ዛሬ በአዲስ አበባ ስታድየም ከተደረጉ ጨዋታዎች መሀከል በቅድሚያ የተከናወነው የጅማ አባ ጅፋር እና መከላከያ ጨዋታ በተመስገን ገ/ኪዳን ብቸኛ ግብ በእንግዶቹ አሸናፊነት ተጠናቋል።
ከ25ኛው ሳምንት አንፃር መከላከያ ጎንደር ላይ ባሳካው ድል ከተጠቀመበት የመጀመሪያ አሰላለፍ ውስጥ አማካዩን አማኑኤል ተሾመን አስቀምጦ ምንይሉ ወንድሙን የተጠቀመ ሲሆን ጅማ አባ ጅፋር በበኩሉ ከቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር ነጥብ ከተጋራበት ጨዋታ ጉዳት የገጠማቸው ቢኒያም ሲራጅን እና ኄኖክ ኢሳያስን በነጂብ ሳኒ እና አሮን አሞሀ ለውጧል።
ከተያዘለት ሰዐት 30 ደቂቃ ቀድሞ 9፡30 ላይ በጀመረው ጨዋታ የመጀመሪያ አጋማሽ በአመዛኙ ሁለቱ ቡድኖች እየተፈራረቁ የኳስ ቁጥጥር የበላይነቱን ይዘው የታዩበት ነበር። ሆኖም የሜዳው ምቹ አለመሆን ተደምሮበት የጨዋታው ፍጥነት ዝግ ማለት ተቃራኒ ቡድን የመከላከል ቅርፁን ከመያዙ በፊት ወደ ሶስተኛው የሜዳ ክፍል እንዳይድርሱ እክል ሆኖባቸዋል። ለዚህ መፍትሄ እንዲሆናቸው በተለይ በመጀመሪያዎቹ ደቂቃዎች ወደ ፊት ቀጥተኛ ኳሶችን ለአጥቂዎች ሲልኩ የነበሩት መከላከያዎች በሙከራ ብዛት የተሻሉ የነበሩ ቢሆንም የፈጠሯቸው አብዛኞቹ ዕድሎች በአጫጭር ቅብብሎች ላይ ከተመሰረተው የመጀመሪያ ዕቅዳቸው የመነጩ አልነበሩም። ቴዎድሮስ ታፈሰ ፣ ፍፁም ገ/ማርያም እና ምንይሉ ወንድሙ ሙከራዎች ከሳጥን ውጪ የተደረጉ ሲሆን 39ኛው ደቂቃ ላይ ከግራ መስመር በተነሳው እና ማራኪ ወርቁ ግብ ጠባቂውን አልፎ ወደ ውስጥ የመለሰውን ኳስ ቴዎድሮስ ታፈሰ ሞክሮ በጅማ ተከላካዮች ርብርብ በዳንኤል አጃዬ የተያዘበት እንዲሁም 44ኛው ደቂቃ ላይ ሳሙኤል ሳሊሶ ወደ ግራ ካደላ የቅጣት ምት በቀጥታ መክሮ በግብ ጠባቂ የተያዘበት ኳሶች ቡድኑ ለጎል የቀረበባቸው ነበሩ። ከዚህ ውጪ ግን መከላከያዎች ጅማዎች ከኳስ ውጪ በሚሆኑባቸው አጋጣሚዎች የሚሰሩትን ሁለት የአራት ተጨዋቼች መስመር ሰብረው ለመግባት ሲቸገሩ ይስተዋሉ ነበር።
ተመሳሳይ ፈተና የነበረባቸው ጅማ አባ ጅፋሮች በበኩላቸው የፊት አጥቂዎቻቸውን ወደ ኃላ በመሳብ እና የቀኝ መስመር ተከላካዩ ኄኖክ አዱኛን በማጥቃት ሂደት ላይ በማሳተፍ ተጨማሪ የመቀባበያ አማራጮችን ለመፍጠር ሲሞክሩ ይታይ ነበር። አባ ጅፋሮች ምንም እንኳን 3ኛው ደቂቃ ላይ ኦኪኪ አፎላቢ የበሀይሉ ግርማን የተሳሳተ ቅብብል ተጠቅሞ ካደረገው ሙከራ በኃላ በርካታ የሚባሉ ዕድሎችን መፍጠር ባይችሉም ኳስ በሚይዙባቸው አጋጣሚዎች በእንቅስቃሴ ክፍተቶችን ለማግኘት ደጋግመው ይሞክሩ የነበረበት ሂደት 30ኛው ደቂቃ ላይ ፍሬ አፍርቶላቸዋል።
በዚህ መሀል ለመሀል ከሰነዘሩት ጥቃት ከመከላከያ የኃላ ክፍል በሚታወቅበት ፍጥነቱ አፈትልኮ የገባው ተመስገን ገ/ኪዳን በይድነቃቸው አናት ላይ ኳስን በመላክ ቡድኑን ቀዳሚ አድርጎታል። ከዚህ በተጨማሪ አባጅፋሮች ይፈጥሯቸው ከነበሩ ጫናዎች ያገኟቸው የማዕዘን ምቶችም ተጨማሪ አጋጣሚዎችን ቢፈጥሩላቸው ወደ ሌላ ንፁህ የግብ ዕድልነት ሳይቀይሯቸው የመጀመሪያው አጋማሽ ተጠናቋል።
ከእረፍት መልስ በነበሩት የመጀመሪያ ደቂቃዎች መከላከያዎች በተሻለ ሁኔታ ኳስ ይዘው በጅማ የሜዳ ክልል መቆየት ችለው ነበር። ሆኖም አሁንም ትኩረታቸው ከሳጥን ውጪ በሚደረጉ ሙከራዎች ላይ ነበር። የምንይሉ ወንድሙ እና ሳሙኤል ሳሊሶ መሰል ሙከራዎችም በብዙ ርቀት ኢላማቸውን ያልጠበቁ ነበሩ። በነዚህ ጊዜያት ወደ ኃላ አፈግፍገው የነበሩት ጅማዎች 47ኛው ደቂቃ ላይ ተመስገን ገ/ኪዳን ከግራ መስመር በጣለው ኳስ በኦኪኪ አማካይነት ከቅርብ ርቀት የመጀመሪያ ሙከራ አድርገው ነበር። ይህ ሁኔታ ሁለተኛውን አጋማሽ ወደ ኃላ ያፈገፈገ እና መልሶ ማጥቃትን ብቻ ምርጫው ያደረገ አባ ጅፋር የሚያሳየን ይመስል ነበር። ሆኖም ቀጣዮቹ ደቂቃዎች እንደመጀመሪያው ሁሉ ቡድኖቹ ብልጫ በመውሰድ የተፈራረቁባቸው ነበሩ።
በብዛት ከግራ መስመር ከሳሙኤል ሳሊሶ እና ታፈሰ ሰረካ በሚነሱ ኳሶች መነሻነት ለማጥቃት ሲሞክሩ የነበሩት መከላከያዎች አሁንም ዘልቀው ወደ ጅማ ሳጥን መግባት ቀላል አልሆነላቸውም። ከ60ኛው ደቂቃ በኃላ ያገኙት አንፃራዊ ብልጫም የሚፈልጉትን ያህል በቂ ዕድሎችን አላመጣላቸውም። 59ኛው ደቂቃ ላይ ከምንይሉ ወንድሙ በተነሳ ኳስ አቤል ከበደ ከግብ ጠባቂ ጋር ተገናኝቶ ያልተጠቀመበት እንዲሁም 71ኛው ደቂቃ ላይ ፍፁም ገ/ማርያም ከአሚኑ ነስሩ ጋር ታግሎ ካገኘው ኳስ ከረጅም ርቀት አክርሮ ሞክሮ ዳንኤል አጃዬ ያወጣበት ሙከራዎች ጦሩን አቻ ለማድረግ የተቃረቡ ሙከራዎች ነበሩ። በተመሳሳይ 58ኛው ደቂቃ ላይ አሮን አሞሀ በቀኝ መስመር ዘልቆ ከገባ በኃላ ካመከነው ኳስ በኃላ ደጋግመው ወደ ሶስተኛው የሜዳ ክፍል መዝለቅ ያልቻሉት ጅማዎች ኳስ በሚይዙባቸው ጊዜያት እንደመጀመሪያው አጋማሽ በትዕግስት ክፍተቶችን ከመፈለግ ይልቅ ረጃጅም ኳሶችን ወደ ፊት መጣል ምርጫቸው አድርገው ነበር።
የመከላከያ ጫና እየበረታ በመጣባቸው ደቂቃዎች ላይ ቡድኑ በሁለቱ መስመሮች በተለይም በግራ በኩል ሰብሮ ለመግባት ተደጋጋሚ ጥረት አድርጎ ነበር። ሆኖም በመጨረሻ ደቂቃ ምንይሉ ወንድሙ ከቀኝ መስመር ደርሶት ከሳጥን ውስጥ ሞክሮ ከሳተው ኳስ ሌላ ያለቀለት የግብ ዕድል መፍጠር አልቻሉም። ጅማዎች በበኩላቸው መላኩ ወልዴን እና እንዳለ ደባልቄን ቀይረው ያስገቡበት ሁኔታ የመከላከያን ጫና ለመቋቋም አግዟቸውል።
የመጨረሻዎቹን ደቂቃዎችም ኤልያስ አታሮን ወደ ግራ መስመር ተከላካይነት በመውሰድ እንዲሁም እንዳለ ኄኖክ አዱኛን በቀኝ በኩል እንዲያግዘው በማድረግ ተጨማሪ ተሻጋሪ ኳሶች ወደ ሳጥናቸው እንዳይጣሉ ያደረጉት ጥረት ተሳክቶላቸዋል። አባ ጅፋሮች በማጥቃት ሂደቱ ላይ የሚያሳትፏቸው ተጨዋቾች ቁጥር ከደቂቃ ወደ ደቂቃ እየተመናመነ ቢመጣም የ1-0 ውጤቱን አስጠብቀው መውጣት ግን አልተሳናቸውም። በውጤቱ አባ ጅፋር ነጥቡን 45 በማድረስ ቅዱስ ጊዮርጊስን በግብ ክፍያ በመብለጥ ወደ ሊጉ ሰንጠረዥ ተመልሷል። በአንፃሩ መከላከያ ወደ 6ኛ ደረጃ ከፍ ሊል የሚችልበትን እድል ሳይጠቀምበት ቀርቷል።