የ2018 የፊፋ ዓለም ዋንጫ ዛሬ ሞስኮ ላይ ሩሲያ እና ሳውዲ አረቢያ በሚያደርጉት የምድብ አንድ መክፈቻ ጨዋታ ይጀምራል፡፡ በዓለም ዋንጫው 5 የአፍሪካ ሃገራት የሚሳተፉ ሲሆን ከተሳታፊ የአህጉሪቱ ብሄራዊ ቡድኖች ጋር በተያያዘ የሮይተርስ የስፖርት ዘጋቢ እንዲሁም የክዌሴ ኢኤስፒኤን እና ጎል አፍሪካ የእግርኳስ ፀሃፊ ኤድዋርድ ዶቭ ከሶከር ኢትዮጵያ ጋር ቆይታ አድርጓል፡፡
በአንተ አስተያየት እና አሁን ላይ ካሉበት ወቅታዊ አቋም አንፃር የትኞቹ የአፍሪካ ሃገራት ወደ ጥሎ ማለፉ የሚያልፉ ይመስልሃል?
እኔ እንደማስበው ግብፅ እና ሴኔጋል የተሻለ የማለፍ እድል ያላቸው ይመስለኛል፡፡ ምክንያቱ ደግሞ የተደለደሉበት ምድብ ነው፡፡ ቱኒዚያ ከሚሳተፉት የአፍሪካ ሃገራት መካከል ደካማዋ ናት፡፡ ያለችበትም ምድብ አሳሳች እና በምድባቸው እንግሊዝ እንዲሁም ቤልጂየምን መኖራቸው ተከትሎ በቶሎ ከውድድር ይወጣ ብዬ ከምጠብቃቸው ሃገራት መካከል ነች፡፡ ሞሮኮ አሁን ካለችበት ምድብ የተለየ ቦታ ላይ ብትሆን ታልፋለች ብዬ አስብ ነበር ሆኖም በምድቡ ስፔን እና ፖርቹጋል አሉ፡፡ ያልጠበቅነውን ነገር ማሳየት እንደሚችሉ ግን እምነት አለኝ፡፡ ነገር ግን ገና በመጀመሪያው መሰናክል ይወድቃሉ ብለን ማሰባች ስህተት አይደለም፡፡ ናይጄሪያ በአቋም መለኪያ ጨዋታ አስደሳች አልነበረችም፡፡ ምድባቸውም ሲታይ ፈተና ያለበት እና ከባድ ነው እነክሮሺያ፣ አይስላንድ እና አርጀንቲና ነው የሚገኙት፡፡ ግብፅ እና ሴኔጋል የራሳቸው ደካማ ጎን ያላቸው ቡድኖች ቢሆንም እኔ እንደማስበው የተመደቡበት ምድብ ይበልጥ ቀናን ነገር እንዲጠብቁ ደርጋቸዋል፡፡ በይበልጥ ግብፅ ሩሲያ እና ሳውዲ አረቢያ ያሉ ትንሽ ደከም ያሉ ሃገራትን ትገጥማለች፡፡ መሃመድ ሳላህ በፍጥነት ያገግማል ብዬ ስለማስብ ግብፅ በተሻለ የማለፍ እድል ይኖራታል፡፡
የግብፁ አሰልጣኝ ሄክቶር ኩፐር በአመዛኙ የሚከላከል ቡድን በመስራት ይታወቃሉ፡፡ በፈርኦኖቹም የሰሩት በተመሳሳይ መልኩ የሚታይ ነው፡፡ ይህ የመከላከል ስትራቴጂ በዓለም ዋንጫ አዋጪ ይሆናል?
ግብፅ በደንብ የተደራጀ እና ችግርን በሚገባ መቋቋም የሚችል ቡድን ነው፡፡ በሚገባ ልምድ ያላቸው ተጨዋቾችን የያዘ እና የተሰራ ቡድን ነው፡፡ በመከላከል የተጠመደ ቡድን መሆኑ ነውር አይደለም በአሉታዊ ጎኑም ብቻ መታየት የለበትም፡፡ መከላከል እራሱ ጥንካሬ ነው፡፡ እንደዓለም ዋንጫ ያሉ ውድድሮች ላይ አንዱ ቡድን ከሌላው ጋር ፈፅሞ ሊመሳሰል እና እኩል ሊሆን አይችልም፡፡ በሶስተኛው የሜዳ ክፍል ላይ የማጥቃት ባህሪ ያላቸውን እና አሰልጣኙ ለሚከተሉት የመከላከል ታክቲክ ማካካሻ የሚሆኑ ለውጥ ፈጣሪ ተጫዋቾች ግብፆች ይዘዋል፡፡ በግልፅ ለማስቀመጥ ሳላህ (የሚመጣው አንድ አፍሪካዊ ተጫዋች በአውሮፓ ታላላቅ ሊጎች ፈፅሞ አድርጎት የማያውቀው የውድድር ዘመን ከጀርባው አድርጎ ነው)፣ እንደ ቴሬዝጌ፣ አብደላ ኤል ሳዒድ፣ ሺካባላ፣ ካራባን ካየን ክህሎት ያላቸው አጥቂዎች ቡድኑ መያዙን መረዳት እንችላለን፡፡ እነዚህ ተጨዋቾች ቡድኑ የሚከተለውን የመከላከል አጨዋወት ማመጣጠን የሚችሉ ናቸው፡፡ እኔ የምጨነቀው የሚከተሉት አጨዋወት ካላወጣ እንዴት ከጨዋታው ጥሩ ነገር ይዘው መውጣት እንደሚችሉ እና ሁለተኛ እቅድን መተግበር ላይ ነው፡፡ በባለፉት ግዜያት እንዳስመሰከሩት ጨዋታዎች እነሱ ባቀዱት መልኩ ሳይሄድ ሲቀር ምላሽ መስጠት ላይ ሲቸገሩ ተስተውሏል፡፡
ስለቱኒዚያ ብሄራዊ ቡድን ያለህ ምልከታ ምን ይመስላል የየሱፍ ሳክኒ እና ጠሃ ያሲን ኬኔሲ በጉዳት አለመኖርንስ እንዴት ይቋቋሙታል ብለህ ተጠብቃለህ?
እስካሁን ባየሁት ነገር ቱኒዚያ ጥሩ ትመስላለች፡፡ የሳክኒ እና ኬኔሲ አለመኖር ለቡድኑ ህመም ነው፡፡ ሳክኒን ማጣት ምንም ጥያቄ የለውም ከባድ ነው ኬኔሲም ቢሆን አምና የቻምፒየንስ ሊጉ የጣምራ ኮከብ ግብ አግቢ ነበር፡፡ በማጥቃቱ ላይ ያለው ድርሻ የቡድኑም የፊት አውራሪ ያስብለዋል ብል ማጋነን አይሆንም፡፡ ሆኖም ከጉዳት የተመለሰ ቢሆንም እና በመጋቢት ወር በነበሩት የአቋም መለኪያ ጨዋታዎች ጥሩ የተንቀሳቀሰው አኒስ ባድሪ እራሱን በሚገባ በቡድኑ ውስጥ እየገነባ ይገኛል፡፡ በመሃልም ይሁን በክንፎች መጫወት ይችላል፡፡ ሌላው ነይም ሲሊቲ ነው፡፡ በፈረንሳይ ሊግ በዲዮን የተሳካ ግዜን አሳልፏል፡፡ ኳስ በእግሩ ከገባች ምን መስራት የሚችል እና በቀላሉ ተጋጣሚዎቹን ማሸበር እና እረፍት መንሳት የሚችል ተጫዋች ነው፡፡ በግራም ይሁን በመሃል ከተሰለፈ ለተጋጣሚዎች ጠንቅ ነው የሚሆነው፡፡ ለቱኒዚያ የራስ ምታት የሚሆነው አስቀድሜ እንደገልፅኩት ምድባቸው ነው፡፡ እንግሊዝ እና ቤልጂየም ነው ያሉት፡፡ ከፓናማ ላይ ሶስት ነጥብ ማሳካት ይችሉ እድላቸው ለማስፋት ይሆናቸዋል፡፡ ሆኖም በመጀመሪያዎቹ ጨዋታዎች ከተሸፉ ይወድቃሉ የሚል ፍርሃት በውስጤ አለ፡፡ እንግሊዝ በጥሩ ሁኔታ ላይ ያለች ትመስላለች ስለዚህም ቱኒዚያ በመጀመሪያው ጨዋታ ትፈተናለች፡፡ ሆኖም ያላቸው የአማካይ ክፍል በጣ ጥሩ ነው፡፡ በመጀመሪያዎቹ 30 ደቂቃዎች እንግሊዞችን ማፈናፈኛ ካሳጡ ምንአልባትም ከጨዋታው በኃላ የምናወራው ሌላ ታሪክ ይሆናል፡፡
የሞሮኮ የቡድን ቅርፅ እና አደረጃጀት በጣም ጥሩ የሚባል ነው፡፡ ካሉት የአፍሪካ ተሳታፊ ቡድኖችም የተመጣጠነ ነው፡፡ ስለአትላስ አንበሶቹ ምን ትነግረናለህ?
ሞሮኮ እጅግ በጣም ሊታመን የማይችል ቡድን ነው ይዛ የቀረበችው፡፡ የሄርቬ ሬናር አድናቂ ነኝ፡፡ በ2017 የአፍሪካ ዋንጫ ምን እየሰሩ መሆኑን እቃዳቸውን አሳይተውናል፡፡ ሬናር በእቅዱ 6 ጠንካራ የሆኑ የመከላከል ባህሪ ያላቸው (ወግ አጥባቂ ተከላካዮች ሳይሆን እራሳቸው በእግርኳስ መግለጥ የሚችሉ) ተጫዋቾችን መያዝን ይወዳል፡፡ አራት ደግሞ ማጥቃት እና ማጥቃትን ብቻ የሚተገብሩ ተጫዋቾች ይይዛል፡፡ ይሄ ቡድንን ለመስበር በጣም አስቸጋሪ ነው፡፡ በማጣሪያው የተቆጠረባቸው የግብ መጠንን መመልከት በቂ ነው፡፡ እንደሃኪም ዚየች ያለኮከብ ቡድኑ አለው፡፡ ዚየች በውድድሩ ባለክህሎት ያለው እና ተፅዕኖ መፍጠር የሚችል አፍሪካዊ የመሆን እድል አለው፡፡ በውድድሩ ላይም ጎልቶ የሚወጣ አፍሪካዊ ተጫዋች ይመስለኛል፡፡ አዩብ ኤል ካቢን በዚህኛው ቡድን ውስጥ መመልከት በመቻሌ ደስተኛ ነኝ፡፡ ቻን ላይ ለሁለተኛው ቡድን እንዳደረገው የዋናው ቡድን የፊት መስመር ተሰላፊ መሆን የቻለበት ሽግግርን ማድነቅ ይገባናል፡፡ በመጀመሪያ የምድብ ጨዋታቸው ማሸነፍ ይችላሉ ከዛ በኃላ ግን ፓርቹጋል እና ስፔን ናቸው ያሉት፡፡ ይህ በጣም ፈተና የበዛበት ሁለት 90 ደቂቃ ነው የሚሆነው፡፡ ፓርቹጋል የወቅቱ የአውሮፓ ቻምፒዮን ናት፡፡ ስፔን ደግሞ በሁሉም ቦታ የተጫዋቾች ሃብታም የሆነ ቡድን ይዛለች፡፡ በወረቀት ላይ ካየነው ከሞሮኮ ይልቅ ለአውሮፓዊያኑ የማሸነፍ ቅድመ ግምትን እንድንሰጥ እንገደዳለን ነገር ግን ሬናር የታክቲክ ጦርነቶቹን የሚወዳቸው ይመስለኛል፡፡ ክሪስቲያኖ ሮናልዶን ለማቆም የሚሰራውን ስራ እና የስፔን ብዙ የማጥቃት ክህሎት ያላቸው ተጫዋቾች ለመግታት የሚተገብረው እቅድ በትኩረት መመልከት አለብን፡፡ ከዚህ ምድብ አምልጦ ወደ ሁለተኛው ዙር ማለፍ የሚችል ቡድን ካለ እሱም ሞሮኮ ብቻ ነው የሚሆነው፡፡
ሴኔጋል በተስጥኦ በኩል የማይታማ ቡድን ይዛ ቀርባለች፡፡ ሆኖም ብዙዎች የአሰልጣኝ አሊዩ ሲሴን የታክቲክ አተገባበር የሚተቹ አሉ፡፡ የ2002 አስገራሚ ግስጋሴ የአሁኑ ቡድን ያሳየናል የሚል እምነት አለህ?
ልክ ነው ሴኔጋል ባለክህሎት የሆኑ ተጫዋቾች የተሰባሰቡበት ቡድን ነው፡፡ በመካከሉም ይሁን በማጥቃቱ ጥሩ ስብሰብ ይየዛ ነው፡፡ በመስመር ተከላካዮች በኩል ይሄንን መናገር አልችልም ለምን ቢባል የቡድኑ ደካማ ጎን እነዚህ የኮሪደር ቦታዎች ናቸው ብዬ ስለማስብ ነው፡፡ በመሃል ተከላካይነት ጥሩ መጫወት የሚችሉ አሉ፡፡ በመሃል ተከላካይነት ሁለትም ይሁን ሶስትም ተጫዋች ቢመርጡ ሊያዋጣቸው የሚችል ቡድን ነው ያላቸው፡፡ በዓለም ዋንጫው ብዙ አማራጮችን ከያዙ ካላቸው በቁጥር ትንሽ ቡድኖች መካከል ሴኔጋል አንዷ ነች፡፡ ቅድም እንደገልፅኩት ምድባቸው በጣም ጥሩ ነው፡፡ ከምድቡ መያዝ የሚገባቸው ማግኘት ይችላሉ፡፡ ከፖላንድ እና ኮሎምቢያ በላይ ሆነ መጨረስ ይችላሉ፡፡ በጃፓን ይህን ያህል አልተገረምኩም፡፡ ሆኖም ፖላንድ እና ኮሎምቢያ ፈተና የመሆን አቅም ያላቸው ቡድኖች ናቸው፡፡ ሴኔጋል ላይ ጉዳት ማድረስ የሚችሉ ናቸው፡፡ ሴኔጋል ከምድብ ብታልፍም ልታገኝ የምትችለው እንግሊዝን ወይም ቤልጂየምን ነው፡፡ አነዚህን ቡድኖች አሸንፋ የ2002ቱ ገድል የመድገም አቅም ይኖራል የሚል እሳቤ የለኝም፡፡ አሁን ላይ እውነት ለመናገር ከሲሴ ካየነው ይበልጥ ብዙ ማየት የሚጠበቅብን ግዜ ላይ ነን፡፡ በማጣሪው ጥሩ ጉዞን አድርገዋል፡፡ ኮያቴ እና ጌይ ጥሩ የተከላካይ አማካዮች ናቸው ግን የመሃል ሜዳውን መቆጣጠሩ ላይ የሉበትም፡፡ ጌይ ከኳስ ጋር መጥፎ ተጫዋች አይደለም ሆኖም ኳሶችን የሚያቀበል እና የጨዋታውን ቴምፖ የሚቆጣጠር ተጫዋች አይደለም፡፡ ይሄን ማድረግ የሚችል እና በማዕበል ወቅት ቡድኑን አረጋግቶ ከፈተናው ማውጣት የሚችል ተጫዋች የላቸውም፡፡ ሲሴ የተለየ ነገር ካላሳየን በቀር በ16ቱ በኃላ ያለውን መንገድ ሴኔጋል የምትጓዝ አይመስለኝም ከምድብ ብታልፍም፡፡
ስለናይጄሪያ እናውራ እሰኪ፡፡ ቡድኑ ካለፉት ጥቂት አመታት ወዲህ መሻሻሎችን አሳይቷል፡፡ የአዕምሮ ዝግጁነት ሁሌም ጥያቄ ቢሆንም በውድድሩ ላይ ጥሩ ውጤት እንዲመጡ ከተፈለ ምን ማድረግ አለባቸው ትላለህ?
ናይጄሪያ በግሮነር ስር የሚታይ ለውጥ አሳይታለች፡፡ ከስቴፈን ኬሺ ቡድን በኃላ ያለውን መጥፎ ግዜም የሚያስረሳ ቡድን አሁን ላይ ሰርታለች፡፡ ከኬሺ በኃላ ኦሊሴ የመራው ቡድን ለ2015 እና 2017 የአፍሪካ ዋንጫ ማለፍ አልቻለም፡፡ በአጠቃላይ የውድድር አዕምሮ የላቸውም ሆኖም እንደጆን ኦቢ፣ ቪክተር ሞሰስ እና አሌክስ ኢዮቢ ያሉ በትላልቅ ክለቦች እየተጫወቱ የሚገኙ እና የተጫወቱ ተጫዋቾችን መያዛቸው ጥቅም አለው፡፡ ዊልፍሬድ እንዲዲ ደግሞ ያሉት አዳዲስ መጪ የብሄራዊ ቡድን ተጫዋቾች አሉ፡፡ እንዲዲ ከሌስተር ጋር ዓምና በነበረው ቻምፒየንስ ሊግ ጥሩ ደረጃ ላይ መድረስ የቻለ እና በፕሪምየር ሊግ ራሱን ማሳየት የቻለ ተጫዋች ነው፡፡ ስለዚህ የአዕምሮ ዝግጁነት ጥያቄ አሳሳቢ አይሆንም፡፡ መሻሻል አለበት ብዬ ማስበው የአማካይ ክፍሉ ነው፡፡ ቁልፍ ክፍሉ ይህ ስለሆነ ነው ይህንን ማንሳት የወደድኩት፡፡ ሚኬኤል እንደተቆጣጣሪ ዲዲ እንደኳስ አጨናጋፊ ኦናዚ ወይም ኦቴቤ እንደኳስ ይዞ ሚጫወት አማካይ ካየን የቡድኑ የልብ ምት ይህ ክፍል መሆን አጠያያቂ አይሆንም፡፡ ከእንግሊዝ እና ቼክ ሪፐብሊክ ጋር ሲጨወቱ በፍጥነትም የመጎተት ነገር የመጠቅጠቅ ችግር በቦታቸው በፍጥነት ያለመገኘት እና ደካማ መሆንን አይተናል፡፡ ይሄን ማረም ከቻሉ የሚያስጨንቅ ነገር አይኖርም፡፡ ከክሮሺያ ጋር ሲጫወቱ ይሄን ችግር ይዞ መገኘት ማለት ለነራክቲች፣ ሞድሪች እና ፔሪሲች ራስን ማጋለጥ ይቆጠራል፡፡