ሞሮኮ ከ1998 የበኃላ የዓለም ዋንጫ ተሳትፎ ትኬቷን ቆርጣለች፡፡ ሞሮኮ የተመጣጠን የቡድን ስብስብ ካላቸው የዓለም ዋንጫው ተሳታፊ ሃገራት መካከል አንዷ ነች፡፡
መቀመጫውን በኔዘርላንድ ያደረገው ሞሮኮዋዊው የእግርኳስ አማካሪ እና ጋዜጠኛ ቢላል ሶፋኒ ከሶከር ኢትዮጵያ ጋር ስለሞሮኮ የዓለም ዋንጫ ተሳትፎ እና መሰል ተያያዥ ጉዳዮች ጋር ቆይታ አድርጓል፡፡
የሞሮኮን የቡድን ስብስብ እንዴት ተመለከትከው? እንደዋሊድ አዛሮ እና ሶፊያን ቡፋል ያሉ ተጫዋቾችን ሄርቬ ሬናር አልመረጡም?
እኔ እንደማምነው ሄርቬ ሬናር ወደ ዓለም ዋንጫው ይዞ ተጓዘው ጠንካራ የሆነውን የሞሮኮ የቡድን ስብስብ ነው፡፡ በዓለም ዋንጫ ማጣሪያው ለሞሮኮ ወሳኝ እና ጠቃሚ የነበሩ ተጫዋቾችን የያዘ ነው፡፡ እኚህ ተጫዋቾች ከብሄራዊ ቡድን ባሻገር ለሚጫወቱበት ክለቦች ጥሩ ግልጋሎትን በውድድር ዓመቱ ያበረከቱ ናቸው፡፡ ከውጪ ለሚመለከት የኤልካቢ ከአዛሮ ቀድሞ መመረጡ ትንሽ ግር ሊያሰኝ ይችላል ግን ዋናው ቁም ነገር ኤል ካቢ በተሻለ ለሞሮኮ አጨዋወት የሚሆን መሆኑ ነው፡፡ ኤል ካቢን መሰረት አድርጎ መጫወት ይቻላል አዛሮ ይበልጥ ተለዋዋጭ ነው፡፡ የቡፋል አለመሄድ አይደንቅም ምክንያቱም ለጨዋታ ሙሉ ለሙሉ ብቁ አይደለም፡፡
ሶስት ብቻ በቦቶላ ሊግ የሚጫወቱ ተጫዋቾች በቡድኑ ውስጥ ተካተዋል፡፡ ሞሮኮ የቻን ዋንጫን ባሸነፈች ማግስት ብዙ ተጫዋቾች ወደ ዓለም ዋንጫ እንደሚሄዱ ይጠበቅ ነበር?
ይህም ሌላ ግርምት ሊጭርብን የሚችል ጉዳይ አይደለም፡፡ በቀደምት ግዜያት አዎ ቡድናችን የሚወቀረው በሃገር ውስጥ ሊግ በሚጫወቱ ተጫዋቾች ነበር፤ በቅርብ ግዜያት ግን ይህ ተለውጧል፡፡ እኔ እንደማምነው አሁን የተመረጡት እና በውጪ ሃገር የሚጫወቱት ተጫዋቾች በአውሮፓ ትልልቅ ሊጎች እየተጫወቱ በመሆኑ ሁሌም ጠንካራ ተጋጣሚዎችን የማየት እና የመጫወት ልምድ ከሃገር ውስጥ ካሉት በተሻለ አላቸው፡፡ የዓለም ዋንጫ ደግሞ ጠንካራ ተጋጣሚዎች ያሉበት ውድድር ነው፡፡ በሃገር ውስጥ የሚጫወቱ ተጫዋቾቻችን አፍሪካ ላይ መንገስ በመቻላቸው ደስተኛ ነኝ ግን የዓለም ዋንጫው ሌላ ውድድር ነው፡፡
የአዩብ ኤል ካቢ ሽግግር ፈጣን እና አስደማሚ ነው….
ኤል ካቢ ከረፈደ በኃላ የጎመራ ተጫዋች ነው፡፡ ከአንድ አመት ከአምስት ወር በፊት ማንም ስለእሱ ማወቅ አይችልም ነበር ምክንያቱም በሁለተኛው ዲቪዚዮን ነበር የሚጫወተው፡፡ ወደ በርካን ያደረገውን ዝውውር ተከትሎ ግብ አስቆጣሪ መሆኑን አስመስክሯል፡፡ በዚህ የተነሳ ብዙ አውሮፓ እና የአረብ ክለቦች ውቅታዊ ብቃቱን በሚገባ እያጤኑት ነው፡፡ እኔ እንደሚመስለኝ በአትላስ አንበሶቹ ቡድን ውስጥም ተቀባይነት ያገኘ ተጫዋች ነው፡፡ የሞሮኮ የቡድን አጋሮቹን ማሳመን መቻሉ ይመስለኛል በቡድኑ ውስጥ ተቀባይነት እንዲገኝ ያስቻለው፡፡ የዓለም ዋንጫ ተሳትፎ ብዛት – 5 (1970፣ 1986፣ 1994፣ 1998 እና 2018)
ውጤት – በ1986 16ቱ ውስጥ መግባት ችላለች
ምድቡ ውስጥ ሁለት የአውሮፓ ሃያላን ይገኛሉ፡፡ ኢራን በአሁኑ ወቅት በእስያ ካሉ ሃያል የእግርኳስ ሃገራት መካከል ቀዳሚ ነች፡፡ ምድቡን እንዴት ተየዋለህ?
ይህ ለእኛ ሊያጋጥመን ከሚችለው የምድብ ድልድል ሁሉ ከባዱ ነው፡፡ ይህ የዓለም ዋንጫ ስለሆነ ቀላል ተጋጣሚ እንደማታገኝ ይታወቃል፡፡ ሞሮኮ በጣም ጥሩ የሆኑ ሶስት ጠንካራ ቡድኖችን ትገጥማለች፣ እርስበርሳቸውም ይጫወታሉ፡፡ ኢራን ቀላል ተጋጣሚ አይደለችም፡፡ ግን እንዴት የፊት መስመር ተሰላፊዎቻችንን እና ፈጣሪ አማካዮቻችን እንደሚቆሙ ለማየት እፈልጋለው፡፡ ፓርቹጋል ያለሮናልዶ ግብ ለማስቆጠር ስትቸገር አይተናል፡፡ ሞሮኮ ደግሞ አስካሁን ባለው ሂደት ብዙም ግብ የማይቆጠርበት የተከላካይ ክፍል አላት፡፡ ስፔን የተለየች ነች፡፡ የመጀመሪያውን ሁለት ጨዋታዎች አሸንፋ ከመጣች ለእኛ ነገሮች ጥሩ ይመስላሉ፡፡
በ1986 ሞሮኮ ጥሩ የዓለም ዋንጫን ጉዞ አድርጋለች፡፡ ይህ አሁን ላይ መደገም ይቻላል?
የሚቻልባቸው አጋጣሚዎች ይኖራሉ፡፡ ዋነኛው ይህንን እንድል ያደረገኝ መልካም የሆነው የጨዋታ ፕሮግራም ነው፡፡ ሞሮኮ ከኢራን ላይ ሶስት ነጥብ መውሰድ ትችላለች፡፡ ከፖርቹጋል ጋር ነጥብ መጋራት ይቻላል፡፡ ይህ ለሞሮኮ ወደ ቀጣይ ዙር ለማለፍ በቂ ይሆናል ስፔን ሁሉንም ጨዋታዎቿን ታሸንፋለች ብዬ ስለማስብ ነው ይሄንን ግምት የምሰጠው፡፡ ከዚህ ምድብ መውደቅም ለሞሮኮ ነውር አይሆንም ከምድቡ ክብደት አንፃር፡፡ በአፍሪካ ዋንጫው እና የዓለም ዋንጫ ማጣሪያው እንዳየነው ፈታኝ ምድቦች የሞሮኮ ተጫዋቾችን ይበልጥ ጥሩ እንዲንቀሳቀሱ ያደርጋቸዋል፡፡
የትኞቹን ተጫዋቾች እግርኳስ አፍቃሪያን ቢመለከቱ ትመክራለህ?
መልሴ አጭር ነው ሃኪል ዚየች እና ሙባራክ ብሶፋ፡፡
ዛሬ ሞሮኮ ኢራንን በመግጠም የዓለም ዋንጫ ጉዞዋን ትጀምራለች፡፡ ሙሉ ስብስብ
ግብ ጠባቂ
ሙኒር ኤል ካጁኢ (ኑማንሲያ/ስፔን)፣ ያሲን ቦኖ (ጂሮና/ስፔን)፣ አህመድ ሬዳ ታግናቲ (ኢቲሃድ ታንገ) ተከላካዮች
መህዲ ቤናቲያ (ዩቬንቱስ/ጣሊያን)፣ ሮሜን ሳኢስ (ዎልቨርሃምፕተን ወንደረርስ/እንግሊዝ)፣ ማኑኤል ዳ ኮስታ (ባሳክሸር/ቱርክ)፣ ባድር ቤኖን (ራጃ ክለብ አትሌቲክ)፣ ነቢል ድራር (ፌነርባቼ/ቱርክ)፣ አሽራፍ ሃኪሚ (ሪያል ማድሪድ/ስፔን)፣ ሃምዛ ምንዲል (ሊል/ፈረንሳይ)
አማካዮች
ሙባረክ ብሶፋ (አል ጀዚራ/የተባበሩት የአረብ ኤምሬቶች)፣ ካሪም ኤል አህመዲ (ፌይኖርድ ሮተርዳም/ኔዘርላንድ)፣ የሱፍ ቤንናስር (ኬን/ፈረንሳይ)፣ ሶፍያን አመርባት (ፌይኖርድ ሮተርዳም/ኔዘርላንድ)፣ የኑስ ቤልሃንዳ (ጋላታሳራይ/ቱርክ)፣ ፈይሰል ፋጅር (ሄታፌ/ስፔን)፣ አሚን ሃሪት (ሻልክ 04/ጀርመን)
አጥቂዎች
ካሊድ ቦታይብ (ማልታያስፖር/ቱርክ)፣ አዚዝ ቦድዶዝ (ሴንት ፖውሊ/ጀርመን)፣ አዩብ ኤል ካቢ (ሬኔሳንስ በርካን)፣ ኒረዲን አምርባት (ሌጋኔስ/ስፔን)፣ መህዲ ካርሴላ (ስታንዳርድ ደ ሊዬዥ/ብልጂየም)፣ ሃኪል ዚየች (አያክስ አምስተርዳምስ/ኔዘርላንድ)