በ26ኛው ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ዓዲግራት ላይ ደደቢትን ያስተናገደው ወልዋሎ ዓዲግራት ዩኒቨርሲቲ 1-0 በማሸነፍ ከ ወራጅ ቀጠናው ለማምለጥ የሚያደርገውን ጥረት አጠናክሯል።
ወልዋሎ በ25ኛው ሳምንት ወልዲያን ካሸነፈው ስብስብ በማናዬ ፋንቱ ምትክ አብዱራህማን ፉሴይኒን ወደ መጀመርያ አሰላለፉ ሲመልስ ደደቢት በ24ኛው ሳምንት ከኢትዮጵያ ቡና ጋር አቻ ከተለያየው ስብስቡ መካከል ታሪክ ጌትነት እና ቅጣት ላይ የሚገኘው ኩዌኩ አንዶህን በማሳረፍ አማራህ ክሌመንት እና የዓብስራ ተስፋዬ ወደ መጀመርያ አሰላለፍ ተመልሰዋል።
ከጨዋታው መጀመር አስቀድሞ ባለፈው ሳምንት በድንገተኛ ህመም ህይወታቸውን ላጡት የደደቢት አሰልጣኝ ንጉሴ ደስታ የ1 ደቂቃ የህሊና ፀሎት የተደረገ ሲሆን በዝናብ ታጅቦ በጀመረው ጨዋታ ወልዋሎዎች ተጭኖ በመጫወት መልካም አጀማመር ቢያደርጉም በማጥቃት ወረዳው የነበራቸው ስኬታማነት ዝቅተኛ ነበር። በ2ኛው ደቂቃ ጋናዊው ሪችሞንድ አዶንጎ ባደረገው ሙከራ የደደቢትን ግብ መፈተሽ የጀመሩት ባለሜዳዎቹ ብዙም ሳይቆዩ በ4ኛው ደቂቃ ፕሪንስ ሰቨሪንሆ አክርሮ በመታው ኳስ ሙከራ አድርገው ክሌመንት አድኖታል።
በ4-4-2 አሰላለፍ ወደ ሜዳ የገቡት ደደቢቶች ከአራቱ ተከላካዮች ፊት የተሰለፉት ሽመክት፣ አስራት፣ የዓብስራ እና ኤፍሬም በመሃል ሜዳ በነበራቸው ያለመናበብ እና የተዘበራረቀ አደራደር ቡድኑ መረጋገት ሲያሳጣው ተስተውሏል። ከዚ በተጨማሪም እስከ 15ኛው ደቂቃ ድረስ የዘነበው ዝናብ የፈጠረው ጭቃ በጨዋታው ሌላ ከባድ ፈተና ነበር። ሆኖም ቀስ በቀስ ወደ ጨዋታው ሪትም በመግባት ጫና መፍጠር የቻሉ ሲሆን ወልዋሎዎች የተከላካይ ክፍላቸው ወደ መሃል ሜዳ በማስጠጋት ለደደቢቶች በቂ የመጫወቻ ቦታ በማሳጣት ከኳስ ውጭ አላስፈላጊ ሩጫዎች እንዳያረጉ ቢረዳቸውም ደደቢቶች ከወልዋሎ ተከላካዮች ጀርባ የሚፈጠሩ ሰፊ ክፍተቶችን ለመጠቀም ሲያደርጉት የነበረው ጥረት የግብ እድሎችን አስገኝቶላቸዋል። ኄኖክ መርሹ በረጅሙ ያሻገረውን ጌታነህ በግንባሩ በመግጨት ለአቤል አመቻችቶለት አቤል በግብ ጠባቂው አናት አሳልፎ የግቡን ብረት ገጭታ ስትወጣ ብዙም ሳይቆይ በተመሳሳይ መንገድ አስራት መገርሳ በግሩም ሁኔታ ያሻገረለት ኳስ አቤል ያለው ከዮሃንስ ጋር 1ለ1 ተገናኝቶ ቢመታም ዮሀንስ ሽኩር በሚያስደንቅ ሁኔታ መልሶታል። ደደቢቶች በጨዋታው እንደነበራቸው ማንሰራራት በመሀል ሜዳ የያብስራ እና አስራት የተገደበ እንቅስቃሴ ቡድኑ በመሃል ሜዳ የሚፈልገውን ፈጠራ ከማሳጣቱ ባለፈ የቡድኑ የማጥቃት አጨዋወት በሁለቱ የመስመር አማካዮች ሽመክት እና ኤፍሬም ላይ የተንጠለጠለ አድርጎታል። በዚህም አጥቂው ጌታነህ ከበደ ወደ ኋላ እየተመለሰ ከአማካዮች ጋር ለመገናኘት ጥረት ቢያደርግም ስኬታማ አልነበረም።
በፈጣን የማጥቃት ሽግግር አብዱልራህማን ፉሴይኒ በተሰለፈበት የግራ መስመር የደደቢትን የኋላ መስመር ማስጨነቅ የቻሉት ወልዋሎዎች በጨዋታው ከደደቢት በተሻለ የጎል እድል ቢፈጥሩም ሁነኛ የሳጥን ውስጥ አጥቂ ባለመያዛቸው እንዲቸገሩ ቢያደርጋቸውም በ28ኛው ደቂቃ ላይ ከመስመር የተሻገረለትን ኳስ ነፃ አቋቋም ላይ የነበረው አምበሉ በረከት ተሰማ በግንባሩ በመግጨት ወልዋሎን መሪ ማድረግ ችሏል። ከጎሏ መቆጠር በኋላ ወልዋሎዎች ኳስን በራሳቸው ሜዳ በማንሸራሸር እንዲሁም ግጭቶችን ተከትለው በሚሰጡ የተንዛዙ የህክምና እርዳታዎች እና ቅጣት ምቶች እየተቆራረጠ የመጀመርያው አጋማሽ በወልዋሎ መሪነት ተገባዷል። በእረፍት ሰዓትም ወልዋሎዎች የደደቢቱ አጥቂ አቤል ያለው 5 ቢጫ እያለበት ተሰልፏል በሚል የተገቢነት ክስ አስመዝግበዋል።
ሁለተኛው አጋማሽ የሜዳው ጭቃማነት በመቀነሱ ከመጀመርያው አጋማሽ የተሻለ እንቅስቃሴ ይታይበታል ተብሎ ቢጠበቅም በተቃራኒው ኢላማቸው ባልጠበቁ ሙከራዎች እና በሜዳ ላይ ውዝግቦች የታጀበ ነበር። ከዕረፍት መልስ ደደቢቶች ኤፍሬም አሻሞን በአቤል እንዳለ በመቀየር አቤል እና ሽመክት ወደ መሃል እያጠበቡ እንዲጫወቱ በማድረጋቸው የመስመር ተከላካዮቹ ከ መጀመርያው አጋማሽ በተሻለ በማጥቃቱ የማጥቃት ተሳትፎን አድርገዋል። በዚህ ሂደትም ስዩም በረጅሙ ለአቤል አሳልፎለት አቤል በግንባሩ ገጭቶ ከግቡ አናት ለጥቂት ወጥታበታለች። በ49ኛው ከዓለምነህ ግርማ በረጅሙ የተሻገረውን ኳስ አብዱራህማን በግንባሩ ገጭቶ ኢላማዋን ሳትጠብቅ በወጣችው ኳስ የሁለተኛ አጋማሽ የመጀመርያ ሙከራ ማድረግ የቻሉት ወልዋሎዎች የደደቢት የመስመር ተከላካዮች ለማጥቃት ትተውት በሚሄዱት ክፍተት ለመጠቀም ሞክረዋል። በተለይም እንየው ካሳሁን ያሳየው እንቅስቃሴ የሚደነቅ ነበር። አማካዩ ዋለልኝ ገብሬ ከሳጥኑ ጠርዝ በግሩም ሁኔታ የመታትና ክሌመንት በአስደናቂ ብቃት ያዳናት ኳስም የምጠቀስ ሙከራ ነበረች።
ሽኩቻ እና አወዛጋቢ የዳኝነት ውሳኔዎች በታየበት የመጨረሻዎቹ 15 ደቂቃዎች አስራት መገርሳ በሰራው ጥፋት የውድድር ዓመቱን ሁለተኛ ቀይ ካርድ ተመልክቶ ከሜዳ ተሰናብቷል። ከቀይ ካርዱ ውሳኔ በኋላ በነበረው መጠነኛ አለመግባባት መልኩ ከመቀየሩ በፊት የሁለቱም ቡድን መሪዎች ለማረጋጋት የወሰዱት እርምጃ በመልካምነቱ የሚነሳ ነበር። በመጨረሻዎቹ 10 ደቂቃች በነበረው እንቅስቃሴ እንግዶቹ ሙሉ ብልጫ ቢኖራቸውም ደስታ ደሙ ከርቀት መትቶ እንየው ተደርቦ ካወጣት ሙከራ ውጭ የሚጠቀስ ሙከራ ሳያደርጉ ጨዋታው በወልዋሎ 1-0 አሸናፊነት ተጠናቋል።