አሰልጣኝ ዘላለም ሽፈራው በወልዲያ መውረድ ዙርያ ይናገራሉ

በተለያዩ ውስብስብ ችግሮች የተነሳ ያልተረጋጋ የውድድር ዓመት ያሳለፈው ወልዲያ ባሳለፍነው ሳምንት ወደ ከፍተኛ ሊግ መውረዱን ማረጋገጡ ይታወሳል። ቡድኑን ከ23ኛ ሳምንት ጀምሮ የተረከቡት አሰልጣኝ ዘላለም ሽፈራው ከተሾሙበት ጊዜ ጀምሮ ስለነበሩ ሂደቶች እና ተያያዥ ሀሳቦች ከሶከር ኢትዮጵያ ጋር ቆይታ አድርገዋል።

የወልዲያ መውረድ ምክንያቶች

በጣም ብዙ ችግሮች ነበሩበት። በመጀመሪያ እኔ ቡድኑን ከመረከቤ በፊት የነበረውን በዝርዝር ላስቀምጥ

1. ከፍተኛ የሆነ የዲሲፒሊን ችግር ነበር። ህዝቡ ፣ የቦርድ አመራሩ እና የደጋፊ ማህበሩ ጭምር የሚያውቀው ከፍተኛ ችግር ነበር። ከዚህ ቀደም በሆቴል ለማዕድ ሲገኙ ስድስት ተጨዋቼች እንኳን አንድ ላይ የማይመገቡበት ከፍተኛ የግሩፕ መከፋፈል ነበር። በጨዋታ መሀል ቀይ ካርዶችን አብዝተው ይመለከቱ የነበሩ ተጨዋቾችም ነበሩ።

2. ቡድኑ ውስጥ ከፍተኛ የሆነ የስኳድ ጥራት ችግር ነበር። ለዚህም እንደማሳያ ሁለተኛው ዙር ላይ ቡድኑን ያጠናክራሉ ተብለው የመጡትን ተጨዋቾች መመልከት ጥሩ ነው። ለምሳሌ ሞገስ ታደሰ አቅም ያለው ተጨዋች እንደሆነ ይታወቃል ሆኖም ወደ ወልድያ መጥቶ ምንም ጨዋታ አላደረገም። ሌሎች የመጡ ተጨዋቾችንም ስታይ ከመስፍን ኪዳኔ በስተቀር ከቀድሞ ክለባቸው የተቀነሱ ፣ ጉዳት ላይ የነበሩ እና ይሄን አመት ፈፅመው ያልተጫወቱ ናቸው። ወልድያ የጉዳተኞች ምሽግ ወይም ማገገሚያ ካምፕ የሆነ ነው የሚመስለው። ሁለተኛው ዙር ላይ መስፍን ኪዳኔ ብቻ ነው አብዛኛው ጨዋታዎች ላይ በመጫወት ክለቡን ማገልገል የቻለው። በውድድሩ አጋማሽ የሚፈርሙ ተጨዋቾች ቡድኑን የሚያግዙ መሆን ሲገባቸው እንዲሁ ተቀምጠው ደሞዝ የሚቀበሉት መብዛታቸው ከፍተኛ ችግር ሆኖ አልፏል።

3. ሌላው ችግር ጉዳት ነው። ተስፋዬ አለባቸውን ማንሳት ይቻላል። እሱ ከመጣ ጀምሮ በተጫወተባቸው ሁለት ጨዋታዎች ባሳየው እንቅስቃሴ ምን ያህል ለቡድኑ እንደሚጠቅም መገንዘብ ይቻላል። ሜዳ ውስጥ ሆኖ ሌሎችን እንዴት ይመክር እና ያነሳሳ እንደነበረ ስታይ ባይጎዳ ኖሮ ቡድኑን ምን ያህል እንደሚጠቅም ታስባለህ። ሌሎችም እንዲሁ በጉዳት ከቡድኑ ስብስብ ውጪ መሆናቸው ትልቅ ችግር ነበር። ከዚህ ጋር በተያያዘ በሚነሳው ሌላ ችግር አንድ ክለብ ተጨዋች ሲቀጥር ተደባደብልኝ ብሎ አይቀጥርም። አንድም የተጨዋቹ የራሱ ችግር አለ። የብሩክ ቀልቦሬን ቅጣት ማለቴ ነው። ክለቡ ከፍተኛ ገንዘብ እያወጣብህ እየደበደብክ እና እያስበጠበጥክ ክለቡ ጤናማ ሆኖ መሄድ አይችልም ፤ ይህ ሌላው ችግር ነበር።

4- ክለቡ ከሜዳው ውጪ እንዲጫወት መደረጉ ሌላው ችግር ነበር። ይህ ደግሞ በቡድኑ ውጤት ማጣት ውስጥ በግልፅ የታየ ነው። ምክንያቱም በተፈጠረው ችግር የተነሳ ከሜዳው ውጪ እንዲጫወት መደረጉ ክለቡ በሜዳው ተጫውቶ የሚያገኘውን ጥቅም ያሳጣ ነው። እንደሰማሁት ከሆነ ተጨዋቾቹ ወልዲያ ላይ ሲጫወቱ እና ሌላ ሜዳ ሲጫወቱ አቋማቸው የተለያየ ነው። 

5. በቡድኑ ውስጥ በቢጫ ቴሴራ (መታወቂያ) የሚጫወቱ ምንም አይነት የተስፋ ቡድን ተጨዋቾች አለመኖራቸውም ትልቁ ችግር ነበር። በተስፋ ቡድን የሚጫወቱ ተጨዋቾችን የምታመጣበት ዋና አላማ በጉዳት አልያም በቅጣት ተጨዋቾች ሲጎሉብህ ለመተካት ነው። እዚህ ግን የተስፋ ቡድን የለም እንዲያውም የሚገርመው በቢጫ ቴሴራ ተጨዋች አምጡልኝ ስል ‘የምን ቢጫ ቴሴራ ነው ?’ ብለው የመለሱልኝ ሰዎች አሉ። ወልዲያ ላይ ተጨዋች ጠፍቶ ነው ? አይመስለኝም። ይህ ትልቅ ችግር ሆኖብናል። ለተጨዋች ማስፈረሚያ ከሚያወጣው ከፍተኛ ወጪ ቀንሶ በአካባቢው የተስፋ ቡድን ተጨዋቾች ላይ ስራ ሊሰራ ይገባል። ከመሰረተ ልማት ጎን ለጎን ለእግርኳሱ ትኩረት በመስጠት በአካባቢው ታዳጊ ተጨዋቾች ላይ መሰራት አለበት።

6. ከ65% በላይ ማለት ይቻላል ከወረደ ቡድን የመጡ ተጫዋቾች ናቸው። ከዚህ ቀደም በተለያየ ምክንያት አምና ቡድን አውርዶ የነበረ ተጫዋች እዚህ ከፍተኛ ብር ተከፍሎት ይጫወታል። ከወረደ ቡድን የሚመጡ ተጨዋቾች አያስፈልጉም ለማለት አይደለም። ከወረደ ቡድን መጥተውም በጣም ጥሩ የሆኑ ተጨዋቾች አሉ። ነገር ግን እንደ አጠቃላይ ስታየው በተደጋጋሚ ቡድን አውርዶ የመጣ እና ነፃ ሆኖ የሚመጣ ተጨዋች በአዕምሮ እኩል አይሆኑም። የማውረድ ልምዱ ካለህ ምንም አይመስልህም። ስለዚህ እነዚህ ነገሮች በግልፅ የሚቀመጡ የወልድያ ችግሮች ናቸው። ክለቡ እንደምታየው ዘመናዊ ሆቴል ነው የሚጠቀመው። ተጨዋቾች ቁርስ ፣ ምሳ እና እራት ደረጃውን በጠበቀ ሁኔታ ይመገባሉ። እኔ ከመጣው የዘገየ ደሞዝ አላየሁም። ይህ ማለት ከክለቡ ምንም የቀረ ነገር የለም ማለት ነው። 

እነዚህ ሁሉ ችግሮች ባሉበት ሁኔታ ክለቡን ስረከብ መጀመርያ የሰራሁት የነበረውን ከፍተኛ የዲሲፕሊን እርምጃ ላይ ነበር። ይሄም ተሳክቷል ማለት ይቻላል። ሌላው ከአርባምንጭ ጨዋታ በፊት ተሰብስበን ተነጋግረን የነበረ ቢሆንም ከአርባምንጭ ሽንፈት ማግስት ውጤቱ ሊስተካከል ባለመቻሉ በግሌ ከዚህ ቀደም ተሞክሮ ስለነበረኝ ለቡድኑ ተጨዋቾች በሙሉ ስማቸውን ሳይፅፉ በቡድኑ ዙርያ ያላቸውን ሀሳብ እንዲገልፁ ለውጪ ተጨዋቾችም በእንግሊዘኛ ሳይቀር በመጠይቅ በተንኩኝ። ሁሉም ማለት በሚያስችል መልኩ 100% የሚያስማማ ሁለት ነገር ፃፉ። አንደኛ ለቡድኑ ውጤት ማጣት እና ውድቀት ቀዳሚ ተጠያቂ እኛ ነን የሚል ነው። ይህ ማለት ህብረት ፣ ፍቅር እና አንድነት የለንም ፣ ግሩፕ አለ ፣ ራሳችንን ለክለቡ ሰጥተን ያለመጫወት ድክመት አለ የሚሉትን ያካትታል። ይህን ያለው አንድ ተጨዋች አይደለም ሁሉም ናቸው ማለት ይቻላል።  ሁለተኛ ‘ወልድያ አይወርድም በእርግጠኝነት እናተርፈዋለን’ የሚል ነበር። 

ከዚህ በኋላ ከወልዋሎ በነበረው ጨዋታ ጎል የማስቆጠር ችግር ቢኖርም ጥሩ መንቀሳቀስ ችለው ነበር። ከጊዮርጊስ ጋርም ተመሳሳይ ነበር። ከጅማ አባጅፋር ጋር ያደረግነው ጨዋታ ሲታይ ግን ፈፅሞ ቡድኑ የተዝረከረከ ሆኖ ነበር። ማንም እንዳየው የመጫወት ፍላጎትም አልነበራቸውም። በእርግጥ አንዳንዴ ተስፋ መቁረጥ ሲመጣ እንደዚህ አይነት ነገር ሊፈጠር ይችላል። ነገር ግን በሌላው አለምም ሆነ እኛም ሀገር የወረዱ ቡድኖች ወጥረው ሲጫወቱ አይተናል። እኛ ጋር ሲመጣ ግን ሌላ ነገር በሚመስል መልኩ ፍፁም በሚባል ሁኔታ ሜዳ ላይ አልነበርንም። አንዳንዴ ለመለያ መጫወት እና ክብር መስጠት ያስፈልጋል። ሰው ያይሀል ፣ ሚዲያውም ይመለከተሀል ተጋጣሚ ቡድን እንኳ ቢያሸንፍህም ይታዘብሀል ።   

በዚህ ሁሉ ሂደት ውስጥ እኔም ብቻ ሳልሆን ሌሎች የክለብ ባለሙያዎች ልንማረው የሚገባ ነገር አለ። እሱም በስም ተጨዋችን ማመን ማቆም አለብን። በወቅታዊ አቋም እና በአቅም ላይ ብቻ ተመስርተን ማመን ያስፈልገናል። ለምሳሌ ጅማ አባጅፋርን ተመልከት። የገብረመድህን ትልቅ አሰልጣኝነት እንዳለ ሆኖ አብዛኛዎቹ ተጨዋቾች ወጣቶች ናቸው። የመጫወት ፍላጎት ያላቸው እና ለመስዋዕትነት የተዘጋጁ ናቸው። በዚህም ነው እዚህ ደረጃ የደረሰው። ጊዮርጊስን ስንመለከት ክለቡ በራሱ የአሸናፊነት ባህል እና የሥነ ልቦናም የበላይነት እንዳለው የሚታወቅ ቢሆንም ልምዱን ተጠቅሞ እዚህ ደርሷል። ኢትዮዽያ ቡናን ስናይ በእኔ እይታ እንደ ዘንድሮ ወጣቶች ያሉበት ቡናን አላየሁም። ሮጠው ያልጠገቡ ናቸው። ከእኛ ጋር ሲጫወቱ በአናታችን ላይ እንዴት ሲሮጡ እንደነበረ አይተናል። ልጆች በመሆናቸው ከፍተኛ የሆነ የመጫወት ፍላጎት አላቸው። መቐለ ከተማም እንደዚሁ ነው ጥረት እና አልሸነፍ ባይነት አለው። ስለዚህ መሰረታዊው ነገር አቅም እና ፍላጎት ካለህ ማሸነፍ ትችላለህ። ባለሙያው እና ሌሎች ነገሮች ሁለተኛ ጉዳዮች ናቸው። ስለዚህ እኔ ከዚህ በኋላ በወጣቶች አቅም ላይ ነው የማምነው። ከዚህ በፊት ተሸውደናል ፤ ስህተት ሰርተናል። እኔም ሆንኩ ሌላው ከዚህ በኋላ በስም ማመን ትተን አቅም በሚለው ነገር ላይ ማተኮር አለብን።

ሌላው እንደሚታወቀው ሁለተኛው ዙር ይከብዳል። ዳኞች ይያዛሉ ፣ ተጨዋቾች ይያዛሉ ይባላል። ብዙ ነገር እንደሚደረግ ይሰማል ፤ ማንም እንደሚሰማው ማስረጃ ማቅረብ ባይቻልም። እኔ የተማርኩበትን ነው የምናገረው። በተለይ ሁለተኛው ዙር ስትጫወት ላለመውረድ በሚኖረው ትንቅንቅ የውጪ ተጨዋቾች እና ግብ ጠባቂዎች ጋር ተማምኖ የመስራቱ ነገር አደገኛ ነው። ምን ያህል ለመለያ ክብር ሰጥተው ይጫወታሉ ? የሚለው ጥያቄ ከባድ ነው። ይህንን ሁኔታ ዜጋውም ብቻ ሳይሆን ኢትዮጵያዊው ተጨዋች ጋር ጭምር እያየን ስለሆነ ነው ። 

“ከመምጣቴ አስቀድሞ እነዚህ ሁሉ ችግሮች እንዳሉ ባውቅ ኖሮ አልመጣም ነበር”

በወልድያ መውረድ ተጠያቂ አይደለሁም አልልም። ነገር ግን በአብዛኛው በጣም ዝርክርክ ያሉ ነገሮች ነበሩ። እነዚህን ነገሮችን ለማስተካከል ጥረት አድርጌ ለፍቼ ከተሳካልኝ ክለቡን ለማትረፍ ነበር የመጣሁት። ከመጣሁም በኋላ ከሌሎች የቡድኑ አባላት ጋር በመሆን ሰርተናል። ነገር ግን ክለቡ ተለውጦ አላየንም። ቅድም በጠቀስናቸው ችግሮች ምክንያት የተፈለገውን ያህል ቢሰራም ተአምር አይመጣም። የአሰልጣኝ ለውጥ የተደረገበት ጊዜ በራሱ የዘገየ ነው። ስለዚህ እኔ ላይ ለመፍረድ ይከብዳል። ምክንያቱም ችግሮቹ ብዙ ናቸው። እኔ ከመምጣቴ አስቀድሞ እነዚህ ሁሉ ችግሮች እንዳሉ ባውቅ ኖሮ አልመጣም ነበር። ለመምጣት አስቤ በቡድኑ ውስጥ ማን አለ ስል። እነ እከሌ አሉ ሲባል እነሱ ካሉ ተባብረን ከሰራን ለውጥ እናመጣለን ብዬ ነው የመጣሁት። ሆኖም ስመጣ መሰረት የሌለው የተወላገደ ነገር ነው ያለው። የተጠያቂነት ጉዳይ አሰልጣኝ ሆኜ እስከተቀመጥኩ ድረስ በተወሰነ ደረጃ ልጠየቅ እችላለሁ። ግን ያልሰራሁት ስራ እና ለህሊና የሚቆጨኝ ነገር የለም። ይሄን ባደርግ ኖሮ ብዬ የምፀፀትበትም ነገር የለም። ብዙ ነገር  ለማስተካከል ከተጨዋቾች ፣ ከቡድን አባላቶቼ ፣ ከክቡር ከንቲባው ጋር በመሆን ሞክርያለሁ። ግን አልተሳካም። ይህ ማለት እኔ የምጠይቅበት ነገር አይኖርም ማለት ነው። 

በቀጣይ…

አሁን ቡድኑ ወርዷል ተብሎ መተው የለበትም። ለምን ወረደ ? ምክንያቱ ምንድነው ? ለሚሉት ጥያቄዎች አሳማኝ መልስ ለህዝቡ መስጠት ያስፈልጋል። ከመጀመርያው ጀምሮ የተጨዋቾች አመላመል ፣ ሁለተኛው ዙር ላይ ለማስተካከል የተደረገው ጥረት ፣ የዲሲፕሊን ችግሮች ፣ የተመልካቹ የድጋፍ መንገድ ፣ የረበሻ መነሻዎች እና የተጨዋቾች ቅጣት ምክንያቶች ዙሪያ ያሉ ጥያቄዎችን መመለስ ያስፈልጋል። ዝም ብሎ ወረደ ተብሎ መዘጋት የለበትም። መጠየቅ እና መመለስ አለበት ፤ የተጠና ነገር መኖር አለበት። 

በመጨረሻም ከክቡር ከንቲባው ጀምሮ እስከ ደጋፊ ማህበሩ ቡድኑን ለማትረፍ በጣም ይጥሩ እና ይለፉ ለነበሩ እንዲሁም መተባበሮችን ላሳዩ ምስጋና ማቅረብ ያስፈልጋል ። በተጨዋቾቹም በኩል ቅድም ያልኩት ችግር ቢኖሩም ክለቡን ለማትረፍ መስዋዕትነት የከፈሉ ተጨዋቾች ነበሩ። የነገ እንጀራቸውም ያማረ ይሆናል። እነርሱንም ማመስገን እፈልጋለው።