ሪፖርት | አጼዎቹ ከ6 ጨዋታ በኋላ የጎል እና የአሸናፊነት መንገዱን አግኝተዋል

በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 27ኛ ሳምንት ጎንደር አጼ ፋሲለደስ ስታዲየም ላይ ሲዳማ ቡናን ያስተናገደው ፋሲል ከተማ 2-1 በማሸነፍ ከ6 ተከታታይ ድል እና ጎል አልባ ጨዋታ በኋላ ወደ አሸናፊነት ተመልሷል።

በፋሲል በኩል ባለፈው ሳምንት አዲስ አበባ ላይ መቐለ ከተማን ከገጠመበት አሰላለፍ  በአምስት ቢጫ ምክንያት ያልተሰለፈው ይስሀቅ መኩሪያን በሙሉቀን አቡሀይ፣ ከረጅም ጊዜ ጉዳት የተመለሰው ያሬድ ባየህን በከድር ኸይረዲን ምትክ ወደ ሜዳ ይዞ ሲገባ በሲዳማ በኩል  ባለፈው ሳምንት በሜዳው ድሬዳዋን 1-0 ካሸነፈው ስብስብ አዲስዓለም ደበበን በወንድሜነህ አይናለም በመተካት ነበር ወደሜዳ  የገቡት።

በመጀመሪያው አጋማሽ ፋሲሎች ተጭነው በመጫወት ገና በጨዋታው ጅማሬ ደቂቃዎች የግብ አጋጣሚዎችን መፍጠር ችለዋል። 6ኛው ደቂቃ ላይ ፊሊፕ ዳውዝ ከሳጥን ውጭ ያገኘውን ኳስ በመግፋት ፍፁም ቅጣት ምት ሳጥን ውስጥ ይዞ ገብቶ የሞከረውን ኳስ ግብ ጠባቂው ሲያድንበት በ13ኛ ደቂቃ ላይ በድጋሚ ራምኬል ከርቀት አክርሮ የመታውን ኳስ መሴይ አድኖበታል። ሆኖም ከሙከራዎች ባሻገር ግብ በማስቆጠር ቅድሚያውን መያዝ የቻሉት ሲዳማ ቡናዎች ነበሩ። ወንድሜነህ ዓይናለም 15ኛው ደቂቃ በቀኝ በኩል ከርቀት አክርሮ በመምታት ድንቅ ግብ አስቆጥሮ እንግዶቹን መሪ ማድረግ ችሏል።

ፋሲል ከተማዎች ጎል ከተቆጠረባቸው በኋላ የመጀመርያዎቹ ደቂቃዎች ላይ የነበራቸው የኳስ ቁጥጥር የበላይነት ጠፍቶ ረጃጅም ኳሾችን በመጣል ጎል ለማግኝት ጥረት ቢያደርጉም መሐመድ ናስር እና ፊሊፕ ዳውዝ በተደጋጋሚ ከጨዋታ ውጭ ሲሆኑ ታይቷል። 28ኛ ደቂቃ ላይ  ከሲዳማ ተከላካዮች ተገጭቶ የተመለሰን ኳስ ሙሉቀን አብሀይ ወደ ግብ ሲመታ የሲዳማ ብናው ዮናታን ፍስሀ በእጅ በመንካቱ የተገኘውን የፍፁም ቅጣት ምት ራምኬል ሎክ ወደ ግብ ቀይሮ ፋሲልን አቻ ማድረግ ችሏል። በጎሉ የተነቃቁት አጼዎቹ   መሪ የሚያደርጋቸውን ሁለተኛ ጎል ለማግኘት ሰባት ደቂቃ ብቻ ነበር የፈጀባቸው። በ35ኛው ደቂቃ ኤፍሬም ዓለሙ እና መሐመድ ናሰር ተቀባብለው ወደ ሳጥን ይዘው በመግባት ከግብ ጠባቂው ጋር አንድ ለአንድ የተገናኘው ኤፍሬም ዓለሙ በድንቅ አጨራረስ ቡድኑን መሪ ማድረግ ችሏል።

41ኛ ደቂቃ ላይ ያሬድ ባየህ የተጨረፈበትን ኳስ  አዲስ ግደይ አግኝቶት ወደግብ  ይዞ በሚሄድበት ስዓት ግማሽ ጨረቃው ላይ ከኋላ ይዞ በማስቀረቱ በቀይ ካርድ ከሜዳ ወጥቷል። ከረጅም ጊዜ ጉዳት በኋላ ወደሜዳ የተመለሰው ያሬድ ከአርባ ደቂቃ በላይ መጫወት ሳይችል በቀጥታ ቀይ ካርድ ከሜዳ ለመውጣት ተገዷል። የተገኘውን የቅጣት ምት ወንድሜነህ ዓይናለም ሳይጠቀምበት ቀርቶ የመጀመርያው አጋማሽም በፋሲል መሪነት ተገባዷል።

ሁለተኛውን አጋማሽ ፋሲሎች በጎደሎ ተጫዋቾች ቢጀምሩም የተሻለ እንቅስቃሴ ማሳየት ችለዋል። 61ኛው ደቂቃ ላይ ከማዕዘን የተሻገረውን ኳስ ራምኬል ሎክ በጭንቅላቱ ገጭቶ ቢያስቆጥርም  ግብ ጠባቂው ላይ ጥፋት በመስራቱ ሳይፀድቅ ሲቀር 67ኛው ደቂቃ ላይ በመልሶ ማጥቃት ያስር ሙገርዋ ይዞት የገባውን ኳስ ለኤፍሬም ዓለሙ አቀብሎት ወደ ውስጥ ሲገባ በድጋሚ ያሻገረለትን ኳስ ግብ ጠባቂው ቀድሞ አውጥቶታል። 69ኛው ላይ ራምኬል ሎክ ከርቀት አክርሮ መትቶ መሳይ ያወጣበት፣ 75ኛው ደቂቃ ላይ ራምኬል ሎክ የግብ ቋሚ የመለሰበት፣ 89ኛው ደቂቃ ላይ ያስር ሙገርዋ ከቀኝ መስመር የመታውና ተከላካዮች ተደርበው ያወጡበት እንዲሁም በጭማሪ ደቂቃ ላይ ኤፍሬም ዓለሙ ከአብዱራህማን ሙባረክ የተሻገረለትን ኳስ የመጨረሻ ተከላካይ አልፎ የመታው የግቡን የግራ ቋሚ ታኮ የወጣበት በሁለተኛው አጋማሽ በፋሲል ከተማ በኩል የሚጠቀሱ ሙከራዎች ነበሩ።

በዚህኛው አጋማሽ ተቀዛቅዘው በመጨረሻዎቹ ደቂቃዎች ላይ መነቃቃት ባሳዩት ሲዳማዎች በኩል ሐብታሙ 72ኛው ደቂቃ ላይ በግራ የፍፁም ቅጣት ክልል ውስጥ አክሮ መቶት ቋሚውን ታኮ ሲወጣበት በ75ኛው ደቂቃ ይገዙ ቦጋለ ከማዕዘን የተሻማውን ኳስ በግንባሩ ገጭቶ ሚኬል ሳማኬ በቀላሉ ያወጣበት ሙከራዎች ተጠቃሽ ናቸው።

ፋሲል ከተማ ድሉን ተከትሎ ፋሲል ከተማ በ38 ነጥብ 6ኛ ላይ ተቀምጦ ከመውረድ ስጋት ነፃ መሆን ሲችል ሲዳማ ቡና በ32 ነጥቦች 10ኛ ደረጃ ላይ በመቀመጥ ወራጅ ቀጠናውን በቅርብ ርቀት እየተመለከተ ይገኛል።

አሰልጣኝ መሳይ ተፈሪ – ፋሲል ከተማ

ጨዋታው ጥሩ ነበር። ባለፉት ሶስት ጨዋታዎች ቡድናችን ጥሩ ነበር። ዛሬ ደግሞ ግብ አስቆጥረን  መውጣት ችለናል። ረጅሙን ሰዓት በጎደሎ ተጫዋች ነበር ስንጫወት የነበረው፤ እናም ተጫዋቾቼ ዋጋ ከፍለዋል። ትልቁ ጠንካራው ጎን ቡድናችን በሞራል ነው የሚጫወተው። የተገጣሚያችን ክፍተት እያየን ነው ስንጫወት የነበረው። ከዚ በፊት ጎል መግባት አልቻልንም ነበር። ዛሬ የገባው ጎል አይታችኋል፤ አንድ ሁለት ተቀባብለው ነው ያገቡት። ያ ጠንካራ ጎናችን ነው። ያየናቸውን ክፍተቶች አሉ። እነሱ ላይ በቀጣይ እንሰራለን። በቀጣይ ባሉት ሶስት ጨዋታዎች ለክብራችን እንዲሁም ለክለበባችን ስም ስንል ጠንክረን እንሰራለን ።

* የሲዳማ ቡናን አሰልጣኝ አስተያየት ማግኘት አልቻልንም።