በሩሲያ አስተናጋጅነት እየተካሄደ የሚገኘው የዓለም ዋንጫ የምድብ ጨዋታዎች ቀጥለው እየተደረጉ ይገኛሉ፡፡ አስካሁን ባለው አፍሪካን የወከሉት ሶስት ሃገራት ግብ ሳያስቆጥሩ ሽንፈትን አስተናግደው ውድድራቸው ጀምረዋል፡፡
ከ2006 በኃላ የዓለም ዋንጫ ተሳትፎ ትኬቷን መቁረጥ የቻለችው ቱኒዚያ የዓለም ዋንጫ ጉዞዋን ዛሬ እንግሊዝን በመግጠም ትጀምራለች። በዓለም ዋንጫው ከካርቴጅ ንስሮቹ የሚጠብቃቸውን ፈተና እና መሰል ተያያዥ ጉዳዮች ቱኒዚያዊው ጋዜጠኛ ሎትፊ ዋዳ ከሶከር ኢትዮጵያ ጋር ቆይታ አድርጓል፡፡ ዋዳ የካፍ የዓመቱ ምርጥ ተጫዋች ምርጫ ላይ የሚዲያ ኤክስፐርቶች ፓናል አባል በመሆን እየሰራ የሚገኝ ጋዜጠኛ ነው፡፡
የቱኒዚያን የዓለም ዋንጫ የቡድን ስብስብ እንዴት አገኘኸው?
በቅርብ ጊዜያት ከነበሩ በጣም ጥሩ የሆነው ስብስብ ይሄ ነው፡፡ ካለንበት ወቅታዊ ሁኔታ አንፃር ወጣቶች የሚገኙበት በሁሉም የሜዳ ክፍል በቴክኒክ ብቃታቸውን የላቁ ተጨዋቾ በሁሉም የሜዳ ክፍል ላይ የሚገኙበት ቡድን ነው፡፡ የሚያሳዝነው በማጣሪው ቁልፍ ሚና የነበረው ኮከቡ ተጨዋች የሱፍ ሳክኒ እና በቅርብ ዓመታት በአፍሪካ ውስጥ ካየናቸው ምርጥ አጥቂዎች መካከል የሆነው የኤስፔራንሱ አጥቂ ጠሃ ያሲን ኬኔሲ በጉዳት አለመኖራቸው ነው፡፡
የሳክኒ እና ኬኔሲ አለመኖር ቡድን ላይ የሚፈጥረውን ክፍተት አሰልጣኝ ነቢል ማሎል እንዴት ለመሸፈን አስበዋል?
የዓለም ዋንጫው ነው ለዚህ መልስ የሚሰጠው፡፡ ነገር ግን ማሎል ያለሁለቱ የተለያዩ ታክቲኮችን በአቋም መለኪያ ጨዋታዎች ሞክረዋል፡፡ መጋቢት ወር ላይ ከኮስታ ሪካ እና ኢራን ጋር በተደረጉ የአቋም መለኪያ ጨዋታዎች ላይ የሬን አጥቂ የሆነው ዋሂብ ካዝሪ የሃሰተኛ 9 ቁጥር ሚናን ተሰጥቶት ነበር፡፡ ነኢም ስሊቲ ደግሞ ሳክኒ ሲኖር ከነበረው ይልቅ በማጥቃቱ ላይ ይበልጥ ሃይል እና ነፃነት ተሰጥሎት እንቅስቃሴዎች ለማድረግ ሲጥሩ ተስተውሏል፡፡
የቱኒዚያ ብሄራዊ ቡድን ጨዋታ ቀያሪ የለውም ብለው የሚከራከሩ አሉ፡፡ ቡድኑ የከዋክብት እና መሪ እጥረት እውን አለበት?
እኔ እንደማስበው የሚያስፈልገን ሁለት መሪ ነው፡፡ አንድ የቴክኒክ መሪ ነው፡፡ ይሄን ሚና ካዝሪ መወጣት የሚችል ይመስለኛል፡፡ ከጎኑ ያሉት ተጨዋቾች እየገፋ ወደ ጥሩ እንቅስቃሴ የሚያስገባ ከሆነ፡፡ አንድ ደግሞ ከኃላ መስመር የሚጫወት በስነ-ልቦናው የሚደራጅ መሪ ያስፈልጋል፡፡ እውነት ለመናገር ከሳክኒ በኃላ ጨዋታ ቀያሪ ተጨዋች በቡድኑ ውስጥ የለንም፡፡ ካዝሪ እና ስሊቲ ጥሩ ጨዋታ ቀያሪ ቡድን ናቸው ግን ይሄ በአፍሪካ ደረጃ ነው፡፡ የዓለም ዋንጫው ደግሞ ከዚህ የተለየ ነው፡፡
የዓለም ዋንጫ ተሳትፎ ብዛት – አምስት (በ1978፣ 1998፣ 2002፣ 2006 እና 2018)
የሚጠቀስ ውጤት – የምድብ ተፋላሚ
አሰልጣኝ ማሎል በቡድኑ ውስጥ ያመጣው ለውጥ ምንድነው?
በአዕምሮ ደረጃ ቡድኑ ጠንካራ ነው፡፡ በኪንሻሳ እና ኮናክሬ ከኃላ ተነስተን ያሸነፍንበት ሁለት የማጣሪያ ጨዋታዎች ለዚህ በቂ ምስክር ናቸው፡፡ በቴክኒክ እና ታክቲክ ረገድ ቡድኑ አፈግፍጎ ከመከላከል ይልቅ አሁን በደንብ ኳስን ይይዛል፡፡ በእርግጥ ይሄ በ2017 አፍሪካ ዋንጫ በሄንሪ ካስፐርዣክ ጊዜ የተጀመረ ቢሆንም ማሎል ይሄን ይበልጥ አበልፅጎታል፡፡
ስለምድባችሁ ምን ታስባለህ ቱኒዚያ ከምድብ የማለፍ እድል ይኖራታል?
ተዐምር ያስፈልገናል ከዚህ ምድብ ወደ ጥሎ ማለፉ ዙር ለማለፍ፡፡ እንግሊዝ እና ቤልጂየም ስታዩ ከእኛ በጣም በርቀት ላይ የሚገኙ ቡድኖች ናቸው፡፡ ግን መጀመሪያ ፓናማን ድል አድርገን ለአርባ አመታት የቆየውን በዓለም ዋንጫው ያለማሸነፍ ጉዟችንን እንግታ፡፡ በመጀመሪያው ዙር የምንወድቅ ይመስለኛል ግን ብሳሳት ደስ ይለኛል፡፡ ቢያንስ ነጥቦችን ብናሳካ እና በቅርብ ግዜያት ስናሳይ የነበረውን እንቅስቃሴ አሁንም ብንደግም መልካም ይመስለኛል፡፡
የትኛውን ተጨዋች ተመልከቱ ትለናለህ?
በወቅታዊ ብቃቱ መልካም የሆነውን ነኢም ስሊቲ፣ በተከላካይ መስመር የሚሰለፈው ያሲን ሜራህ፣ በአማካይ ክፍል ላይ ከመሃመድ አሚን ቤን አሞር ወይም ኤልየስ ስኪሪ አንዱን ቢመለከቱ እመክራለው፡፡
ሙሉ የቡድን ስብስብ
ግብ ጠባቂዎች
ፋሩቅ ቤን ሙስጠፋ (አል ሸባብ/ሳውዲ አረቢያ)፣ ሞይዝ ሃሰን (ቻትሮ/ፈረንሳይ)፣ አይመን ማትሎቲ (አል ባታን/ሳውዲ አረቢያ)
ተከላካዮች
ራሚ ቤዶኢ (ኤትዋል ደ ሳህል)፣ ዮሃን ቤናሎአን (ሎስተር ሲቲ/እንግሊዝ)፣ ሲያም ቤን የሱፍ (ካሲምፓሳ/ቱርክ)፣ ዲሊያን ብሮን (ጌንክ/ቤልጂየም)፣ ኦሳማ ሃዳዲ (ዲዮን/ፈረንሳይ)፣ አሊ ማሎል (አል አህሊ/ግብፅ)፣ ያሲን ሚራህ (ሴፋክሲየን)፣ ሃሚድ ናጉዝ (ዛማሌክ /ግብፅ)
አማካዮች
አኒስ ባድሪ (ኤስፔራንስ)፣ መሃመድ አሚን ቤን አሞር (አል አሃሊ ሪያድ/ሳውዲ አረቢያ)፣ ጋይላን ቻላሊ (ኤስፔራንስ)፣ አህመድ ካሊል (ክለብ አፍሪካ)፣ ሰይፈዲን ካውኪ (ትሮይስ/ፈረንሳይ)፣ ፈርጃኒ ሳሲ (አል ናስር/ሳውዲ አረቢያ)፣ ኤልየስ ስኪሪ (ሞንፔሌ/ፈረንሳይ)፣ ነኢም ስሊቲ (ዲዮን/ፈረንሳይ)፣ ባስም ስራርፊ (ኒስ/ፈረንሳይ)
አጥቂዎች
ፋክረዲን ቤን የሱፍ (አል ኢቲፋቅ/ሳውዲ አረቢያ)፣ ሳብር ካሊፋ (ክለብ አፍሪካ)፣ ዋሂብ ካዝሪ (ሬን/ፈረንሳይ)