ሪፖርት | ጅማ መሪነቱን ሲያስቀጥል ወልዲያ የከፍተኛ ሊግ በር ላይ ቆሟል

ረፋድ 4፡00 ላይ ወልዲያን ከጃማ አባ ጅፋር ያገናኘው የ27ኛው ሳምንት የአዲስ አበባ ስታድየም የመጀመሪያ ጨዋታ በአባ ጅፋር 2-0 አሸናፊነት ተጠናቋል።

እዚሁ አዲስ አበባ ስታድየም ላይ የ26ኛ ሳምንት ጨዋታቸውን ያከናወኑት ሁለቱ ቡድኖች ዛሬ መጠነኛ ለውጦችን አድርገዋል። ወልዲያ በቅዱስ ጊዮርጊስ 3-1 ከተሸነፈበት ጨዋታ ቢያድግልኝ ኤልያስ እና ኤዶም ኮድዞን በያሬድ ሀሰን እና አሳልፈው መኮንን ለውጧል። ጅማ አባ ጅፋር ግን መከላከያን ከረታበት ጨዋታ ነጂብ ሳኒን አሳርፎ መላኩ ወልዴን ያሰለፈበት ቅያሪ ብቸኛው ለውጡ ነበር።

ጨዋታው ጫን ብለው በመጫወት በጀመሩት አባ ጅፋሮች የእንቅስቃሴ የበላይነት የጀመረ ነበር። ሆኖም ጅማዎች በተመስገን ገ/ኪዳን በሁለት አጋጣሚዎች ካገኛቸው የመልሶ ማጥቃት ዕድሎች እና ኦኪኪ አፎላቢ ከርቀት በቀጥታ ከመታው የቅጣት ምት ውጪ ተጋጣሚያቸውን እምብዛም አላስጨነቁም ነበር። ቀስ በቀስ ወደ ጨዋታው የገቡት ወልዲያዎችም ዳንኤል አጄዬን የሚፈትን ሙከራ ማድረግ አልቻሉም። በጅማ ሳጥን ውስጥ ሆኖ ኳሶችን ለሚጠብቀው ዓንዱአለም ንጉሴ ተሻጋሪ ኳሶችን ከማድረስ ይልቅ ከኃላ ጀምሮ በመመስረት ወደ ውስጥ ለመዝለቅ ያሰበ የሚመስለው የቡድኑ አጨዋወት ከሜዳው ሁኔታ ጋር ተዳምሮ ፍሪያማ አልሆነም። ከተስፋዬ አለባቸው እና ምንያህል ተሾመ ተነስተው ወደ መስመር የሚላኩ ኳሶችም በብዛት ይቆራረጡ ነበር። በመሆኑም በውድድር አጋማሹ ቡድኑ ተቀላቅለው በግራ እና ቀኝ መስመር አማካይነት የተሰለፉት መስፍን ኪዳኔ እና አሳልፈው መኮንን የጃማን የመስመር ተከላካዮች አልፈው ለመግባት የሞከሩባቸው እንቅስቃሴዎች እንዳሰቡት አልሆነላቻውም። ወልዲያም የመጀመሪያውን አጋማሽ አንድም ያለቀለት የግብ ዕድል ሳይፈጥር ቀርቷል።


ከተለመደው በተለየ በማጥቃት ሂደቱ ላይ ሲሳተፍ ይታይ የነበረው የግራ መስመር ተከላካዩ ኤልያስ አታሮ 20ኛው ደቂቃ ላይ ወደ ውስጥ ከጣለው ኳስ ኦኪኪ አፎላቢ ጥሩ ዕድል ያገኘበት የማጥቃት ሂደት ለአባ ጅፋር የመጀመሪያ ነበር። በዚሁ ደቂቃ አኪኪ ከአሮን አሞሀ በተቀበለው ኳስ ንፁህ የማግባት ዕድል ቢያገኝም ቤሊንጋ ኤኖህ ፈጥኖ በመውጣት አምክኖበታል። በመከላከል ሂደት ላይ ተጋጣሚያቸው መሀል ለመሀል ለመጀመር የሚሞክራቸውን ጥቃቶች ማፈን የቻሉት ጅማዎች ፊት ላይ በተመስገን ገ/ኪዳን ጫና በመፍጠር ኳስ ይዘው በቆዩባቸው ደቂቃዎች ደግሞ ወደ ወልዲያ ሳጥን በመግባት ጫናቸውን ቀጥለው 36ኛው ደቂቃ ላይ ኦኪኪ ከሳጥን ውስጥ ወደ ጎል የሞከረው ኳስ በወልዲያ ተከላካዮች በእጅ ሲነካ የፍፁም ቅጣት ምት ማግኘት ችለዋል። ኦኪኪ አፎላቢም አጋጣሚውን ተጠቅሞ በማስቆጠር አባጅፋርን ቀዳሚ አድርጓል። ከግቡ ጥቂት ደቂቃዎች ቀድመ ብሎ ጉዳት ያስተናገደው ተስፋዬ አለባቸው በአልሳዲቅ አልማሂ የተቀየረ ሲሆን አልሳዲቅ በመሀል ተከላካይነት ጨዋታውን ሲቀላቀል ዳንኤል ደምሴ ወደ አማካይ መስመር እንዲመጣ ሆኗል። ሆኖም በቀሩት ደቂቃዎች ሌላ ጥሩ የግብ አጋጣሚ የፈጠሩት አባ ጅፋሮች ነበሩ። 44ኛው ደቂቃ ላይ ኤልያስ አታሮ በፍፁም ቅጣት ምት ክልል ውስጥ ያገኘውን ይህን ዕድል ወደ ግብነት መቀየር ሳይችል የመጀመሪያው አጋማሽ ፍፃሜ ሆኗል።


ሁለተኛው አጋማሽ ሲጀመር ወልዲያዎች የተሻለ መነቃቃት አሳይተዋል። ወደ ጅማ የሜዳ አጋማሽ አጋድለው በተጫወቱባቸው የመጀመሪያ ደቂቃዎችም ከመጀመሪያው በተሻለ ቀጥተኛ ኳሶችን ለዓንዱአለም ንጉሴ ለማድረስ ጥረት ሲያደርጉ ይታይ ነበር። 49ኛው ደቂቃ ላይ አንዷለም በረጅሙ የደረሰውን ኳስ ወደ ኃላ መልሶለት መስፍን ኪዳኔ ከርቀት የሞከረው ኳስ የቡድኑ ጥሩ ሙከራ ሆኗል። ወልዲያዎች በቀጣይም ኤዶም ኮድዞን በአሳልፈው መኮንን ቀይረው በማስገባት የቡድኑ ጥቃት ፊት ላይ የተሻለ ጉልበት እንዲኖረው ለማድረግ ሞክረዋል። ሆኖም በአመዛኙ የኤዶም ከአንዷለም ርቆ እና ለአማካይ መስመሩ ቀርቦ መጫወት የአባ ጅፋር የመሀል ተከላካዮች ብዙም ሳይቸገሩ የመከላከል ሀላፊነታቸውን እንዲወጡ በር የከፈተ ነበር። ወልዲያዎች የታየባቸው መጠነኛ መነሳሳትም ደቂቃዎች በሄዱ ቁጥር ቡድኑ ይፈጥረው የነበረው ጫና እየቀነሰ መጥቶ ከመስፍን ሙከራ ሌላ ተጨማሪ የግብ አጋጣሚዎችን ሳይፈጥር ጨዋታውን እንዲያጠናቅቅ አድርጎታል። 

የተጋጣሚያቸውን አጀማመር ማርገብ የቻሉት ጅማዎች 52ኛው ደቂቃ ላይ ኦኪኪ ከመሀል ሜዳ ጀምሮ በገፋው እና ለተመስገን አሻግሮለት በተከላካዮች በወጣው ኳስ ጥቃት መሰንዘር ጀምረዋል። ጅማዎች ኦኪኪን በቀኝ መስመር ወደ ኃላ እየተመለሰ አማካይ ክፍሉን እንዲያግዝ በማድረግ እና ድንገተኛ ጥቃቶችን በመሰንዘር የበላይነታቸውን መልሰው ማግኘት ችለዋል። በተለይ 56ኛው ደቂቃ ላይ ተመስገን ገ/ኪዳን ከአልሳዲቅ አልማሂ ቀምቶ ካሻገረውን ኳስ ኦኪኪ አፎላቢ ወደ ግብነት ለመቀየር ተቃርቦ ነበር። በይሁን እንዳሻው መሪነት ለተከላካይ ክፍሉ በቂ ሽፋን ይሰጥ የነበረው የቡድኑ አማካይ ክፍል በማጥቃቱም ወደ ወልዲያ የሜዳ ክልል ተጭኖ መጫወት እምብዛም አልከበደውም። ከዚህ በመነሳትም ከረጅም ርቀት የተገኘን የቅጣት ምት አዳማ ሲሴኮ መቶ ካመከነው ከደቂቃዎች በኃላ ከተመሳሳይ ቦታ ላይ ሌላ ቅጣት ምት ሲሰጥ በአግባቡ ተጠቅመውበታል። ይሁን እንዳሻው በቀጥታ ከመምታት ይልቅ ከወልድያ የመከላከል አጥር በላይ ከፍ አድርጎ ሲጥልለት አሮን አሞሀ በጠንካራ ምት ሁለተኛውን ግብ ማስቆጠር ችሏል። ከ2 ደቂቃዎች በኃላ በኦኪኪ የሳጥን ውጪ ኳስ ሌላ ሙከራ ያደረጉት አባ ጅፋሮች እስከ መጨረሻው ወደ ፊት ገፍተው በመጫወት ጫና ሳይሰማቸው ጨዋታውን ጨርሰዋል። በመጨረሻዎቹ አስር ደቂቃዎች ደግሞ ንጋቱ ገ/ስላሴን በይሁን እንዳሻው ለውጠው በማስገባት መሀል ሜዳውን ለወልዲያ የበለጠ ከባድ አድርገውታል። የመጨረሻ በነበረው ክስተትም አዳሙ መሀመድ በተመስገን ላይ በሰራው ጥፋት በሁለተኛ ቢጫ ካርድ ወጥቶ ተጨማሪ ግብ ሳንመለከት ጨዋታው ፍፃሜውን አግኝቷል።

ጅማ አባ ጅፋር ባሳካው ድል በሶስት ነጥብ ርቀት ሊጉን መምራት የጀመረ ሲሆን 20 ነጥቦች ላይ የቀረው ወልዲያ በዚሁ ሳምንት በሚደረጉ ጨዋታዎች ላይ ተመስርቶ መውረዱን የሚያረጋግጥበት ዕድል በጣሙን ሰፊ ሆኗል።