ፕሪምየር ሊግ | የ26ኛ ሳምንት ጨዋታዎች ቅድመ ዳሰሳ – ክፍል 3

ትናንት ስድስት ጨዋታዎችን ያስተናገደው የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 26ኛ ሳምንት ዛሬ በአዲስ አበባ ስታድየም በሚቀጥሉ ሁለት ጨዋታዎች ፍፃሜውን ያገኛል። የሳምንቱ ቅድመ ዳሰሳችን የመጫረሻ ክፍልም እነዚሁ ጨዋታዎች ሆነዋል።

መከላከያ ከ ጅማ አባ ጅፋር

ከዚህ ጨዋታ የሚገኙት ሶስት ነጥቦች ውድነት ለእንግዶቹ ጅማ አባ ጅፋሮች ያመዝናሉ። ከቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር አቻ ከተለያየበት በውዝግብ ከተገባደደው ጨዋታ በኃላ ወደ መዲናዋ የሚመጣው አባ ጅፋር አሁን በ42 ነጥቦች አራተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል። መከላከያን ማሸነፍ ደግሞ ከቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር ለመስተካከል ብሎም በግብ ክፍያ በልጦ በድጋሜ በሊጉ አናት ለመቀመጥ የሚችልበትን በር ይከፍትለታል። ይህ ሲታሰብ የአሰልጣኝ ገብረመድህን ኅይሌ ቡድን ለጨዋታው የሚሰጠው ትኩረት ከፍተኛነት ግልፅ ሆኖ ይታያል። በ32 ነጥቦች 9ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጠው መከላከያ በበኩሉ ድል ማድረግ ወደ 6ኛነት ከፍ ያደርገዋል። ይህም በዘንድሮው የውድድር አመት ለመጀመሪያ ጊዜ ከላይኞቹ ስድስት ቡድኖች መሀከል መቀላቀልን ያስችለዋል። ከወራጅ ቀጠናው ያለውን የነጥብ ልዩነትም ከአራት ወደ ሰባት በማሳደግ ራሱን ከስጋት ነፃ ማድረግ የሚችልበት ዕድል ይፈጠርለታል። 

መከላከያ የረጅም ጊዜ ጉዳት ላይ ከሚገኘው ቴዎድሮስ በቀለ በተጨማሪ አወል አብደላን በጉዳት ሲያጣ ዳዊት እስጢፋኖስ እና አዲሱ ተስፋዬ ደግሞ በቅጣት ከዛሬው ጨዋታ ውጪ ናቸው። በጅማ አባ ጅፋር በኩል የቅጣት ዜና ባይኖርም ኄኖክ ኢሳያስ እና ቢኒያም ሲራጅ ጉዳት ላይ ሲሆኑ የአዳማ ሲሴኮ መግባትም አጠራጣሪ ሆኗል።

የትናንትናዎቹ ሶስት የአዲስ አበባ ጨዋታዎች ለተመለከተ እና የሜዳውን ሁኔታ ላጤነ ሰው የመሀል ሜዳ ሽኩቻዎች ማሸነፍ እና እስከመጨረሻው ያለድካም የመጫወት ብቃት ያለውን ዋጋ መረዳት ይችላል። እዚህ ጨዋታ ላይም ተመሳሳይ የበላይነት የሚኖረው ቡድን ጨዋታውን በአሸናፊነት ለመወጣት ዕድሉ የሰፋ ነው። ከጅማ በኩል እንደ ይሁን እንዳሻው እና አሚኑ ነስሩ በመከላካያ በኩል ደግሞ እንደ በሀይሉ ግርማ እና አማኑኤል ተሾመ አይነት ጉልበታም የሆኑ የጨዋቾች መሀል ላይ የሚገናኑባቸው ፍልሚያዎች በጨዋታ ላይ የሚፈጥሩት ልዩነት ከፍተኛ ይሆናል። በተለይም ወደ ፊት ለአጥቂዎች የሚጥሏቸው ረጃጅም ኳሶች ምጣኔ ትርፍ ሊያስገኙላቸው ይችላሉ። 

የቡድኖቹ ፊት አውራሪዎች ኦኪኪ አፎላቢ እና ፍፁም ገብረማርያም የሜዳውን አስቸጋሪነት ተቋቁመው ከተጋጣሚዎቻቸው ተከላካዮች ጋር የሚኖሩ ፍልሚያዎችን ማንነፍን ይጠበቅባቸዋል። በኃላ መስመር ተሰላፊዎች ላይ ጫና ማሳደርም በተመሳሳይ ከቡድኖቹ የፊት መስመሮች ተሰላፊዎች እንቅስቃሴ ውስጥ ሌላው ተጠባቂ ጉዳይ ነው። ለመልሶ ማጥቃት በተመቸው ጅማ አባ ጅፋር በኩል ወደ ማጥቃት በሚደረገው ሽግግር ከመስመር አማካዮቹ እና ከሁለተውኛ አጥቂ ተመስገን ገብረኪዳን የሚነሱ ኳሶች አደጋ የመፍጠር ዕድላውቸ ሰፊ ነው። መሀል ሜዳ ላይ የቁጥር ብልጫ የሚኖራቸው መከላያይዎችም አጥብበው በሚጫወትቱ የመስመር አማካዮቻቸው እንዲሁም ማቅቃቱን በረጃጅም ኳሶቻቸው በሚያግዙት የመስመር ተከላካዮቻቸው እንቅስቃሴዎች ዕድሎችን ለመፍጠር እንደሚሞክሩ ይገመልታል።

የእርስ በእርስ ግንኙነት እና እውነታዎች

– የፕሪምየር ሊጉ የመጀመሪያ ግንኙነታቸው በነበረው የ11ኛው ሳምንት የጅማው ጨዋታ 1-1 ተለያይተዋል።

– ጅማ አባ ጅፋር ወደ አዲስ አበባ ስታድየም በመምጣት ካደረጋቸው አራት ጨዋታዎች አንድ ጊዜ ሽንፈት አንድ ጊዜ ደግሞ ድል ሲያስመዘግብ በሁለት ጨዋታዎች ነጥብ ተጋርቷል።

– መከላከያ ዘንድሮ በ9 አጋጣሚዎች የክልል ቡድኖችን ያስተናገደ ሲሆን ሁለቴ ተሸንፎ ሶስቴ ነጥብ ሲጋራ አራት ጊዜ ደግሞ ድል ቀንቶታል። ከነዚህ ድሎቹ መሀከል ሶስቱ በመጨረሻ ጨዋታዎቹ የተገኙ ነበሩ።

ዳኛ

– ፌደራል ዳኛ ማኑኤ ወልደፃዲቅ ጨዋታውን በመሀል ዳኝነት እንደሚመራው ይጠበቃል።

ኢትዮጵያ ቡና ከአዳማ ከተማ

ይህን 26ኛው ሳምንት የመጨረሻ ጨዋታ በብዙ መልኩ እንድንጠብቀው ያደርገናል። ባለፉት አመታት ግንኙነታቸው ያስተናገደው ፉክክር እንዳለ ሆኖ የቡድኖቹ አቋም ከምንም በላይ ደግሞ ጨዋታው በሊጉ ፉክክር ላይ የሚያመጣው ልዩነት ትኩረትን እንዲስብ አስገድዷል። ከሸገር ደርቢ ሽንፈት በኃላ በአራት ጨዋታዎች 8 ነጥቦችን የሰበሰበው ኢትዮጵያ ቡና በሁለተኛው ዙር የታየበት መሻሻል ኮስታራ የዋንጫ ተፎካካሪ አድርጎታል። በተለይ ሳምንት ከሶዶ ይዞ የተመለሳቸው ሶስት ነጥቦች በእጅጉ ጠቅመውታል። ዛሬ ሙሉ ነጥቦች ካገኘም ቅዱስ ጊዮርጊስን በሁለት ነጥቦች ርቀት የመከተል ዕድል ይኖረዋል።  ባገኘው ድንገተኛ የፎርፌ ውሳኔ እስከትናንት ድረስ ሊጉን መምራት ችሎ የነበረው አዳማ ኢትዮ ኤሌክትሪክ ላይ ግማሽ ደርዘን ግቦች ካዘነበበት የውድድር ሳምንት በኃላ ነው ወደዚህ ጨዋታ የሚመጣው። ይህን ጨዋታ በማንኛውም ውጤት ቢያሸንፍም ወደ መሪነቱ ዳግም የሚመለስ ይሆናል። 

ኢትዮጽያ ቡና ከተከላካዩ አክሊሉ አያናው ጉዳት በቀር ሙሉ ስብስቡ ለጨዋታው ዝግጁ ሲሆን ዳዋ ሁቴሳ ከቅጣት የሚመለስለት አዳማም ያለ ጉዳት እና ቅጣት ዜና ለዛሬው ጨዋታ ደርሷል።

ቡድኖቹ ከያዟቸው ተጨዋቾች የቴክኒክ ብቃት አንፃር ጨዋታው በደረቅ ሜዳ ላይ የሚካሄድ ቢሆን ጥሩ የኳስ ፍሰት እና በርካታ ሙከራዎችን ሊያስመለክተን ይችል ነበር። ሆኖም የአዲስ አበባ ስታድየም ወቅታዊ ሁኔታ ነገሮችን በቴክኒኩ ከፍ ላሉ ተጨዋቾች አስቸጋሪ ሊያደርግባቸው ይችላል። በአመዛኙ የአማካይ ክፍላቸው   እንቅስቅሴ ላይ የሚመረኮዙት ሁለቱ ቡድኖች ደጋግመው ከማጥቃት ወደ ኃላ የማይሉ የመስመር ተከላካዮችን መያዛቸው ደግሞ በሁለቱ ኮሪደሮች ላይ የሚጠበቁትን ፍልሚያዎች ወሳኝነት ክፍ ያደርገዋል። አራቱ የመስመር ተከላካዮች በሽግግሮች ወቅት ከሳሙኤል ሳኑሚ እና ሚኪያስ መኮንን እንዲሁም ከሱራፌል ዳኛቸው እና በረከት ደስታ ጋር የሚገናኙባቸው ቅፅበቶችም የመጨረሻ የግብ ዕድሎችን የመፍጠር ዕድላቸው የሰፋ ነው። በተለይም በአንድ ለአንድ ግንኙነቶች ሳሙኤል ሳኑሚ ከሱለይማን መሀመድ እንዲሁም በረከት ደስታ ከሀይሌ ገ/ትንሳይ የሚኖራቸው ፉክክር በጣሙን አጓጊ ነው።

የአዳማ ከተማው ጫፉን ወደ ተጣጥሚው ግብ ያደረገው ሶስት ማዕዘናዊ የአማካይ ክፍል ጥምረት ጥሩ ውህደት ላይ ይገኛል። የአዲስ ህንፃ እና ኢስማኤል ሳንጋሪ ከተከላካዮች ፊት ያለ ጥምረት ነጣቂ እና የጥልቅ አማካይነት ሚናን በሚወወጡ ሁለቱ ተጨዋቾች ተጠቃሚ ሆኗል። ከፊታቸው በነፃነት የሚጫወተው ከንዓን ማርክነህ ደግሞ ሰፊ ሜዳን በማካለል ዕድሎችን ከመፍጠር ግቦችን እስከ ማስቆጠር ድረስ ስኬታማ ጊዜን እያሳለፈ ነው። በዚህ ጨዋታ በተከላካይ አማካይነት አስገራሚ ጊዜን እያሳለፈ ከሚገኘው አማኑኤል ዮሀንስ ጋር ሲገናኝ ምን ይፈጠራል የሚለው ደግሞ ከወዲሁ አጓጊ ይሆናል። የኢትዮጵያ ቡና የአጥቂ አማካዮች ጥምረት ተደጋጋሚ ለውጦች ሲደረግበት ቢታይም ካለው ልምድ አኳያ የሳንጋሪ እና አዲስ ህንፃን ጥምረት መፈተኑ የማይቀር ነው። በተለይ ቡድኑ ወደ ማጥቃት ሲሻገር እዚህ ቦታ ላይ ካሉ ተጨዋቾች ወደ መስመር አጥቂዎች የሚላኩት ኳሶች የቡድኑን ውጤት የመቀየር አቅሙ ያላቸው ናቸው። ከዚህ ውጪ ዳዋ ሁቴሳ እና ባቲስታዬ ፋዬ ወይም አቡበከር ነስሩ ከተጋጣሚያቸው የመሀል ተከላካዮች ጋር የሚያደርጉት ፍልሚያም ወሳኝነት የጎላ ነው። የክሪዚስቶም ንታንቢ እና የቶምስ ስምተቱ እንዲሁም የግዙፎቹ ሙጂብ ቃሲም እና ምኞት ደበበ የመሀል ተከላካይ መስመር ጥምረት የትኩረት ደረጃም በዚህ ጨዋት ይፈተናል።

የእርስ በእርስ ግንኙነት እና እውነታዎች

– ሁለቱ ቡድኖች 33 ጊዜ ተገናኝተው ኢትዮጵያ ቡና 18 ጊዜ በማሸነፍ የበላይነት ሲይዝ አዳማ ከተማ 6 ጊዜ አሸንፏል። በ9 አጋጣሚዎች አቻ ተለያይለዋል።

– 92 ጎሎችን ባስተናገደው የሁለቱ ቡድኖች የእርስ በእርስ ግንኙነት ኢትዮጵያ ቡና 61፣ አዳማ ከተማ 31 ጎሎችን አስቆጥረዋል። በ2002 ቡና 6-1 ያሸነፈበት ውጤትም ከፍተኛው ነው።

– አዲስ አበባ ላይ 17 ጊዜ ተገናኝተው ቡና በ13 ድል ሲያስመዘግብ አዳማ 2 አሸንፎ ሁለት ጊዜ አቻ ተለያይተዋል። የአዳማ ድሎች እና ሁለቱ አቻዎች የተገኙት ካለፉት 5 ጨዋታዎች ነው።

– አዳማ ከተማ ባለፉት ሶስት ተከታታይ የአዲስ አበባ ጨዋታዎች በቡና አልተሸነፈም።

ዳኛ

– ይህ ጨዋታ በኢንተርናሽናል ዳኛ ቴዎድሮስ ምትኩ መሪነት ይከናወናል።