ሆሳዕና ከነማ ወሳኝ ተጫዋቾቹን በማቆየት ተጠምዷል

በድሬዳዋ ከተማ በተካሄደው የብሄራዊ ሊግ የማጠቃለያ ውድድር 2ኛ ደረጃን በመያዝ ለ2008 የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ማለፉን ያረጋገጠው ሆሳዕና ከነማ ለከርሞ በፕሪሚየር ሊጉ ለሚጠብቀው ፈተና የተጫዋቾቹን ውል በማደስ እየተዘጋጀ ይገኛል፡፡ የሆሳዕና ከነማ አሰልጣኝ ግርማ ታደሰ ተጫዋቾቻቸው ወደ ሌሎች ክለቦች እንዳይጓዙ በውል ማደስ ላይ መጠመዳቸውን ለሶከር ኢትዮጵያ በሰጡት አስተያየት ጠቁመዋል፡፡
‹‹አዳዲስ ተጫዋቾች ለማምጣት እንቅስቃሴ እያደረግን ቢሆንም ትኩረት አድርገን እየሰራን ያለነው ያሉንን ወሳኝ ተጫዋቾች በማቆየት ላይ ነው፡፡ በርከታ የሊጉ ታላላቅ ክለቦች ተጫዋቾቻችንን ለማስፈረም ፍላጎት እያሳዩ ነው፡፡ ከፍተኛ ገንዘብ እየቀረበላቸው በመሆኑም የመሄድ ጉጉት አለባቸው፡፡ ስለዚህ የቡድን ስብስቡ እንዳይበታተን ስለምፈልግ በገንዘብ ዙርያ ተደራድረን ያስቀረናቸው ተጫዋቾች አሉ፡፡ ዛሬም ሌሎች 3 የነቡድኔ ወሳኝ ተጫዋቾችን አሳምነን ውላቸውን እንዲያድሱ እናደርጋለን ብለን እንጠብቃለን፡፡ ›› ብለዋል፡፡
አሰልጣኙ አዳዲስ ተጫዋቾችን በማስፈረም በቡድናቸው ላይ የፕሪሚር ሊግ ልምድ ለማከል እየተንቀሳቀሱ እንደሆነም ተናግረዋል፡፡
‹‹ በፕሪሚየር ሊጉ ለመፎካከር ባሉን ተጫዋቾች ብቻ ሳይሆን የሊጉ ልምድ ያላቸው ተጫዋቾችን ማስፈረም እንፈልጋለን፡፡ ለቡድኑ የሚመጥኑ እና ለቡድናችን ልምድ ሊጨምሩ የሚችሉ ተጫዋቾች እናስፈርማለን፡፡ በቀጣዮቹ ቀናት ልምድ ያላቸው 3 ተጫዋቾችን እናስፈርማለን ብለን እንጠብቀለን፡፡ እስከ አርብ ባለው ጊዜ ተጫዋቾችን አስፈርመን እናሳውቃለን፡፡›› ሲሉ ሀሳባቸውን አጠቃለዋል፡፡

ያጋሩ