ጋና በህዳር 2018 ታዘጋጃለች ተብሎ ለሚጠበቀው የአፍሪካ ሴቶች ዋንጫ ለማለፍ ዛሬ ወሳኝ ሆነውን የመልስ ጨዋታ አዲስ አበባ ላይ ያደረገው የኢትዮጵያ ሴቶች ብሄራዊ ቡድን በአልጄሪያ 3-2 (6-3 የአጠቃላይ ውጤት) ተሸንፎ ከውድድር ውጪ ሆኗል፡፡
10፡00 ሰዓት መጀመር የነበረበት ጨዋታው በጣለው ከባድ ዝናብ ምክንያጥ የመጫወቻ ሜዳው ውሃ በመያዙ በ30 ደቂቃዎች ተራዝሞ ነበር የተጀመረው፡፡ የጨዋታው አርቢትሮች እና ኮሚሽነሯ ሜዳው እንደማያጫውት በማመን ግጥሚያው እንደይካሄድ ቢፈልጉም የሉሲዎቹ የቡድን መሪ መስከረም ታደሰ ጥረት መግባባት ላይ ተደርሶ ጨዋታው በ30 ደቂቃ ተገፍቶ ሊጀመር ችሏል፡፡
ከቀናት በፊት አልጀርስ ላይ 3-1 ከተሸነፈው የሉሲቹ ቋሚ 11 ውስጥ አሰልጣኝ ሰላም ዘርዓይ የአራት ተጫዋች ለውጥ አድርጋ ወደ ሜዳ ገብታለች፡፡ ግብ ጠባቂዋ አባይነሽ ኤርቀሎ፣ ብዙዓየሁ ታደሰ እና ገነሜ ወርቁ እና እመቤት አዲሱ በጨዋታው ላይ በመጀመርያ አሰላለፉ ውስጥ የተካተቱ ተጫዋች ሲሆኑ በአልጄሪያ በኩል የተጫዋች ለውጥ ሳያደርጉ ነበር ጨዋታው የተጀመረው፡፡
በአዲስ አበባ ስታዲየም ሜዳ መጨቅየት ምክንያት ሁለቱም ቡድኖች ኳስን ተቆጣጥረው ለመጫወት ሲቸገሩ ሲስተዋል ይበልጥ ደግሞ ከራሳቸው የሜዳ ክፍል ኳስን አደራጅቶ ለመውጣት ጥረት ሲያደርጉ ለነበሩት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድ ተጫዋቾች ፈተናውን አበርትቷል፡፡ ጨዋታው በተጀመረ በሶስተኛው ደቂቃ ከማዕዘን ምት የተሻገረ ኳስ በአልጄሪያ የግብ ክልል ትርምስ ከፈጠረ በኃላ ታሪኳ ደቢሶ አግኝታ በቀጥታ ወደ ግብ ብትልክም የአልጄሪዋ ካሂና ታኬኒንት በቀላሉ በያዘችው ሙከራ የመጀመርያው የግብ አጋጣሚ የፈጠሩት ሉሲዎች በፈጣን እንቅስቃሴ ወደ አልጄሪያ የግብ ክልል ለመግባት የሚያደርጉት ጥረት ከደቂቃ ወደ ደቂቃ እየተዳከመ እና በአልጄሪያ ተከላካዮች በቀላሉ እየታፈነ ሊቀዘቅዝ ችሏል፡፡
በራሳችን የሜዳ ክልል ላይ አብዛኞቹ ተጫዋቾቻችን መገኘታቸው እና በማጥቃቱ ወረዳ በቂ የተጫዋቾች ቁጥር አለመኖር ይበልጥ ለእንግዶቹ ነገሮችን እንዲቀሉ አድርጓል፡፡ በ18ኛው ደቂቃ በካናዳ የተወለደችው አሲያ ሲዶም በኢትዮጵያ ተከላካዮች አናት ላይ ያሻገረችውን ኳስ ለሉሲዎቹ ፈተና የነበረችው ነኢማ ቦውሄኒ በደረቷ አብርዳ ኳስን ወደ ግብነት በመለወጥ አልጄሪያን ቀዳሚ አድርጋለች፡፡ የአልጄሪያዎች ግብ ባለሜዳዎቹን ጫና ውስጥ የከተተ ሲሆን በቀላሉም የማጥቃት እንቅስቃሴያቸው የተሳካ እንዳይሆን አድርጎታል፡፡ አልጄሪያዎች በሁለቱም ጨዋታዎች ለኢትዮጵያ ተከላካዮች ፈተና የነበረችው ቦሄኒ ላይ መሰረት ያደረገ የማጥቃት እንቅስቃሴ ሲደርጉ ታይተዋል፡፡ በ26ኛው ደቂቃ ከመሃል በረጅሙ የተሻገረውን ኳስ ቦሄኒ አግኝታ ውሳኔ ለመወሰን በማቅማማት ላይ በነበረችው አባይነሽ ግብ ላይ ብትሞክርም ኳስ ወደ ውጪ የወጣዝ ኳስም ለዚት ማሳያ ነበር።
ከ29ኛው ደቂቃ ጀምሮ ሉሲዎቹ የማጥቃት እንቅስቃሴያቸው ላይ መጠነኛ መሻሻሎችን ማየት ችለናል፡፡ የዙሌካ ጁሃድ እና የሎዛ አበራን ግብ መሆን የሚችሉ እድሎችንም ታኬኒንት አምክናለች፡፡ መደበኛው ደቂቃ አልቆ ወደ መልበሻ ክፍል ለእረፍት ቡድኖቹ ከማምራታቸው በፊት ከቅጣት ምት የተሻገረውን ኳስ አምበሏ ፋቲማ ሴኮውኔ በግንቧራ በመግጨት የአልጄሪያን መሪነት ወደ ሁለት ከፍ አድርጋለች፡፡
ሉሲዎቹ ከእረፍት መልስ በተሻለ መልኩ ተጭነው ለመጫወት ቢሞክሩም ለአልጄሪያዎች መልሶ ማጥቃት በቀላሉ የተጋለጡ ነበር፡፡ ቦሄኒ ከ30 ሜትር ርቀት ኳስ ገፍታ በሳጥኑ ውስጥ ሆኗ የመታችውን ኳስ አባይነሽ ብታድንም በፈረንሳይ የምትጫወተው ሜሪያም ቤንላዛር የተተፋውን ኳስ አስቆጥራ እንግዶቹ 3-0 መምራት እንዲችሉ አድርጋለች፡፡
የአረጋሽ ከልሳ ወደ ሜዳ ተቀይሮ መግባት የሉሲዎቹ የማጥቃት እንቅስቃሴ ላይ ለውጥ መፍጠር ችሏል፡፡ በ63ኛው ደቂቃ ሎዛ በግሩም ሁኔታ ከ18 ሜትር በግራ እግሯ አክርራ በመምታት የግብ ልዩነቱን ስታጠበው ከ9 ደቂቃዎች በኃላ ትግስት ዘውዴ ከቀኝ መስመር ያሻገረችውን ኳስ አሁንም ሎዛ በግንባሯ ገጭታ በማስቆጠር ልዩነቱን ወደ 3-2 አውርዳለች፡፡ ከዚች ግብ መገኘት በኃላ ሉሲዎቹ በሎዛ፣ ረሂማ ዘርጋ እና ህይወት ደንጊሶ ተደጋጋሚ ሙከራዎችን ቢያደርጉም ወደ ግብነት ሊለወጡ አልቻሉም፡፡ በውጤቱም አልጄሪያ በአጠቃላይ ውጤት 6-3 በማሸነፍ ከ2014 በኃላ ወደ አፍሪካ ዋንጫው ሲመለሱ ኢትዮጵያ ከ2012ቱ ውድድር በኋላ ዳግም ወደ አፍሪካ ዋንጫው መመለስ ተስኗታል፡፡ በጨዋታው ላይ አረጋሽ ከሉሲዎቹ በኩል እንዲሁም ቦሄኒ ከአልጄሪያ በኩል ጨዋታውን በታደመው ደጋፊ በኩል አድናቆት ተችሯቸዋል፡፡
ኢትዮጵያ በአልጄሪያ ተጫዋቾች ተገቢነት ጥያቄ ክስ አቅርባለች፡፡ አሳማኝ ክስ እንደሆነ የተነገረለት የሉሲዎቹ ክስ ለካፍ ሲቀርብ 2000 የአሜሪካ ዶላር ማስያዣ ይጠየቅበታል፡፡ ሁለቱ ተጫዋቾች በፊፋ የወዳጅነት ጨዋታዎች ላይ እና የዞን ቻምፒዮናዎች ላይ የተባበሩት የአረብ ኤምሬቶችን ወክለው ሲጫወቱ የሚያሳይ በምስል የተደገፈ ማስረጃ ብሔራዊ ቡድን በክሱ እንዳቀረበ ለማወቅ ተችሏል፡፡