ወልዲያ እና ፋሲል ከተማ ባደረጉት ጨዋታ በተፈጠረው የስፖርታዊ ጨዋነት ጉድለት ዋነኛ መንስኤ ናቸው ተብለው ቅጣት ከተላለፈባቸው መካከል አንዱ የሆነው አማካዩ ብሩክ ቃልቦሬ በፈዴሬሽኑ የአንድ አመት እገዳ እና የ10 ሺህ ብር ቅጣት እንደተላለፈበት ይታወሳል። ያለፉትን ሶስት ወራት በቅጣት ያሳለፈው አማካዩ ስለፈጠረበት ስሜት ቅጣቱ ስላደረሰበት ተፅዕኖ እና በይፋ ይቅርታ የሚጠይቅ መሆኑን ከሶከር ኢትዮጵያ ጋር ባደረገው ቆይታ ተናግሯል።
ቅጣቱ ምን አይነት ስሜት ፈጥሮብሀል ?
መጀመሪያ ላይ ቅጣቱን ስሰማ አስደንግጦኛል። እዚህ አይነት ደረጃ ላይ የሚያደርሰኝም አልነበረም። በሰዐቱ ምንም ያደረኩት ነገር የለም። ተጨዋቾች አነሳስተሀል ከተባልኩኝ ወይም ህዝብ አነሳስተሀል ተብዬ ከተወነጀልኩኝ በምን አይነት መልኩ የሚለው ጥያቄ መመለስ ነበረበት። ውሳኔው ግራ ነው ያጋባኝ። መቀጣቴን አስመልክቶ የደረሰኝ ወረቀትም አልነበረም። በሶከር ኢትዮጵያ ነበር ያየሁት። ቅጣቱ በጣም ነው የጎዳኝ። ከቡድኔ ጋር ጥሩ ነገርን ለመስራት እያሰብኩኝ ባለበት ሰዐት ነው የተቀጣሁት። በዚህ ምክንያትም ያሰብኩትን ማድረግ ያልቻልኩም። እኔም ሆንኩ ክለቡ ይግባኝ ብለን ነበር። የክለቡ ይግባኝ ተቀባይነት ሲያገኝ ቅጣቱም ሲቀልለት የኔ ግን ተቀባይነት እንዳላገኘ ነው የሰማሁት። ሚስጥሩ ምን እንደሆነ ግን አላውቅም። ከምችለውም በላይ ጥረት አድርግያለሁ። ወደ ሜዳ መመለስ በጣም ናፍቆኛል። እኔ ገና ወጣት ነኝ ፤ ገና አልተጫወትኩም ብዬ የማስብ ተጨዋች ነኝ። እንዲህ አይነት ጉዳይ ሲገጥመኝ ደግሞ በጣም ነው ውስጤ የተጎዳው።
ወልዲያን የተቀላቀልከው ገና ዘንድሮ ነው ፤ በመጀመሪያው አመትህ ክለብህ የደረጃው ሰንጠረዡ ግርጌ ላይ ሆኖ ላለመውረድ እየታገለ ነው ፤ አንተም ቅጣት ላይ ትገኛለህ...
ቡድኑ እንዲህ ሆኖ እኔም ቅጣት ውስጥ በመሆኔ ይሄን አመት ደስተኛ አይደለሁም። ከዚህም በላይ በታሪክ ላይ የሚፃፍም ስለሆነ የዛ አንድ አካል በመሆኔ ጥሩ ስሜት እየሰጠኝ አይደለም። ብችል ብጫወት እና ለክለቡ አንድ ነገር ባደርግ ደስ ይለኝ ነበር። ክለቡ ያለበት ደረጃ እንዲሁም ተጨዋቾቹ የሚገኙበት ስሜት ሁሉም ላይ ቁጭትን የሚፈጥር ነው።
በተደጋጋሚ በየጨዋታው የምንሰማቸው ነገሮች አሉ። “ብሩክ ከዳኛ ጋር ሰጣ ገባ ውስጥ ይገባል እና ሆን ብሎ ተጨዋቾች ይማታል።” ይባላል። እኚህ ባህሪዎቹ ተጠራቅመው ነው ለቅጣት ያበቁት የሚል አስተያየይም ይሰጣል። እዚህ ላይ ምን ትላለህ ?
ለኔ ወልዲያ የመጀመሪያ ክለቤ አይደለም። በእንደዚህ አይነት ባህሪም አልታወቅም። ድቻ እና አዳማም ተጫውቻለሁ። እንደተባለው የነገሩ መገጣጠም እንጂ በፍፁም ይህ ባህሪዬ አይደለም። እንዲህ አይነት አስተሳሰብም የለኝም። ስለኔ ባህሪ የሚያውቅ ደግሞ ሊመሰክር ይችላል። እኔ ስጫወት ሜዳ ላይ አግሬሲቭ ነኝ። መሸነፍ አልወድም ፤ ባህሪዬ ነው። ይህ ነገር ወደ ሌላ ከዞረብኝ ያ የአረዳድ ችግር ይሆናል። በግሌ በፍፁም ሽንፈትን አልወድም። ከፋሲል የተጫወትን ሰአት ምንም ያደረኩት ነገር የለም። በርግጥ አግሬሲቭ ነበርኩ። የምንጫወተው እግር ኳስ እንጂ ቴኒስ አይደለም። እንዳልከው ተጫዋቾች ይማታል ይባል ይሆናል። ሆን ብዬ ይህን ባደርግ እኔስ ምን አይነት ህሊና ነው ሚኖረኝ ? አስቤ ሜዳ ላይ ሰው ለመማታት እንዴትስ እገባለሁ ? እንዴትስ ዳኛ ላይ እንዲህ አይነት ነገር እንዲከሰት አደርጋለሁ ? ይሄ አሁን ድረስ አልገባኝም። እኔ የምችለውን ነገር አድርጌያለሁ። አንዳንዴ እንዲህ አይነት ነገር ሲያጋጥምም ፈተና ነው ፤ ለነገም ትምህርት ይሆናል ብዬ ነው ማስበው። ድቻም ሆነ አዳማ በእንቅስቃሴ ጥሩ ሆኜ ስጫወት ነው የቆየሁት። አንድም ቀን በሁለት ቢጫ ወጥቼ አላውቅም። ነገሩ ተገጣጥሞ ይህ ችግር ባይፈጠር ፤ ደጋፊም ወደ ሜዳ ባይገባ የለሚ እና የረዳት ዳኛው መመታት አይመጣም ነበር። ሆኖም በቅርቡ በወልዋሎ የተቀጡት ተጨዋቾች ቅጣታቸው ተንስቶላቸው አይተናል። ይህ ለኔስ ለምን አልሆነም እላለሁ። በእለቱ ዳኛውን አፀያፊ ንግግር እንኳን አልተናገርኩም።
ፌድሬሽኑ ቀጥቶህ አሁን ቅጣት ላይ ነህ። ምናልባት አንተ ውስጥ የጥፋተኝነት ስሜት ይኖር ይሆን ?
እኔ ለክለቤ ያለኝን ሳልሰስት ነው የምሰጠው። ምን አገባኝ ብዬ መጫወት አያቅተኝም። እንዲህ አይነት ቸልተኝነት ስለሌለብኝ መጥቀም ባለብኝ ልክ ነው የማገለግለው። ስሸነፍ የሆነ ነገሬ እንደተነካ ነው የማስበው። ግን አሁን የተማርኩት ክፉውንም ሆነ ጥሩውን ነገር ያወኩበት ዓመት ነው። የተፈጠረውን ነገር ፈፅሜያለሁ ባልልም ለክለቡ ብዬ ስጫወት ጫናው ወደኔ መጣ። እየሆነብኝ ያለውን አሁን በግልፅ አላወራም። አሜን ብዬ የተቀበልኩትም ነገር ነው። ብቻ እግዚአብሔር ፍርድ ይስጥ። ጥፋት ሆኖ ከታየብኝ ግን ይቅርታ መጠየቅ ነው የምፈልገው። ሁሉንም ይቅርታ መጠየቅ እፈልጋለሁ። ይቅርታም ደግሞ ትልቅነት ነው። ይቅርታ ጠይቄ ወደ ሜዳ መመለስ እና እኔ እንዲህ አይነት ሰው አለመሆኔን በድጋሚ ማሳየት ነው የምፈልገው። ስለኔ አመለካከቱ የተቀየረውን የስፖርት ቤተሰብ በሙሉ ይቅርታ መጠየቅ እፈልጋለሁ። ወዳጅነት ላለማጣት ስል ይቅርታን እጠይቃለሁ። እኔ እንዲህ አይነት ሰው አለመሆኔን እንዲረዱልኝም እፈልጋለሁ። በአጠቃላይ በኔ ላዘኑ ሁሉ በሶከር ኢትዮጵያ በኩል ይቅርታዬ ይድረሳቸው።
በመጀመሪያ አላጠፋሁም እያልክ ነበር መጨረሻ ላይ ደግሞ ይቅርታ እየጠየቅክ ነው። ይህ እርስ በእርሱ የሚጣረስ አይሆንም?
ጥሩ ግንኙነትን ላለማጣጣት ስል ይቅርታ እላለው። መጫወትን ስለምፈልግ አደርጌዋለው። የምፈልገውን ላለማጣት ስል መሸነፍም አለብኝ። በሰአቱ ያ ነገር እንዲፈጠር ያደረኩት በሴራ ወይንም ሆን ብዬ አይደለም። የረዳት እና ዋና ዳኛውም መጎዳት እውነት እኔ ያቀድኩትም አይደለም። እውነት ግን ጥፋተኛ ከተባልኩ ጥፋቴን አምኜ ይቅርታን ጠይቃለሁ። ነገር ግን እኔ ሆን ብዬ እንዲፈጠር አስቤ እንዳልሆነ ቢረዱኝ ደስ ይለኛል። አሁን ላይ ደሞዜ እስከመቆም ደርሷል። ለፌዴሬሽኑም ይቅርታ ብዬ ወደ ሜዳ እንድመለስ ጠይቄ ነበር። አሁን ደግሞ ለሁሉም ሰው ይቅርታዬን አደርሳለሁ።