ሪፖርት | የዮሴፍ ዮሀንስ ድንቅ ግብ ለሲዳማ ቡና ሶስት ነጥብ አስጨብጣለች

በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 26ኛው ሳምንት በእኩል 29 ነጥቦች የወራጅ ቀጠናው አፋፍ ላይ የተገኙት ሲዳማ ቡና እና ድሬዳዋ ከተማን ያገናኘው ጨዋታ ሀዋሳ ዓለም አቀፍ ስታድየም ላይ ተካሂዶ ሲዳማ ቡና 1-0 በሆነ ውጤት አሸንፏል።

ሲዳማ ብሔረሰብ በድምቀት የሚከበረው የፍቼ ጨምበላላ በዓልን አስመልክቶ ሲዳማ ቡና ጨዋታው ከይርጋለም ወደ ሀዋሳ እንዲዞር ለኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌድሬሽን ባቀረቡት ጥያቄ መሰረት ሀዋሳ ዓለም አቀፍ ስታድየም ላይ ተከናውኗል።

ባሳለፍነው ሳምንት አርብ ፌዴሬሽኑ በ24ኛው ሳምንት ሲዳማ ቡና አዳማ ከተማን በረታበት ጨዋታ አዲስ ግደይ 5 ቢጫ እያለበት ተሰልፏል በሚል ሲዳማ ላይ የፎርፌ ውሳኔን ማሳለፉን ተከትሎ ክለቡ ለዚህ ስህተት ተጠያቂ ያደረጋቸው ምክትል ካሳሁን ገብሬን አሰናብቶ በምትኩ የ20 አመት በታች ቡድን አሰልጣኙ ስንታየውን በመሾም ለዛሬው ጨዋታ ሲቀርብ በድሬዳዋ በኩል ከጨዋታው አስቀድሞ ሲዳማ ቡናዎች ለእንግዳ ቡድን ማድረግ የነበረባቸውን ትብብር አላደረጉልንም በሚል ያነሷቸው ጥያቄዎች ከጨዋታው መጀመር አስቀድሞ ትኩረት ያገኙ ጉዳዮች ነበሩ።

ሲዳማ ቡናዎች በ25ኛው ሳምንት ከሀዋሳ ነጥብ ከተጋራው ስብስብ መካከል አዲስ ግደይን በአዲሱ ተስፋዬ፣ በተመሳሳይ ቅጣት ላይ ባለው ወንድሜነህ አይናለም ምትክ አዲስዓለም ደበበን በማስገባት በ 3-4-3 አሰላለፍ ወደሜዳ ሲገቡ ድሬዎች በሜዳቸው መቐለ ከተማን ከረታው ስብስባቸው መካከል በአትራም ኩዋሜ እና ሱራፌል ዳንኤል ምትክ ለሳውሬል ኦልሪሽ እና ዘነበ ከበደ እድል በመስጠት በ4-4-2 አሰላለፍ ወደ ሜዳ ገብተዋል።

በኢትዮጵያ ህዝብ መዝሙር ታጅቦ ከተያዘለት ሰዓት 10 ደቂቃዎች ዘግይቶ የጀመረው ጨዋታው በበርካታ ተመልካች ቢታጀብም የተጫዋቾች እልህ መጋባት፣ ሽኩቻ እና ውበት አልባ እንቅስቃሴ የጨዋታው መልኮች ነበሩ። ሲዳማ ቡናዎች በመስመር ላይ ያጋደለ እና በሐብታሙ ገዛኸኝ ላይ ማዕከል ያደረገ ፈጣን የማጥቃት እንቅስቃሴ ሲያደርጉ ድሬዎችም በተመሳሳይ ከመስመር በሚነሱ ኳሶች የግብ እድል ለመፍጠር ሞክረዋል። 4ኛ ደቂቃ ላይ ትርታዬ ደመቀ በቀኝ የድሬዳዋ የግብ ክልል ያሻገረውን ኳስ ወጣቱ የመስመር ተጫዋቾች አዲሱ ተስፋዬ አክርሮ መትሎ ሳምሶን አሰፋ በአስደናቂ ሁኔታ ያወጣበት የእለቱ ቀዳሚዋ እድል ነበረች። ከአራት ደቂቃዎች በኋላ ከማዕዘን ምት የተሻማችውን ኳስ ባዬ ገዛኸኝ አግኝቷት ሳይጠቀምባት የቀረችው ሌላኛዋ ተጠቃሽ ሙከራ ነበረች።
ጨዋታው 15 ደቂቃዎች ከተቆጠረ በኋላ በርከት ያሉ የኃይል አጨዋወትን ያየንበት እና የተጫዋቾች ዕርስ በእርስ ሽኩቻ እና አሳማኝ የዳኝነት ውሳኔን ያልተመለከትንበት ነበር። ለዚህም ማሳያ 18ኛው ደቂቃ ላይ ዮሴፍ ዳሙዬ በአበበ ጥላሁን ላይ በሰራው ጥፋት ዳኛው በፊሽካ ካስቆሙ በኃላ የፈጠሩት የሁለቱ ተጫዋቾች ሰጣ ገባ እና የሌሎች ተጫዋቾች ግብ ግብ የእለቱ ዳኛ አንድም የማስጠንቀቂያ ካርድ ሳያሳዩ መቅረታቸው ነው። ለቀጣይ ደቂቃዎች የረባ እነረቅስቃሴ ባልታየበት ጨዋታ 26ኛው ደቂቃ ላይ አዲስዓለም ደበበ ከርቀት የተሰጠውን ቅጣት ምት ወደ ግብ መትቶ ሳምሶን አሰፋ በግሩም ሁኔታ አውጥቶበታል ፡፡ 29ኛው ደቂቃ ላይ ደግሞ ከመስመር ወደ ውስጥ እየገባ በልዩነት ድንቅ አቀሙን ሲያሳየን የነበረው ሐብታሙ ገዛኸኝ እየገፋ ገብቶ ከሳምሶን አሰፋ ጋር አንድ ለአንድ ተገናኝቶ የመታትን አልቀመስ ብሎ የዋለው ሳምሶን አድኖበታል። ከሁለት ደቂቃ በኃላ ባዬ ገዛኸኝ ያሳለፈለትን ኳስ አዲሱ ተስፋዬ በግብ ክልል ውስጥ አግኝቶ ሲመታት ሳምሶን በድጋሚ አውጥቶበታል። 35ኛ ደቂቃ ላይ ግን ሲዳማን ወደ ድል የመራች ግብ የተቆጠረችበት ነበረች። ዮሴፍ ዮሀንስ ከባዬ የተቀበለውን ኳስ በግምት 30 ሜትር ርቀት ላይ አክርሮ በመምታት ለሳምሶን አሰፋ ኳሷን የማዳን እርምጃ ለመውሰድ እድል ሳይሰጥ በድንቅ ሁኔታ አስቆጥሯል።


ሁለተኛው አጋማሽ ሲጀምር ድሬዎች ሳውሬል ኦልሪሽን አስወጥተው አትራም ኩዋሜን ያስገቡ ሲሆን ዘላለም ኢሳያስንም በወጣቱ አማካይ ያሬድ ታደሰ ተክተዋል። ሲዳማ ቡናዎች ደግሞ አዲስአለም ደበበን በወንድሜነህ ዘሪሁን ፣ ባዬ ገዛኸኝን በይገዙ ቦጋለ እንዲሁም አዲሱ ተስፋዬን በሙጃይድ መሀመድ ለውጠው ነበር። ድሬዎች አሰላለፋቸውን ወደ 4-3-3 ቀይረው ጋናዊው አትራም ኩዋሜ ከገባበት ሰዐት ጀምሮ ከኢማኑኤል ላርዬ ጋር እየተጣመረ በጥልቀት ሳጥን ውስጥ ለመግባት ጥረቶችን አድርጓል። ሲዳማ ቡናዎች አሁንም መሠረታቸውን ወደ መስመር አድርገው ሀብታሙ ገዛኸኝን ማዕከል ያደረጉ እንቅስቃሴወችን ማድረግ መርጠዋል። 47ኛው ደቂቃ ላይ ዮሴፍ ዮሀንስ በረጅሙ ከመሀል ሜዳ ካሻገረለትን ኳስ ባይ ገዛኸኝ ከሳምሶን አሰፋ ጋር ፊት ለፊት ተገናኝቶ ሳምሶን የመለሰበት ሲሆን 53ኛው ደቂቃ ላይ ደግሞ አዲስአለም ደበበ ለአዲሱ ተስፋዬ ሰጥቶት አዲሱ ወደ ግብ በቀጥታ ሲሞክር የውስጥ ብረት መልሶበታል፡፡
ከድሬዳዋ በተሻለ መልኩ ወደ ግብ መቅረብ የቻሉት ሲዳማዎች ጥረታቸውን ቀጥለው 65ኛው ደቂቃ ላይ በተለየ መልኩ ብቃቱን ሲያሳይ የነበረው ሀብታሙ ገዛኸኝ በቀኝ በኩል ወደ ሳጥኑ እየገፋ ገብቶ የመታውን ሳምሶን ሲመልስበት አዲሱ ተስፋዬ በድጋሜ ሞክሮ ወደ ውጭ ወጥቶበታል። የመጨረሻወቹ 5 ደቂቃዎች ላይ ብልጫ የነበራቸው ድሬዳዋዎች ጫና  ፈጥረው ቢጫወቱም ግብ  ማስቆጠር ግን አልቻሉም። በተለይ አትራም ኩዋሜ  በግል ጥረቱ እየገፋ ወደ ሳጥን በተደጋጋሚ የሚገባበት ሂደት ተጠቃሽ ነበር። አትራም ኩዋሜ በድሬዳዋ ብቸኛ የጨዋታው ለግብ የቀረበች ዕድል 89ኛው ደቂቃ ላይ በግራ በኩል ያሻገረው ኳስ በግቡ ትይዩ ለነበረው ዮሴፍ ዳሙዬ ቢደርስም በእግሩ ስር ሾልኮበታል። በሌላ አጋጣሚ ድሬዎች ወሰኑ ማዜ ወደ ግብ ክልል በላከው ኳስ ሌላ ዕድል ቢፈጥሩም ወጣቱ ተከላካይ ዮናታን ፍሰሀ ተንሸራቶ አውጥቶበታል። ጨዋታውም በሲዳማ ቡና 1-0 አሸናፊነት ተጠናቋል፡፡ ከጨዋታው መጠናቀቅ በኃላ በይርጋለም እንደምናስተውለው ሁሉ በተመሳሳይ ሁኔታ የደጋፊዎች ወደ ሜዳ ገብተው ለተቃራኒ ቡድኖች እና ዳኞች ስጋት ሲሆኑ የሚታይበት ሁኔታ ዛሬም ተደግሟል።

የአሰልጣኞች አስተያየት

ዘርዓይ ሙሉ –  ሲዳማ ቡና

ጨዋታው ብዙ ነገር የነበረው ነው። ምክንያቱም ሶስት ነጥብ ተቀንሶብን ስለነበር በስነ-ልቦና ረገድ በተጫዋቾቹ ላይ ብዙ ስራ ሰርተን ነው ለጨዋታው የቀረብነው። በአሁኑ ሰዓት ነጥብ ሲቀነስብህ ከባድ ነው። አዲስ ግደይ ደግሞ አንዴ ከተቀጣ በኃላ በድጋሚ ቅጣት ዛሬም አለመኖሩ ቡድኑን አሁንም በስነ ልቦናው ጎድቶት ነበር። ዞሮ ዞሮ እዛ ላይ ጥሩ ነገር በመስራታችን በጥሩ ብልጫ እና እንቅስቃሴ አሸንፈን ወጥተናል፡፡

ስምዖን ዓባይ – ድሬዳዋ ከተማ

ጨዋታውን ምን ብዬ እንደምገልፅ አላውቅም። ብዙ ተፅእኖ ውስጥ ሆነን ነው የተጫወትነው። እግር ኳስ ደሞ እንደዚህ ከሆነ በጣም ያሳዝነኛል። አንደኛ እግር ኳሳችን ያለበትን ደረጃ እናውቀዋለን፤ ሲቀጥል በእንደዚህ አይነት አካሄድ ከሄድን ደረጃችን አሁንም እንደገና ወደ ኋላ..። በኔ እምነት ዛሬ ቡድኔ ተበልጦ አይደለም የተሸነፈው። 11 ለ 12 ሆነን ስለተጫወትን ነው፤ በዳኝነቱ ላይ ችግር ነበር። ምንም ቡድኔ የተበለጠው ነገር የለም። እርግጥ ከዕየእረፍት በፊት የነሱ ጫና ነበረው። ከእረፍት በኃላ ግን የተሻለ ሆነን ቀርበናል። ቢሆንም ግን በርግጠኝነት የምነግራችሁ 12 ለ 11 ሆነን ነው የተጫወትነው። ከዚህ በፊት ስለዳኛ አውርቼ አላቅም የዛሬው ግን አሳሳቢ ዳኝነት ያየንበት ነበር። ከጨዋታው በፊት የሜዳም ሆነ የመስተንግዶ ችግር ገጥሞናል። ተጋጣሚያችን አልተባበረንም፤ ይህም አሳዝኖኛል፡፡