ወልዲያ በይፋ መውረዱን አረጋገጠ

የድሬዳዋ ከተማ እና ኢትዮ ኤሌክትሪክ ጨዋታ በአቻ ውጤት መጠናቀቁን ተከትሎ ወልዲያ የመጀመሪያው ከሊጉ መውረዱን ያረጋገጠ ቡድን ሆኗል።

ዛሬ ረፋድ 4፡00 ላይ በአዲስ አበባ ስታድየም ከመሪው ጅማ አባ ጅፋር ጋር ተገናኝቶ 2-0 የተረታው ወልዲያ በሂሳብ ስሌት በሊጉ የመቆየት ጠባብ ዕድል ይዞ ቆይቶ ነበር። ሆኖም 11፡00 ላይ ያለግብ የተጠናቀቀው የድሬዳዋ ከተማ እና የኢትዮ ኤሌክትሪክ ጨዋታ ወልዲያን ወደ ከፍተኛ ሊግ የሸኘ ሆኗል። በሊጉ የሶስት ሳምንት ጨዋታዎችን ማድረግ የሚቀረው ወልዲያ ሊያስመዘግብ የሚችለው ከፍተኛ የነጥብ ስብስብ 29 በመሆኑ እና ከወራጅ ቀጠናው ውጪ የሚገኙት ወላይታ ድቻ ፣ ድሬዳዋ ከተማ እና ወልዋሎ ዓ.ዩ 30 ነጥብ ላይ በመድረሳቸው በሊጉ የመቆየት ህልሙ ሊያከትም ችሏል።

በ2007 የውድድር አመት ሊጉን ተቀላቅሎ በዛው አመት 16 ነጥቦች ብቻ ይዞ ተመልሶ የወረደው ወልዲያ በ2008 በአሰልጣኝ ንጉሴ ደስታ መሪነት ዳግም ወደ ፕሪምየር ሊጉ በማደግ በጠንካራ መከላከል ላይ ተመስርቶ እና ዝቅተኛ ግብ ካስተናገዱ ቡድኖች መሀከል አንዱ በመሆን 7ኛ ደረጃን ይዞ ማጠናቀቅ ችሎ ነበር። ዘንድሮም በርካታ ተጨዋቾችን በማስፈረም ተጠናክሮ ቢቀርብም በተለያዩ ችግሮች የታጀበው ያልተረጋጋ ጉዞው መጨረሻው እንዳያምር አድርጎታል። ቡድኑ በሁለተኛው ዙር ብቻ አስር ሽንፈቶች ያስተናገደ ሲሆን ከ20ኛው ሳምንት በኃላ ምንም ነጥብ ማግኘት አልቻለም።