ተመስገን ገብረኪዳን አምና ያሳካውን የከፍተኛ ሊግ ድል ዘንድሮም በፕሪምየር ሊጉ ለመድገም ያልማል

ተመስገን ገብረኪዳን ከከፍተኛ ወሳኝ ጎሎችን በማስቆጠር ጅማ አባ ጅፋር ወደ ኢትዮዽያ ፕሪምየር ሊግ እንዲያድግ ትልቁን አስተዋፆኦ ካበረከቱ ተጫዋቾች መካከል አንዱ ነው ። በዘንድሮ አመትም ጅማ በአሰልጣኝ ገብረመድህን ኃይሌ እየተመራ ለሊጉ ቻምፒዮንነት እየተፎካከረ እንዲገኝ ካስቻሉ ወሳኝ ተጫዋቾች አንዱ ነው። 

ተመስገን ራሱ ባስቆጠረው ጎል መከላከያን 1-0 በመርታት ወደ ሊጉ አናት ከተመለሱበት ጨዋታ በኋላ ስለ እግርኳስ ህይወቱ እና ተያያዥነት ስላላቸው ጉዳዮች ከሶከር ኢትዮጵያ ጋር ቆይታ አድርጓል።

በከፍተኛ ሊግ በቀድሞ ስሙ ጅማ ከተማ አሁን ጅማ አባጅፋር ጋር የነበረህ ቆይታ ምን ይመስል ነበር ?  

አምና ቡድኑን የተቀላቀልኩት ዘግይቼ ነበር ። የአሁኑ የፌዴሬሽኑ ፕሬዝደንት ኢሳይያስ ነው ከፋሲል ከተማ ጋር አብሬ እየሰራው በዝግጅት ወቅት ሲቀንሱኝ እሱ በመጨረሻ የዝውውር ወቅት ነው ወደዚህ ያመጣኝ። እንደመጣው አሰልጣኝ ክፍሌ ቦልተና ነው ቡድኑን የያዘው እንደ አጋጣሚ ከያዘው ስብስብ ውስጥ ከፊት መስመር ላይ እኔን የሚመቹኝ አይነት አጥቂዎች እንደ ሄኖክ መሀሪ ሌሎቹም የነበሩ በመሆኑ ብዙም ለመዋሀድ አልቸገረኝም ነበር። በጣም ጥሩ ጊዜ ነው ያሳለፍኩት ወሳኝ ወሳኝ የሚባሉ ጨዋታዎች ላይ ግብ በማስቆጠር ቡድኑም ወደ ፕሪምየር ሊግ እንዲያድግ ከማድረጋችን በተጨማሪ እኔም በግሌ 17 ጎል በማስቆጠር የከፍተኛ ሊጉ ሁለተኛ ኮከብ ጎል አስቆጣሪ ሆኜ መጨረስ ችያለው።

በከፍተኛ ሊግ ላይ በአጥቂ መስመር ላይ ስማቸው ቀድሞ ከሚጠሩ ተጫዋቾች መካከል አንዱ ነህ ። ሆኖም ከዚህ ቀደም በፕሪምየር ሊግ መጫወት አልቻልክም። በፕሪምየር ሊጉ ክለቦች ከአንድም ሁለት ክለብ ገብተህ ተቀንሰሀል። ምንድነው ምክንያቱ ?  

ለኔ በከፍተኛ ሊግ እና በፕሪምየር ሊግ መጫወት ብዙም ልዩነት የለውም። ዋናው ነገር የምትሰጠው ትኩረት ነው። ፕሪምየር ሊጉ ትኩረት ይሰጠዋል ፣ አንፃራዊ ጥራት ያለው ሜዳ ላይ ትጫወታለህ ፣ የተሻለ የዳኝነት ውሳኔ ታገኛለህ… ይህ ካልሆነ በቀር ከከፍተኛ ሊግ ብዙ የተለየ ነገር የለም። አሁን በፕሪምየር ሊግ መጫወት እንደምችል አቅሜን እያሳየው እገኛለው። አንዳንዴ ያልተረዱኝ አሰልጣኞች አሉ፤ ከእነሱ ጋር ማሳለፌ በፕሪምየር ሊጉ እንድጫወት አላገዘኝም ይሆናል ። አሁን ግን አሰልጣኝ ገብረመድህን ተረድቶኝ የተሻለ ነገር እየሰራው አቅሜንም እያሳየሁ ነው። ለእኔ ዋናው ነገር የአሰልጣኝ መረዳት እና አለመረዳት ነው በፕሪምየር ሊግ እንዳልጫወት እንቅፋት የሆነብኝ የምለው።

በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ስትጫወት ይህ አመት የመጀመርያህ ነው። እንዴት አየህው ? 

አዎ የመጀመርያዬ ነው። ግን ብዙም አልከበደኝም። እንዳውም ከፍተኛ ሊጉ በጣም ይከብዳል። በከፍተኛ ሊግ ሳደርገው ከነበረው እንቅስቃሴ በተሻለ ሁኔታ አሰልጣኝ ገብረመድህን ባለኝ ነገር ላይ ጨምሮልኝ እንደ መጀመርያ ፕሪምየር ሊግ ተሳትፎ አይደለም እየተጫወትኩ ያለሁት። ብዙ ጎል ባላስቆጥር እንኳ የጎል እድሎችን እየፈጠርኩ ነው። ፈጣሪ ይመስገን አሁን አቅሜን እያወጣሁ፤ ልምዶችም እያገኘሁ ነው። ከዚህ በኋላም በሊጉ ብዙ አቅሜን እያሳየሁ እቀጥላለው።

የክለብህ አስገራሚ የውድድር ዘመኑ ጉዞ እንዴት ይገለፃል?

መጀመርያ ላይ በተከታታይ ሳምንት ነጥብ ስለጣልን ጅማ እንደመጣ ይወርዳል ተብለን ነበር። ነገር ግን ትልቁን ሚና እየተጫወተ የሚገኘው አሰልጣኝ ገብረመድህን ነው። ተከታታይ ነጥብ ስንጥል “እኔ አለሁ፤ ሙሉ ኃላፊነቱን እኔ እወስዳለው። አምኜባቹ ነው እዚህ ያመጣኋችሁ፤ የተሻለ አቅም አላችሁ። ያሰራኋቹሁን ልምምድ ሜዳ ላይ ተግብሩ።” በማለት ከጫና ነፃ አድርጎናል። አንድ አሰልጣኝ  ካመነብህ ደግሞ ያለህን ነገር ሁሉ ትሰጣለህ። በነፃነት እየተጫወትን ነው እዚህ ደረጃ ላይ መድረስ የቻልነው። ጅማ አባጅፋር ውስጥ የምንጫወተው እንደ ቡድን አንድ ሆነን ነው። ሜዳ ላይ አንዳንችን ከአንዳችን እየተነጋገርን ያለንን አቅም ሁሉ አውጥተን ነው የምንጠቀመው። ይህን ይመስላል እስከ ዛሬ ድረስ የነበረው ጉዟችን።

አሁን ወደ ወሳኝ ምዕራፍ ደርሳችኋል። አራት ጨዋታ ይቀረዋል፣ የሊጉ መሪ ናችሁ፣ አሸናፊ ሆኖ ለማጠናቀቅ ምን ታስባላቹ ?

ለጅማ ህዝብ የሊጉን ዋንጫ አንስተን ማሳየት እንፈልጋለን። ምክንያቱም የጅማ ህዝብ በጣም ኳስ ይወዳሉ፤ ለእግርኳሱ ጥሩ ነገር አላቸው። በምንችለው አቅም ሁሉ ቀሪ ጨዋታዎችን በድል በማጠናቀቅ ዋንጫውን ወደ ጅማ ይዘን ለመሄድ ከፍተኛ ሞራል ላይ ነው የምንገኘው።

በግልህስ ምን ታልማለህ ?

እኔ ታሪክ መስራት እፈልጋለው። ጅማ አባጅፋርን ፕሪምየር ሊግ እንዲያድግ ረድቻለሁ ፤ ዋንጫም አንስተናል። አሁን ደግሞ ሌላ ታሪክ መስራት እፈልጋለሁ። በተከታታይ ዓመታት የከፍተኛ ሊጉን እና የፕሪምየር ሊጉነ ዋንጫ አነሳ መባልን እፈልጋለው፤ አላማዬም ይሄ ነው ። ከዚህ በተረፈ ዋናው ነገር ከእኔ የግል ስኬት በፊት ጅማ አባጅፋር እንዲቀድም ነው የምፈልገው። በተቻለኝ አቅም ማግባት የምችላቸው ኳሶች እጨርሳለሁ። ካልሆነ እንደ ቡድን እንቀሳቀሳለው። እኔ በግሌ ጎልቼ እንድወጣ የተለየ ነገር ማድረግ አልፈልግም። ምን አልባት ስግብግብ አለመሆኔ ትንሽ ጎል እንዳገባ አድርጎኛል። ይህ የሆነው ደግሞ ቅድሚያ የሰጠሁት ለጅማ አባጅፋር በመሆኑ ነው። ዘንድሮ ብዙ ልምድ አግኝቻለው፤ በቀጣይ ዓመት ከዚህ የተሻለ እሰራለው ብዬ አስባለሁ።