የቅዱስ ጊዮርጊስ ስፖርት ማህበር የዲሲፕሊን ኮሚቴ በክለቡ ላይ የተጣለበት የ50 ሺህ ብር የገንዘብ ቅጣት ተገቢ አለመሆኑን እና በጅማ አባጅፋር ላይ የተወሰደው የዲሲፒሊን ውሳኔ የተፈጠረውን ጉዳት ከግምት ያላስገባ ነው ሲል ይግባኝ ጠይቋል።
በ25ኛ ሳምንት የኢትዮዽያ ፕሪምየር ሊግ ጅማ ላይ በተካሄደው የጅማ አባ ጅፋር እና ቅዱስ ጊዮርጊስ ጨዋታ ዙርያ የዲሲፒሊን ኮሚቴው ጅማ አባጅፋር 1 ጨዋታ ከሜዳው ውጭ 200 ኪሎ ሜትር ርቆ እንዲጫወት፣ 150 ሺህ ብር ቅጣት እንዲሁም የተጎዱ ደጋፊዎችን የህክምና ወጪ እንዲሸፍን፣ ቅዱስ ጊዮርጊስ የ50 ሺህ ብር ቅጣት እንዲሁም የእለቱ ዋና ዳኛ የነበሩት ፌድራል ዳኛ ይርጋለም ወ/ጊዮርጊስ እና ኮሚሽነር ፍቃዱ ጥላሁን ስለጨዋታው ያቀረቡት ሪፖርት እና ትላንት በአካል ተገኝተው ያስረዱት በመለያየቱ የዳኞች ኮሚቴ ዳኞቹን እና የሊግ ኮሚቴው ደግሞ ኮሚሽነሩን የተመለከተ የቅጣት ውሳኔ በመወሰን ሪፖርት በአፋጣኝ እንዲቀርብ መወሰኑን ይታወቃል።
የቅዱስ ጊዮርጊስ እግርኳስ ክለብ 50 ሺህ ብር የተቀጣበት መንገድ በየትኛውም አግባብ ተገቢ ያልሆነ ውሳኔ ነው። እንዲሁም “በዕለቱ በቡድናችን ውጤት እና በደጋፊዎቻችን ላይ የደረሰው ጉዳት ከግምት ያላስገባ ውሳኔ” በመሆኑ ቅሬታውን ለይግባኝ ሰሚ ኮሚቴ ዝርዝር ሀሳቦችን የያዘ በደብዳቤ እንዳቀረበ ታውቋል። የይግባኝ ሰሚ ኮሚቴም ጉዳዩን ተመልክቶ በቀጣይ ውሳኔ ይሰጣል ተብሎ ይጠበቃል።