ውድድር የመመራት አቅሙ ላይ ሁሌም ጥያቄ የሚነሳበት የኢትዮዽያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ላይ በዚህ ሁለት ቀናት ውስጥ ብቻ የፕሪምየር ሊግ ክለቦች በውድድር መርሀግብር እና መሰል ጉዳዮች ዙርያ ያላቸውን ቅሬታ በደብዳቤ ሲገልፁ ውለዋል።
ኢትዮ ኤሌትሪክ ፣ ቅዱስ ጊዮርጊስ እና ድሬዳዋ ከተማ ቀሪ ተስተካካይ ጨዋታዎች ካልተደረጉ 28ኛ ሳምንት ጨዋታዎችን አናደርግም ሲሉ ፣ ኢትዮዽያ ቡና ከአርባምንጭ የጥሎማለፍ ጨዋታ መልስ በአጭር ቀናት ውስጥ ወደ ሀዋሳ ሄጄ እንድጫወት መደረጉ ተገቢ አይደለም ፣ ሀዋሳ ከተማ ቡድኔ ልምምድ ማቋረጡ እየታወቀ ከኢትዮዽያ ቡና ጋር እንድጫወት የወጣው መርሀግብር ተገቢ አይደለም ፣ ወልዋሎ ወደ ሰባት ነጥብ የያዘ ቅሬታ በተደጋጋሚ በሚዘበራረቀው የፕሮግራም አወጣጥ ምክንያት በክለቤ ላይ ከፍተኛ እንግልት እየፈጠረ ነው ፣ ደደቢት ደግሞ በፌዴሬሽኑ የተዘበራረቀ የመርሀ ግብር አወጣጥ የተነሳ ራሴን ከኢትዮዽያ ዋንጫ አግልያለሁ ሲል የተሰማው ዛሬ ነበር። እነዚህ ሁሉ የቅሬታ አቤቱታዎች እያስተናገደ የሚገኘው ፌዴሬሽኑ በሚቀርቡት የቅሬታ ደብዳቤዎች ዙርያ ምን ምላሽ አለው በማለት የፌዴሬሽኑን ዋና ፀሀፊ የሆኑት አቶ ሰለሞን ገ/ስላሴን አናግረን የሰጡንን ምላሽ እንዲህ አቅርበነዋል ።
” እየቀረቡ ያሉ ቅሬታዎች በሙሉ ተገቢነት ያላቸው ቢሆንም አንዳንዶቹ ደግሞ ተገቢነት የሌላቸው ናቸው ። የሦስቱ ክለቦች የቅዱስ ጊዮርጊስ ፣ የድሬደዋ ከነማ እና የኢትዮ ኤሌክትሪክ ጥያቄ ምላሽ አያስፈልገውም። አስቀድሞ ደብዳቤ ከማስገባታቸው በፊት የሊግ ኮሚቴው ሰርቶ ተስተካካዮቹ ጨዋታዎች ሳይደረጉ 28ኛው ሳምንት እንደማይጀምር ወስኖ አሳውቋል። ስለዚህ የእነዚህ ክለቦች ጥያቄ የተመለሰ ሲሆን የተቀረውን የክለቦች ጥያቄም ዛሬ ፌዴሬሽኑ በሰጠው መመርያ መሰረት የሊግ ኮሚቴ አባላት አስቸኳይ ስብሰባ በማድረግ ለቀረቡት ጥያቄዎች በሙሉ ማጣራት በማድረግ ተገቢውን ምላሽ ሰጥቷል። ነገ በፅህፈት ቤቱ በኩል ለጥያቄያቸው ምላሽ ደብዳቤ በዝርዝር ለክለቦቹ የሚደርስ ይሆናል። ለሚዲያም ይፋ ይደረጋል። አንዳንዴም ክለቦችም በማይመች ሁኔታ ሲያጋጥም ፌዴሬሽኑን ሊያግዙ እና ችግሮችንም ሊካፈሉ፣ ሊጋሩ ይገባል።”