በዕለቱ የመጨረሻ በነበረው የ26ኛ ሳምንት የሊጉ ጨዋታ ቅዱስ ጊዮርጊስ ወልዲያን አስተናግዶ 3-1 በማሸነፍ ከረጅም ጊዜያት በኋላ በሰንጠረዡ አናት መቀመጥ ችሏል።
በጨዋታው ቅዱስ ጊዮርጊስ ጅማው ላይ ከተጠቀመው የመጀመሪያ አሰላለፍ ምንም አይነት ለውጥ ሳያደርግ ወደ ሜዳ ሲገባ ወልዲያም ያሬድ ሀሰንን ተጠባባቂ አድርጎ ለኤደም ኮድዞ ዕድል ከመስጠቱ በቀር በወልዋሎ 1-0 የተሸነፈበትን የመጀመሪያ አሰላለፍ ተጠቅሟል።
በዕለቱ በአዲስ አበባ ስታድየም ከተስተናገዱት ሶስት ጨዋታዎች መሀከል ፈጣን እና ጥሩ ፉክክር ያስመለከተን የመጀመሪያው አጋማሽ በወልዲያዎች ጫን ያለ አጨዋወት ነበር የጀመረው። አንዱአለም ንጉሴን እና ኤደም ኮድዞን በፊት አጥቂነት በማሰለፍ ጨዋታውን የጀመሩት ወልዲያዎች ኳስ ይዘው ለመጫወት የሞከሩ ሲሆን በድንገት አንድ ጊዜ ለአንዱአለም ሌላ ጊዜ ደግሞ ለኤደም የጣሏቸው ኳሶች አደጋ ለመፍጠር ተቃርበው ነበር። 5ኛው ደቂቃ ላይም ተስፋዬ አለባቸው ከርቀት አክርሮ የመታውን ኳስ አንዱአለም ጨርፎ የመጀመሪያ ግብ አስቆጥሯል። ከግቧ መቆጠር በኃላ ቅዱስ ጊዮርጊሶች ምላሽ ለመስጠት የፈጀባቸው ጊዜ አራት ደቂቃ ብቻ ነበር። 9ኛው ደቂቃ ላይ ታቫሬዝ ከአሜ የተቀበለውን ኳስ በግራ በኩል ይዞ ገብቶ ሞክሮ ደረጄ ሲያድንበት በሀይሉ ቱሳ የተመለሰውን ኳስ በድጋሚ በመምታት ቡድኑን አቻ አድርጓል።
ጨዋታው በመጀመሪያዎቹ አስር ደቂቃዎች ሁለት ግቦችን ካስተናገደ በኃላም በመጠኑ ጋብ ብሏል። 12ኛው ደቂቃ ላይ ሙሉአለም መስፍን ከሳጥን ውጪ አክርሮ ከሞከረው ኳስ በኃላም እስከ ሀያዎቹ አጋማሽ ደቂቃዎች ሙከራ አልተስተዋለም። የሜዳው መጨቅየት ተጨዋቾች የሚያደርጉትን ቅብብል እጅግ ፈታኝ ያደረገው በመሆኑም ሁለቱ ቡድኖች የመጨረሻ የግብ ዕድሎችን እንዳይፈጥሩ ሆኗል። ቀስ በቀስ ግን ጨዋታው ወደ ቀደመው ፍጥነቱ መመለሱ አልቀረም። በሂደት ደጋግመው ወደ ወልዲያ የግብ ክልል መቃረብ የጀመሩት ቅዱስ ጊዮርጊሶች በ26ኛው እና 30ኛው ደቂቃዎች በሙሉአለም እና ሳላሀዲን ባርጌቾ ግቦች ውጤቱን ወደ 3-1 ከፍ አድርገውታል። የወልዲያ ተከላካዮች ሙሉአለም ከሳጥን ውስጥ መትቶ ሲያስቆጥር እና ሳላሀዲንም ከማዕዘን ምት ከተገኘ ዕድል በቀጥታ ሲያስቆጥር ግባቸውን በመሸፈኑ በኩል የነበረባቸው በድክመት የሚነሳ ነው። በተለይም ሙሉአለም ከፍ አድርጎ ወደ ግብ የላካትን ኳስ ማዳን በሚችሉበት የግቡ መስመር ላይ የነበሩት የቡድኑ የኃላ መስመር ተሰላፊዎች ጥረት ማነስ አስገራሚ ነበር። በሁለቱ ጎሎች መሀል ቅዱስ ጊዮርጊሶች 29ኛው ደቂቃ ላይም በኃይሉ ከሳጥን ውጪ ባደረገው ሙከራ ሌላ ግብ ለማግኘት ተቃርበው ነበር።
ቀሪዎቹ የመጀመሪያው አጋማሽ ደቂቃዎች የጨዋታው ግለት ቀንስ ያለባቸው ነበሩ። የኤደም ኮድዞ የ36ኛ ደቂቃ ኢላማውን የጠበቀ ሙከራም ተጠቃሽ የግብ ዕድል ነበር። ቅዱስ ጊዮርጊሶች በቀኝ መስመር ባሰለፉት በሀይሉ አሰፋ እንዲሁም ድንቅ አቋም ላይ በሚገኘው እና ከጀርባ በመነሳት ማጥቃቱን ሲያግዝ በነበረው አብዱልከሪም መሀመድ በኩል አመዝነው ጥቃቶችን ለመሰንዘር ሲሞክሩ ነበር። ለዚህም ይመስላል አሰልጣኝ አላለም ሽፈራው በቦታው ያሳለፉትን ተከላካይ አማረ በቀለን በ34ኛው ደቂቃ በያሬድ ሀሰን ቀይተው አስወጥተዋል። በሁለቱም ቡድኖች በኩል ወደ ፊት ገፍቶ ለመሄድ ይደረግ የነበረው ጥረት በቀጣዬቹ ደቂቃዎችም ቀጥሎ ነገር ግን ተጨማሪ ግቦችን ሳንመለከት የመጀመሪያው አጋማሽ ተጠናቋል።
ሁለተኛው አጋማሽ ሙሉአለም መስፍን ከማዕዘን ምት የተሻገረን ኳስ በግንባሩ የሞከረበትን አጋጣሚ በሶስት ደቂቃዎች ውስጥ ያሳየን ቢሆንም እንደመጀመሪያው ተሟሙቆ አልቀጠለም። አጨዋወታቸውን ለወጥ አድርገው የመጡት ወልዲያዎች ኳስ ከኃላ በመመስረት ወደ ግራ መስመር ወጥቶ እንዲጫወት እና የቁጥር ብልጫ እንዲያመጣላቸው ባሰቡት ኤደም ኮድዞ በኩል አድልተው ለማጥቃት ያቀዱ ይመስሉ ነበር። ህኖም ግን ቅብብሎቻቸው መሀል ሜዳውን ከመሻገራቸው በፊት ጫና በማሳደር ያስጨንቁ የነበሩት ቅዱስ ጊዮርጊሶች ከሚቀሟቸው ኳሶች በቶሎ ወደ ፍፁም ቅጣት ምት ክልል ሲደርሱ ይታዩ ነበር። 50ኛው ደቂቃ ላይ አብዱልከሪም መሀመድ መሀል ላይ ካስጣለው ኳስ በመነሳት ወደ ውስጥ የገባባት እንዲሁም መሀሪ መና እና ታቫሬዝ በ54ኛው ደቂቃ በቅብብል ወደ ወልዲያ ሳጥን የቀረቡባቸው አጋጣሚዎችም ተመሳሳይ ይዘት ነበራቸው። ወልዲያዎች ግን የተሻለ አስፈሪነት የነበራቸው መሀል ሜዳውን ባለፉባቸው አጋጣሚዎች ወደ ውስጥ ከሚጥሏቸው ኳሶች መነሻነት ነበር። በተለይም 57ኛው ደቂቃ ላይ ከግራ መስመር ለአንዷለም ተሻግሮለት በግንባሩ የጨረፈው ኳስ በዚህ ረገድ ተጠቃሽ ነበር።
ጨዋታው በዚህ ሁኔታ ቀጥሎ ከ65ኛው ደቂቃ በኃላ የተሻሉ ሙከራዎችን አስመልክቶናል። 68ኛው ደቂቃ ላይ በሀይሉ ከጀመረው ድንገተኛ ቅጣት ታቫሬዝ ወደ ውስጥ አሳልፎለት አሜ ሳይደርስበት የቀረው እንዲሁም 73ኛው ደቂቃ ላይ አሜ የወልዲያን ተከላካዮች ከጀርባው አድርጎ ሳጥን ውስጥ ከተገኘ በኃላ በቶሎ ባለመወሰኑ የተነጠቀበት አጋጣሚ ፈረሰኞቹ የግብ ልዩነቱን ከፍ ለማድረግ ተቃርበው የነበሩባቸው ዕድሎች ናቸው። ከዚህ ውጪ በጭማሪ ደቂቃ ታቫሬዝ በግራ በኩል ያሬድ ሀሰንን አታሎ ወደ ውስጥ ከገባ በኃላ ወደ ውስጥ ሲያሻማ ያለቅጥ ወደላይ የተነሳበት ኳስ ከባለሜዳዎቹ በኩል ተጠቃሽ አጋጣሚ ነበር። ከወልዲያዎች በኩልም 75ኛው ደቂቃ ላይ አንዷለም ከግራ መስመር ወደ ውስጥ ጥሎት የላይኛው መረብ ላይ ያረፈው እንዲሁም 89ኛው ደቂቃ ላይ ከአንዷለም የግንባር ኳስ መስፍን ኪዳኔ ከሮበርት ጋር የተገናኘበት አጋጣሚዎች የተሻሉ ነበሩ። ሆኖም ሁለቱም ቡድኖች ተጨማሪ ግብ ሳያስቆጥሩ ጨዋታው ተጠናቋል። በውጤቱም ቅዱስ ጊዮርጊስ ነጥቡን 45 አድርሶ አንደኛ ደረጃ ላይ ሲቀመጥ ወልዲያ ከበላዩ ካለው አርባምንጭ ጋር የተፈጠረውን የሰባት ነጥብ ልዩነት ማጥበብ ሳይችል በሊጉ ግርጌ ለመቅረት ተገዷል።
የአሰልጣኞች አስተያየት
አሰልጣኝ ቫስ ፒንቶ – ቅዱስ ጊዮርጊስ
ወልዲያ ነጥቡ ያስፈልገው የነበረ በመሆኑ እና ሜዳውም አስቸጋሪ በመሆኑ ጨዋታው ከባድ ነበር። ነገር ግን እንደማስበው በሁሉም ደቂቃዎች ከወልድያ የተሻለ ተጫውተናል። በጣም ወሳኝ ሶስት ነጥቦችን ነው ያገኘነው። በውጤቱም ደስተኛ ነኝ። ሊጉን መምራት መጀመራችንም ለቀጣይ ጨዋታዎች በራስ መተማመናችንን ከፍ ያደርገዋል።
አሰልጣኝ ዘላለም ሽፈራው – ወልዲያ
ጨዋታው ክፍት ነበር። እነሱም ለሻምፒዮንነት እየተጫወቱ በመሆኑ እና እኛም ላለመውረድ ያለውን ነገር ለማጠናከር በመፈለጋችን አጥቅተን ለመጫወት ሞክረናል። ያው እነሱ ያገኟቸውን አጋጣሚዎች ተጠቅመዋል። ያለንበት ሁኔታ አስፈሪ ነው። አይ ልንወርድ አንችልም ብል ሽንገላ ነው የሚሆነው። እስካልወረድን ድረስ ግን መውረዳችንን አናምንም።