ቡድኖች ተመሳሳይነት ይታይባቸዋል። አማካይ ክፍል ላይ ለሚጠቀሙባቸው ተጨዋቾች ከሚሰጡት ሀላፊነት እንዲሁም ለኳስ ቁጥጥር ካላቸው ቦታ አንፃርም በጨዋታው መሀል ላይ የሚኖረው ፍልሚያ ተጠባቂ ይሆናል። የወልዋሎዎቹ አፈወርቅ ሀይሉ እና ዋለልኝ ገብሬ እንዲሁም የደደቢቶቹ አቤል እንዳለ እና የአብስራ ተስፋዬ የሚገናኙባቸው አጋጣሚዎችም በዚህ ሂደት ውስጥ ወሳኝ ይሆናሉ። ተጨዋቾቹ እርስ በእርስ እና ከመስመር ተሰላፊዎች ጋር የሚኖራቸው የቅብብል ስኬት የበላይነቱን ለመውሰድ አስፈላጊያቸው ይሄናል። አጠቃላይ እንቅስቃሴያቸውም ለፊት አጥቂዎቹ ሪቻርድ ኦዶንጎ እና ጌታነህ ከበደ የመጨረሻ የግብ ዕድሎችን የመፍጠር አላማ ይኖረዋል።
በእንቅስቃሴ ወደ ሶስተኛው የሜዳ ክፍል በሚርደሱባቸው አጋጣሚዎች ደግሞ ሁለቱም ቡድኖች በመስመር አጥቂዎቻቸው በኩል አድርገው ወደ ውስጥ መግባት ይቀናቸዋል። በመሆኑም ከፊት አጥቂዎቹ በተጨማሪ ከመስመር የሚነሱት ሁለት አጥቂዎችም በቡድኖቹ የፊት መስመር እንቅስቃሴ ላይ ጉልህ ሚና ይኖራቸዋል። ወደ አማካይ ክፍሉ ቀርበው ቅብብሎችን ሲከውኑ የሚታዩት የወልዋሎዎቹ ፕሪንስ ሰቨሪንሆ እና አብዱርሀማን ፉሰይኒ ከዚህ ሀላፊነታቸው በተጨማሪ የሜዳውን ስፋት በመጠቀም ከደደቢት የመስመር ተከላካዮች ጋር የሚያደርጉት ፍጥጫ ተጠባቂ ነው። ተመሳሳይ ሚናን በመወጣት የሚታወቁት ኤፍሬም አሻሞ እና ሽመክት ጉግሳ ወይም አቤል ያለው ደግሞ እንደመጀመሪያው ዙር የአዲስ አበባ ስታድየም የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ የተጋጣሚያቸው የኃላ መስመር ከግብ ጠባቂው ጋር የሚተወውን ሰፊ ክፍተት ለመጠቀም ተጭነው መጫወታቸው የማይቀር ነው።
የእርስ በእርስ ግንኙነት እና እውነታዎች
– የመጀመሪያው የቡድኖቹ የሊጉ ግንኙነት አዲስ አበባ ላይ በደደቢት 3-1 አሸናፊነት የተጠናቀቀ ነበር።
– ጨዋታው ለወልዋሎ ዓ.ዩ በሁለተኛው ዙር በሜዳው የሚያደርገው አራተኛ ጨዋታ ሲሆን እስካሁን አንዴ ሲያሸንፍ ሁለት ጊዜ ደግሞ የ1-1 ውጤት አስመዝግቧል።
– ደደቢት ካለፉት ሰባት ጨዋታዎች በሁለቱ አቻ ውጤት ሲያስመዘግብ በቀሪዎቹ ተሸንፏል።
ዳኛ
– የሁለቱን ቡድኖች ጨዋታ በመሀል ዳኝነት የሚመራው ፌደራል ዳኛ ተፈሪ አለባቸው ነው።