ኮፓ ኮካ ኮላ ሀገር አቀፍ የህፃናት እግር ኳስ ውድድር ነገ ይጠናቃል

(ይህ ዜና የተላከው ከኢትዮጵያ እግርኳስ ፌድሬሽን የህዝብ ግንኙነት ነው)

 

በዘጠኝ ክልላዊ መስተዳድሮች እና በሁለት የከተማ አሰተዳደሮች 22 ቡድኖች መካካል ከነሃሴ 16 ቀን 2007 ዓ.ም ጀምሮ በአዳማ አበበ በቂላ እና በአዳማ ዪኒቨርስቲ ስታድየሞች ሲካሄድ የሰነበተው ኮፓ ኮካ ኮላ የመጀመሪያው ሀገር አቀፍ የታዳጊ ህፃናት እግር ኳስ ውደድር በሁለት የፍፃሜ እግር ኳስ ውድድሮች እንዲሁም በተለያዩ ደማቅ የመዝጊያ ስነ ስርዓቶች ታጅቦ ነገ ነሃሴ 24 ቀን 2007 ዓ.ም ይጠናቃቃል፡፡
የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን እና የፌዴራል ስፖርት ኮሚሽን ከኮካ ኮላ ኢንተርናሽናል ኩባንያ/ COCA-COLA CENTRAL EAST AND WEST AFRICA LIMITED/ጋር በመተባበር ያዘጋጁትና በአይነቱ የመጀመሪያ በሆነው ሀገር አቀፍ ውድድር ላይ የዘጠኙ ክልላዊ መስተዳድሮች እንዲሁም የሁለት ከተማ አስተዳደሮች ምርጥ 22 የህፃናት ቡድኖች በሁለቱም ፆታ ተካፋይ ሆነውበታል፡፡
ተተኪና ልዩ ተሰጥኦ ያላቸውን ምርጥ ተጫዋቾችን በስፖርት አካዳሚዎች ለማሰልጠን የሚስችል ምልመላ በተካሄደበት በዚህ ሀገር አቀፍ ውድድር በክልል እና በከተማ አስተዳድሮች ደረጃ በ64 የወንዶች እና በ54 የልጃገረዶች ቡድኖች መካከል የማጣሪያ የውስጥ የተካሄደ ሲሆን በምርጦቹ 22 ቡድኖች መካካል ባለፈው ቅዳሜ የተጀመረው ሻምፒዮና ነገ ከጠዋቱ 3፡00 ጀምሮ በአዳማ ዪኒቨርስቲ ስታድየም በሚካሄዱ ሁለት የፍጻሜ ግጥሚያዎች እንደሚጠናቀቅ ይጠበቃል፡፡በስድስት ምድቦች ተከፍሎ ለሰባት ቀናት በተካሄዱት የዙር እና የጥሎ ማለፍ ውድድሮች በወንዶች የኢትዮጵያ ሶማሌ እና የአፋር እንዲሁም በልጃገረዶች የአማራ እና የኦሮሚያ ቡድኖች ለፍፃሜው የዋንጫ ጨዋታዎች መድረስ ችለዋል ፡፡
በመዝጊያው ስነ ስርዓት ላይ ልዩ የሙዚቃ እና የዳንስ ትርኢት የሚቀርብ ሲሆን ለአሸናፊ ቡድኖች ለተሳታፊዎች በተጨማሪም ለኮከብና ምስጉን ስፖርተኞች የዋንጫ የሜዳሊያ እንዲሁም የተለያዩ የማበረታቻ ሽልማቶች ኮካ ኮላ ኩባንያ ማዘጋጀቱን ለማወቅ ተችሏል፡፡ውድድሩን በተሳካ ሁኔታ ለማካሄድ በኮፓ ኮካ ካላ ኢንተርናሽናል ኩባንያና በኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን መካከል ሁሉን አቀፍ ስምምነት በግንቦት 2007 ዓ.ም የተፈረመ ሲሆን የውድድሩ አጠቃላይ ወጪ በኮካ ኮላ ኩባንያ ስፖንሰርነት ተሸፍኗል፡፡

ያጋሩ