በ26ኛው ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ጨዋታ አዲስ አበባ ላይ ሀዋሳ ከተማን ያስተናገደው ኢትዮ-ኤሌክትሪክ በሁለተኛው አጋማሽ በተቆጠሩ ሁለት ግቦችን 2-0 ማሸነፍ ችሏል፡፡ እንዳለፉት ዓመታት ሁሉ ላለመውረድ እየታገለ ያለው ኤሌክትሪክ ባለፈው ሳምንት ከደረበሰበት ከደድ ሽንፈት አገግሞ ወደ ድል ሲመለስ ሀዋሳ ከተማ በበኩሉ ዳግም ከሜዳው ውጪ ሶስት ነጥብ ማሳካት ሳይችል ቀርቷል፡፡
ኤሌክትሪክ በአዳማ ከተማ 6-1 በሆነ ሰፊ ውጤት ከተሸነፈው ቡድኑ ውስጥ ግርማ በቀለ፣ ሄኖክ ካሳሁን እና ኮትዲቯራዊው ዲዲዬ ለብሪን ከመጀመርያ 11 አስወጥቶ በጥላሁን ወልዴ፣ ሃይሌ እሸቱ እና በውድድር ዓመቱ ለመጀመርያ ጊዜ የተሰለፈው ወልደአማኑኤል ጌቱን ቀይሮ ወደ ሜዳ ገብቷል፡፡ ሀዋሳ ከተማ በበኩሉ በሩድዋ ደርቢ ከሲዳማ ቡና ጋር 1-1 ከተለያየበት ጨዋታ ላይ በቅጣት ላይ የሚገኘው ግብ ጠባቂው ሜንሳ ሶሆሆ፣ ሙሉዓለም ረጋሳ፣ መሐመድ ሲይላ እና ጋብርኤል አህመድን በአላዛር መርኔ፣ አስጨናቂ ሉቃስ፣ ፍቅረየሱስ ተወልድብርሃን እና ዳዊት ፍቃዱ ተክቶ ለጨዋታው ቀርቧል፡፡ ኤሌክትሪክ ከዘንድሮው የውድድር ዘመን ባልተለመደ መልኩ በሁለት አጥቂዎች ሲጫወት የሀዋሳን የፊት መስመር እስራኤል እሸቱ እና ዳዊት ፍቃዱ መርተዋል፡፡
የጨዋታው መጀመሪያ ላይ ባለሜዳዎቹ ጫና ፈጥረው በመጫወት በኩል ከእንግዶቹ ይሻሉ ነበር፡፡ በተለይ ከቀኝ መስመር በኩል ከአወት ገብረሚካኤል እና ጥላሁን ወልዴ በኩል የሚነሱ ኳሶች ዋነኛ የማጥቂያ መሳሪያዎቻቸው ነበሩ፡፡ ሆኖም ይህ ጫና መቀጠል ሳይችል ሀዋሳዎች ወደ ጨዋታው ምት መግባት የሚችሉበትን እድል ተፈጥሯል፡፡ በሀዋሳ በኩል ቁልፍ የማጥቂያ መሳሪያ የነበሩት እስራኤል እና ዳዊት ነበሩ፡፡ ጋናዊው አማካይ ካሉሻ አልሃሰን በ14ኛው ደቂቃ ከሳጥኑ ውጪ አክርሮ የመታውን ኳስ ወደ ውጪ ሲወጣበት ከአራት ደቂቃዎች በኃላ በኤሌክትሪክ የቀኝ መስመር ሰብሮ ወደ አደጋ ክልሉ የገባው እስራኤል የመታው ኳስ በተከላካዮች ተጨርፋ ወደ ውጪ ወጥታለች፡፡ በ19ኛው ደቂቃ ሀዋሳዎች መሪ መሆን የሚችሉበትን እድል ታፈሰ ሰለሞን አግኝቶ ሳይጠቀምበት ቀርቷል፡፡ ከመሃል በረጅሙ የተላከውን ኳስ ወልደአማኑኤል በግንባሩ ጨርፎ ለማውጣት ሲሞክር ታፈሰ አግቶ በግብ ጠባቂው ሱሌማና አቡ አናት ላይ ቢያሳልፍም ኳስ ወደ ላይ ተነስታ ወጥታለች፡፡ በ23ኛው ደቂቃ ከካሉሻ የተላከለትን ተከላካይ ሰንጣቂ ኳስ ታፈሰ ተስፋዬ አግኝቶ ሳይጠቀምበት ቀርቷል፡፡
ባለሜዳዎቹ የአምበላቸው አዲስ ነጋሽ መጎዳት ተከትሎ ግርማ በቀለን ወደ ሜዳ ቀይረው አስገብተዋል፡፡ ይህም ቅያሪ ይበልጥ ሀዋሳዎችን የመሃል ሜዳ ብልጫ እንዲገኙ ሲረዳ ኤሌክትሪኮች የመሃል ክፍል የተከላካይ መስመር ይበልጥ እንዲጠጋ እና ከአጥቂ ክፍሉ ጋር ያለው ርቀት እንዲሰፋ አድርጎታል፡፡ ከግራ መስመር እየተነሳ ሲያጠቃ የነበረው ዳዊት በሁለት አጋጣሚዎች የግብ ማግባት ሙከራ ያደረገውም ከአዲስ ጉዳት በኃላ ነው፡፡ በ33ኛው ደቂቃ የሀዋሳው ግብ ጠባቂ አላዛር ኳስን ለማራቅ በሚሞክርበት ወቅት በበኃይሉ ተሻገር ተቀምቶ አማካዩ ግብ ማስቆጠር ካልቻለበት እድል ውጪ ኤሌክትሪኮች ሌላ የግብ አጋጣሚ በአጋማሹ አልፈጠሩም፡፡ ነገር ግን ሀዋሳዎች በ39ኛው ደቂቃ መሪ ሊሆኑ የሚችሉበት አጋጣሚ ሲፈጠር የኤሌክትሪኩ ኃይሌ እሸቱ ኳስ በግንባሩ ለመራቅ ሲሞክር ራሱ ግብ ላይ ለማስቆጠር ቢቃረብም ተከላካዮች እንደምንም ከመስመር ላይ አድነውታል።
ከእረፍት መልስ የነበረው እንቅስቃሴ ግቦች የታዩበት ሲሆን ገና ጨዋታው በተጀመረ ሰከንዶች ውስጥ ኃይሌ ኳስን ወደ ሀዋሳ የግብ ክልል ገፍቶ ከገባ በኃላ ከፊቱ የነበረውን ተከላካይ በማለፍ ኳስ እና መረብ ማገናኘት ችሏል፡፡ መሪ መሆን የቻሉት ኤሌክትሪኮች በካሉሻ የቅጣት ምት ሙከራ የግብ ልዩነቱን በ48ኛው ደቂቃ ለማስፋት ተቃርበውም ነበር፡፡ ሀዋሳዎች የኳስ ቁጥጥር ብልጫን ቢወስዱም ተጭኖ በመጫወት እና የግብ እድሎችን በመፍጠር በኩል ከኤሌክትሪኮች የተሻሉ አልነበሩም፡፡ የሜዳው ምቹ አለመሆንም በአጨዋወታቸው ላይ ተፅዕኖው የጎላ ነበር። በ58ኛው ደቂቃ በኃይሉ ከቀኝ መስመር ለታፈሰ ለማቀበል ሲሞክር የሀዋሳ ተከላካዮች ያወጡበት እና በ62ኛው ደቂቃ አወት ያሻገረውን ኳስ አላዛር በአግባቡ መያዝ ባለመቻሉ በኃይሉ ሞክሮ አሁንም ተከላካዮች ያቋረጡበት እድሎች የኤሌክትሪክን ጫና ያመላከቱ ነበሩ፡፡ በ65ኛው ደቂቃ ፍሬው ሰለሞን ከቀኝ መስመር የሳጥኑ ጠርዝ የሞከረውን ሙከራ ሱሌማና ሲያመክንበት ከደቂቃ በኃላ ሄኖክ ድልቢ ከ20 ሜትር አክርሮ የመታው ኳስ ለጥቂት በግቡ አናት ወደ ውጪ ወጥቶበታል፡፡ ጨዋታው መቀዛቀዝ ባይታይበትም በሙከራ ረገድ አብዱልከሪም ሀሰን ያሻገረውን ኳስ የአሌክትሪክ ተከላካዮች ያወጡበት እንዲሁም የታፈሰ የግንባር ኳስ ወደ ውጪ የወጣበት በእንግዶቹ በኩል የሚጠቀስ ነው፡፡ በ82ኛው ደቂቃ ላይ አወት ያሻገረውን ኳስ ካሉሻ በግንባሩ ግጭቶ ግብ በማስቆጠር የኤሌክትሪክን ማሸነፍ ይበልጥ አስተማማኝ አድርጓል፡፡
ኤሌክትሪክ ነጥቡን ወደ 28 በማሳደግ አሁንም ወራጅ ቀጠናው ውስጥ 14ተኛ ደረጃን በመያዝ ለመቀመጥ ተገዷል፡፡ ሀዋሳ ከተማ በበሉሉ በ34 ነጥብ በደደቢት በግብ ክፍያ ተበልጦ 8ኛ ነው፡፡
የአሰልጣኞች አስተያየት
የኢትዮ-ኤሌክትሪክ ምክትል አሰልጣኝ ቦጋለ ዘውዴ
ወራጅ ቀጠና ውስጥ እንደመሆናችን መጠን ሶስት ነጥብ ያስፈልገን ነበር፤ ሶስት ነጥቡን አሳክተናል፡፡ አራት ጨዋታ ይቀረናል፡፡ ይህንን ውጤት አጠናክረን ለመቀጠል ነው ቡድናችን እየሰራ ያለው፡፡ ቡድናችን ይወጣል ይወድቃል ትንሽ ጨዋታዎች እልህ አስጨራሽ እና አስቸጋሪ ቢሆኑም፡፡ ያሉብንን ቀሪ ጨዋታዎች አሸንፈን ቡድኑን ለመታደግ ነው፡፡
የሀዋሳ ከተማ አሰልጣኝ ውበቱ አባተ
ጨዋታው ከእረፍት በፊት ጥሩ ነበር፡፡ የግብ እድሎችን እና አጋጣሚዎችን የተሻለ መፍጠር ችለን ነበር፡፡ እንደአጋጣሚ ሆኖ ግብ ማስቆጠር አልቻልንም፡፡ ከእረፍት በኃላ ደግሞ አንድ ደቂቃ ሳይሞላ ተቆጠረብን፡፡ ከዛ በኃላም ተጭነን ለመጫወት ነው ሙከራ ያደረግነው፡፡ በመልሶ ማጥቃት እየመጡ እድሎችን ይፈጥሩ ነበር፡፡ ግብ ካላስቆርክ ማሸነፍ አትችልም፡፡ እነሱ ያገኟቸውን አጋጣሚዎች ተጠቅመው አሸንፈዋል፡፡