የአሰልጣኞቻችን የእግርኳስ አስተሳሰብ ፣ የስልጠና ሀሳብ ፣ የስራ ህይወት እና የውጤታማነት መንገድ ዙርያ ትኩረት በሚያደርገው ” የአሰልጣኞች ገጽ ” አምዳችን የዛሬ ተረኛ አሰልጣኝ ጉልላት ፍርዴ ናቸው።
ጉልላት ፍርዴ በተጫዋችነት ዘመናቸው ፔፕሲን ለቀው በ1980 ወደ ኤሌክትሪክ ካመሩ በኋላ ለሁለት አስርት ዓመታት በለክቡ ተጫዋችነት እና አሰልጣኝነት ቆይተዋል። በብዙዎች የሚታወሰው የ1993ቱ የሊግ እና ጥሎማለፍ አሸናፊ ኤሌክትሪክ አሰልጣኝ የነበሩ ሲሆን በቀጣይ ዓመታትም ተፎካካሪ አድርገውት ቆይተዋል።
በዛሬው የመጀመርያ ክፍል መሰናዷችን ስለ ኤሌክትሪክ ስኬታማ ዘመናት አውግተናል። ለቃለ ምልልሱ እንዲያመችም ከ”አንቱ” ይልቅ “አንተ” በሚለው ተጠቅመናል። ከኤሌክትሪክ ይልቅም በአሰልጣኙ የስራ ዘመን የነበረው ስያሜ ” መብራት ኃይል” ተጠቅመናል።
በሚልኪያስ አበራ እና አብርሀም ገብረማርያም
በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ያለፉት ሃያ አመታት ከታዩ ክለቦች እጅግ በጣም ምርጡና ስኬታማው የ1993ቱ የመብራት ኃይል ቡድን ዋነኛ ጥንካሬው ምንድን ነበር? በብዙ የእግርኳስ ባለሙያዎች ከተሰጡ ምላሾች በተለየ አንተ የዚያ ቡድን ዋና አሰልጣኝ ስለነበርክ ተለይቶ የሚጠቀስ ጎን ከነበረው ዘርዘር አድርገህ ብትገልጽልን…
★ በአንድ ክለብ ውስጥ ቡድን ሲገነባ “በስብስቡ የሚገኙ ተጫዋቾች በምን አይነት የብቃት ደረጃ ላይ የደረሱ ናቸው?” የሚለው ጥያቄ መሰረታዊ ይመስለኛል፡፡ ሊሰመርበት የሚገባው ጉዳይም አሰልጣኙ የሚመርጣቸው ተጫዋቾች የአጨዋወት ባህሪና ችሎታ ነው፡፡ የጊዜው የቡድኑ ተጫዋቾች የብቃት ደረጃ በጣም የሚገርም ነበር፡፡ሁለቱም የጊዜው የመብራት ኃይል በረኞች ጸጋዘአብ አስገዶምና ደያስ አዱኛ የብሄራዊ ቡድኑን ግብ ይጠብቃሉ፡፡ በተከላካይ ክፍሉ ደግሞ በቋሚነት የሚጫወቱት ሶስቱ የመሀል ተከላካዮች አንዋር ሲራጅ፣ ዳንኤል ሀብታሙና ዮናስ ገ/ሚካኤል በጉልበት፣ ቴክኒክና የኳስ ችሎታ ምንም እንከን የማታወጣላቸው የወቅቱ ምርጦች ነበሩ ፡፡ በ ሚናም መስፍን ደምሴ በግራ መስመር ከሳጥን-ሳጥን ያለድካም እየተመላለሰ የሚጫወትና <ኳስ የሚችል> ተጫዋች ነው፡፡ በቀኝ መስመር ደግሞ የተለያዩ ተጫዋቾችን ተጠቅመናል፡፡ ሙሴ ንፍታሌም፣ (ቻይና)፣ ፋንታሁንን እና ሌሎች ብዙ ልጆችን እየቀያየርን አሰልፈናል፡፡ በተለይ መሀል ላይ የነበሩት ተጫዋቾች እንቅስቃሴና ወቅታዊ ብቃት ጥሩ ከሆነ ሙሉ ቡድኑ ጥሩ ይሆን ነበር፡፡ በመሀለኛው የሜዳ ክፍል ጎበዙ ኳስ ነጣቂ ተጫዋች ያሬድ፣ ከፊቱ የሚሰለፉት ተክሌ ብርሐኔና አለማየሁ ዲሳሳ ደግሞ ኳስን እንደፈለጉ እየተቆጣጠሩና ጊዜውን የጠበቀ ፊንታ እየሰሩ የሚጫወቱ <አርቲስቶች> ነበሩ፡፡ አለማየሁ እኮ ሳይነጠቅ አስር ሰው አብዶ እየሰራ የሚያልፍ፣ ተክሌ ደግሞ የመሀል ክፍሉን እንደፈለገ ያሽከረክረዋል፡፡
የፊት መስመር ላይ የነበሩት ተጫዋቾች “አንተ አግባ፤ እሱ ያግባ፤ ዮርዳኖስ ያግባና ኮከብ ይሁን፤…” በማለት እየተገባበዙ ብዙ ግቦችን አስቆጥረዋል፡፡ ወደ ኋላ (Back Pass) ሁሉ እየተቀባበሉና ተዝናንተው እየተጫወቱ ዮርዳኖስን ይፈልጉ ነበር፡፡ስምዖንና ዮርዳኖስ በጥሩ ሁኔታ እየተናበቡ ረጅምና አጭር ቅብብሎችን በቀላሉ የሚቆጣጠሩ ሲሆኑ ዮርዳኖስ ደግሞ በግሉ የአየር ላይ ኳሶችን በመግጨት ጥሩ Header ከመሆኑም በላይ ሁሉን ያሟላ አጥቂ ነበር፡፡
ስምኦን ተከላካይ ሰንጣቂ ቅብብል በማድረግ ከአንድ አንድ እንድታገባ የሚያደርግ በመሆኑ የዮርዳኖስ ብዙዎቹ ጎሎች በስምኦን አማካኝነት የተገኙ ነበሩ፡፡ የቡድኑ አጠቃላይ የማጥቃት እንቅስቃሴ በፍጥነት የተጋጣሚ ጎል ክልል መድረስና የባላጋራን የተጠቀጠቀ የተከላካይ ክፍል ለማስከፈት በምክንያት ወደ ኋላ እየተሳበ በቀኝና በግራ መስመሮች ክፍተቶችን እንዲፈጥር የሚያደርግ እቅድን ያካትታል፡፡ በግርግር ጎሎች ሊገኙ የሚችሉት በአንድ አጋጣሚ እንጂ ሁሌም ሊሆን ስለማይችል በተጠና አቀራረብ የባላጋራን ተከላካይ እያስከፈትን በየጨዋታው አራትና አምስት ያላገባንበት ተጋጣሚ አልነበረም፡፡ የዚህ ስኬት ደግሞ ቡድኑ የሚጠቀምበት የታቀደበትና በአግባቡ የተሰራበት የአጨዋወት ስልት ነበር፡፡ በማጥቃት የጨዋታ ሒደት ተጫዋቾቻችን ብዙውን ጊዜ በቁጥር በዝተው ወደፊት ይሄዳሉ፤ ቢስቱ እንኳ እንደሚያገቡ እርግጠኞች ስለሆኑ ተደጋጋሚ ሙከራዎችን ያደርጋሉ፡፡ በቡድን እንቅስቃሴ ሳይሳካ ሲቀርም ተጫዋቾቹ ያላቸው ስነ ልቦናዊ ጥንካሬ ጫናዎችን እንዲቋቋሙ እያደረጋቸው ሻምፒዮን ሆነዋል፡፡ ስለዚህ ሁሉንም ክለቦች እያሳመነ በማሸነፍ ዋንጫ የወሰደው ያ ቡድን ከማንም የላቀ ችሎታ በታደሉት በጣም ምርጥ ምርጥ ተጫዋቾቹ ምክንያት ባለ ድል ሊሆን ችሏል፡፡ በተጨማሪም በተጫዋቾቹ መሀከል የነበረው አንድነት፣ፍቅርና ዲሲፕሊን የጠነከረ በመሆኑ ለመስራት አመቺ አካባቢን ፈጥሯል፡፡ አሁን እኮ ጥሩ ድሪብል የሚያደርግ ተጫዋች አላይም፤ ድሪብሊንግ ለምን እንደቀረም አላውቅም፡፡ ሰው እየቀነሱና በተጋጣሚ ላይ የቁጥር ብልጫ እየወሰዱ ወደ ጎል ክልል ለመግባት የሚደረግ እንቅስቃሴ የለም፡፡
ቡድኑ አመቱን ሙሉ ምርጥ አቋም ያሳይ ስለነበር ከተጫዋቾቹ ከፍ ያለ የብቃት ደረጃ በተጨማሪ የእናንተ አሰልጣኞቹ አስተዋጽኦስ ምን ያህል ነበር? በተለይ በዝግጅት ወቅት የተሰራው ስራ የፈጠረው ልዩነት ምንድን ነው?
★ በስልጠናው ስራ ትልቁ ኃላፊነት ያሉህን ተጫዋቾች ችሎታ በአግባቡ መገንዘብ ነው፡፡ በቡድንህ ውስጥ ባሉት ተጫዋቾች ምን አይነት አጨዋወት መከተል ትችላለህ? በየትኛው እንቅስቃሴ ምን አይነት ውጤት እንደምታመጣ ቀድመህ ማወቅ ይኖርብሀል፡፡ ስለዚህ ላሉህ ተጫዋቾች የሚሆነውን የጨዋታ ስልት መምረጥ ያስፈልጋል፡፡ ውጤት ያመጣነውም በዝግጅት ወቅት ልጆቹን በመረጥነው እንቅስቃሴ በማስራታችን ነው፡፡ ማንም ተጫዋች ዝም ብሎ ስለተሰበሰበ ብቻ ውጤት ሊያመጣ አይችልም፡፡ ዋናው በቡድኑ በተመረጠው የአጨዋወት ስልት እንዲገቡና እንዲዋሀዱ በማድረግ ነው፡፡ አጫጭር አንድ-ሁለት ቅብብሎች (Double Passes) በየትኛው የሜዳ ክፍሎች ላይ ማድረግ እንዳለባቸው ያውቃሉ፤ ክፍተቶችን እንዴት መሸፈን እንደሚገባቸውም ጠንቅቀው የተረዱ ናቸው፤ ተረዳድተው መጫወት ይችሉበታል፤ በዋናነት ደግሞ ሁሉም ተጫዋቾች ኳስን በትክክለኛ ቦታ መስጠት የተካኑ ነበሩ፤ ከሁሉም በላይ በጣም ሀይለኛ ኳስ አቀባዮች (የተሳካ ቅብብል አድራጊዎች) ነበሩ፡፡ አማካዮቹ ሁሌም ያለቀላቸውን ኳሶች ለፊት መስመር ተሰላፊዎች ያደርሳሉ፡፡ ዮርዳኖስ ደግሞ መሳት የሚባል ነገር የማያውቅና ከአንዱ እድል አንድ የሚያስቆጥር አጥቂ ነበር፡፡ ስለዚህ እንዲህ አይነት ውህደት ያለው እንቅስቃሴ በማድረግ ቡድኑ ውጤታማ ሆኗል፡፡
በ1990 ዓ.ም ባለድል የነበረ ቡድን መሆኑም ስነልቦናዊ ጥንካሬ ሰጥቶታል፡፡ የተነሳሽነት ችግር ያልነበረበትና ለሊግ አሸናፊነት አዲስ ያልሆነ ስብስብ መሆኑስ የሰጠው ጠቀሜታ ?
★ በነገራችን ላይ በ1990 መብራት ኃይል ሻምፒዮን ሲሆን ወሳኝ ሚና የተጫወቱት እነ በለጠ ወዳጆ ፣አንዋር ያሲን፣ አፈወርቅ ኪሮስ፣ኤልያስ ጁሐርና ሌሎችም ትልልቅ ተጫዋቾች ነበሩ፡፡ ሆኖም በ1991ክለቡ ወደ ሰባትና ስምንት የሚደርሱ አንጋፋ የሆኑ ተጫዋቾችን ቀንሶ ወጣቶቹን በማሳደግ እድል ሰጠ፡፡ “ሁለተኛ ዙር ላይ ክለቡ አይወርድም፤ ወደ ላይም አይወጣም፤ ስለዚህ እነዚህ ወጣቶች ፕሪምየር ሊጉን ይልመዱትና ልጆቹ ወደፊት ከተሰራባቸው ውጤት ሊገኝባቸው ይችላል፡፡” የሚል እምነትና ግምት ስለነበር አንዋርና አፈወርቅ ቀርተው ሌሎቹ ለቀው ነበር፡፡ በተተኪነት በተያዙት ወጣቶችም ጥሩ ስራ ተሰራ፡፡
በወቅቱ የመብራት ኃይል ዋና አሰልጣኝ አንተ ሆነህ ሳለህ “ቡድኑ ቀደም ብሎ በማስተር ቴክኒሻን ሐጎስ ደስታ የተሰራና በዋነኝነት የሳቸው ተጽዕኖ ያረፈበት ስለሆነ <የሐጎስ ቡድን ነው> ነው፡፡” እየተባለ በብዙዎች የሚሰጥ አስተያየት አለ፡፡ ይህ ጉዳይ በተደጋጋሚ ሲነሳና ስለጥረትህ ዋጋ ስታጣ ምን ይሰማሀል? ወይስ በሀሳቡ ሙሉ በሙሉ ተስማሚ ነህ?
★ አቶ ሐጎስ ይሰራ የነበረው ለመብራት ሐይል ነው፤ እኔም እንደዚያው፡፡ የሐጎስ ልጅ-የጉልላት ልጅ የሚባል ነገር አልነበረም፡፡ ሁለታችንም የምናሰለጥነው በክለቡ ሊኖሩ የሚችሉ ተጫዋቾችን ነው፡፡ የሚለየው ጉዳይ በቡድኑ ያገኘሀቸውን ተጫዋቾች ” እንዴት አድርጌ እጠቀምባቸዋለሁ?” የሚለው ይመስለኛል፡፡ የትኛውም አሰልጣኝ ይህን በጥልቀት አስቦበት በመስራት ውጤት ማምጣት ይኖርበታል፡፡ የመብራት ኃይል ቡድን በ1990 ዓ.ም ዋንጫውን ሲወስድ በውድድሩ የመጨረሻ ቀን ነበር ሻምፒዮንነቱን ያረጋገጠው፡፡ እኔ የመራሁት የ1993ቱ ቡድን ደግሞ ከተከታዩ በብዙ የነጥብ ርቀት ቀድሞ አምስት ጨዋታ እየቀረው ባለድል መሆኑን አረጋግጦ ነበር፡፡ ይህ ልዩነት የስራውን እንቅስቃሴያዊ ሁኔታ ሙሉ በሙሉ የሚገልጸው ይመስለኛል፡፡ ስለዚህ ሁለታችንም ስንሰራ የነበረው ለክለቡ እንጂ ለየግል ለምናመጣው ውጤት አልነበረም፡፡ በእርግጥ ጋሽ ሐጎስ የራሱ የሆነ አጨዋወት፣ አካሄድና ፍልስፍና ሊኖረው ይችላል፡፡ እኔም በተመሳሳይ በተለይ ከእርሱና ከሌሎች በወሰድኳቸውና የራሴ በሆኑት መንገዶች ሄጄ ተሳክቶልኛል፡፡ ‘ስራው የኔ ነው!’ ከማለት ውጪ ምንም ልል አልችልም፤ የሌላ የማንም አይደለም፡፡ በእርግጥ አቶ ሐጎስ መሰረቱን ዘርግቶ ሊሆን ይችላል፤ ሆኖም ግን መሰረቱን ይዤና የራሴን እምነት ቀላቅዬ ያንን ውጤታማነት ያስቀጠልኩት እኔ ነኝ፡፡እኔ እኮ መብራት ኃይልን የለቀኩት ” ለምን አራተኛ ደረጃን ያዝክ?” ተብዬ ነው፡፡ ከቡድኑ እስከተለየሁበት ጊዜ የዋንጫ ተፎካካሪ ሆኖ ሁለተኛና ሶስተኛ የሚወጣ ቡድን ነበር፡፡ ያ ቡድን በምን አይነት ጠንካራ መሰረት ላይ የተገነባ እንደነበር ይህ አስረጂ ሁኔታ መሆኑን መገንዘብ እንችላለን፡፡ በወቅቱ ከክለቡ ስሰናበት ጀማል ጣሰው፣ ፋሲል(በጣም ጎበዝና አሁን በአዲስ አበባ ከተማ የሚጫወት)፣ ወንድይፍራው ጌታሁን (“አይጠቅምም!” ተብሎም ነበር)፣ ሳላዲን ባርጌቾና ሌሎችም አሁን በብሔራዊ ቡድን ደረጃ የሚጫወቱ ልጆችን አዘጋጅቼ በእነርሱ የተሻለ ነገር መስራት በምችልበት ጊዜ ነው የተሰናበትኩት፡፡ እስካሁንም የሚያናድደኝና የሚያሳዝነኝ ተጫዋቾቹ ያላቸውን ነገር ሳያሳዩና ክለቡን ሳይጠቅሙ ወደ ሌላ ቦታ መሄዳቸው ነው፡፡ ሆኖም አሁንም ድረስ በተለያዩ ክለቦች የሚጫወቱና የራሳቸውን ብቃት አጎልብተው ትልቅ ቦታ ለመድረስ የሚጥሩ አሉ፡፡ መብራት ሃይል ቢሆኑ ኖሮ ደግሞ ከዚህም የበለጠ ጎልተው ይታዩ ነበር፡፡ እንግዲህ ሁኔታውን ምንም ልናደርግ አንችልም፡፡
በወቅቱ ወጣትና መብራት ኃይልን ለድርብ ድል ያበቃህ፣ በትልቅ ቡድን ውስጥ ደግሞ በፍጥነት ስኬትን ያገኘህ አሰልጣኝ ስለነበርክ በሌሎችም ክለቦች በዋና አሰልጣኝነት የመስራትና ራስህን የማሳየት እድሉ ይኖርሀል ተብሎ ይታሰባል፡፡ቀጥለው ለሚመጡት የውጭ ዜጋ አሰልጣኞች ረዳት የመሆን ፍቃደኝነትን እንዴት ልታሳይ ቻልክ?
★ የዚያን ጊዜ የክለብ አሰልጣኞች ከፍተኛው ወርሀዊ ደመወዝ 5,000 ብር ገደማ ይደርሳል፡፡ እኔ ደግሞ በድርጅቱ ስራዬ የማገኘውና የተወሰነ ከክለቡ የምቀበለው ደመወዝ ተደማምሮ ለዚህ የገንዘብ መጠን የተጠጋ ይሆናል፡፡ ስለዚህ ‘ተመሳሳይ ክፍያ (5,000 ብር) ለማግኘት ስራ መልቀቅ አስፈላጊ ነው ብዬ አላምንም!’ ነበር፡፡ ስራውንና ያለህበትን ቦታ ወደህ ካልሰራህ በስተቀር ምንም የምትጠቀመው ነገር አይኖርም፡፡ አሁን ላይ ሆኜ ሳስበውም እዚያው በመቆየቴ ብዙ ትምህርት እንዳገኘሁ ይሰማኛል፡፡ ቀደም ብዬ እንደገለጽኩት በታክቲክ ረገድ ብዙ ትምህርት የወሰድኩት ከፔትሬሊ ነው፡፡ ከኬን ሞርተንም እንዲሁ የተለያዩ እውቀቶችን ቀስሜያለሁ፡፡ እነዚህ ጎበዝ የሆኑ አሰልጣኞች ወደ ክለቡ ሲመጡ መብራት ኃይል በእነርሱ የተሻለ ደረጃ ላይ ለመገኘት ፍላጎት ነበረው፡፡ በነበረው ሁኔታ እኔም አብሬ የእድገቱ አካል የመሆን ተሳትፎ እንዲኖረኝ እፈልግ ነበር፡፡ በዚያው መጠን የማይሆን ነገር ሲመጣም ያልተስማማሁባቸውና ለቅቄ የወጣሁባቸው ጊዜያት ነበሩ፡፡ ለምሳሌ ያህልም ፔትሬሊ በመብራት ኃይል የቆየው ለሁለት አመታት ነው፡፡በመጀመሪያው አመት አብረን ሰራንና ውድድሩ ሲያልቅ እርሱ ወደ አገሩ ሄደ፡፡ በክረምቱ እኔ የቅድመ ውድድር ዘመን ዝግጅት አሰርቼ ከጨረስኩ በኋላ እርሱ ተመልሶ መጣና ” እኔ በድጋሚ የዝግጅት ልምምድ አሰራለሁ፡፡” ሲል በሀሳቡ ስላልተስማማሁ ተጋጨን፡፡ እንዳለውም የዝግጅት ስልጠና ሲያሰራቸውም ‘ለምንድነው በድጋሚ የምታሰራቸው? ፈትነሃቸው ስታበቃ “የሚገኙበት ደረጃ ከአውሮፓውያኑ ጋር የሚወዳደር ነው!” በማለት ተጫዋቾቹን አመስግነህ እኔንም አበረታተኸኛል፡፡ እንደገና ወደ ሩጫ ልምምድ የምታስኬዳቸው ለምንድን ነው? ይሄ ቡድን እኮ ወደ ውድድር ሲገባ በመዳከሙ ምክንያት ውጤት ለማምጣት ይቸገራል፡፡ ስለዚህ ይህን የድጋሚ ስልጠና መስጠት የለብህም፡፡’ በማለቴ አለመስማማት ላይ ደረስንና ተጣላን፡፡ የማይሆን ነገር እየተደረገ ስመለከት ዝም ማለት አልችልም፡፡ ” እንዴት እኔን እንዲህ ይለኛል?” በማለት ለአቶ ምህረት ይነግርና የ”B” ቡድን እንዳሰለጥን ይደረጋል፡፡ ሆኖም ግን በዚያው አመት ቡድኑ ላይ እኔ ያልኩት ነገር ደረሰበትና 14ኛ ወጥቶ ለጥቂት ከመውረድ ተረፈ፡፡ ከዚያም እርሱ ማሰራት ሲያቆም እኔ ተመልሼ መስራት ቀጠልኩ፡፡ ሁሌም ቢሆን የማላምንበት ሁኔታ ሲገጥመኝ ከሰዎች ጋር የሚያጋጨኝ እንኳ ቢሆን አልቀበልም፡፡ የማምንበት ደግሞ ሲሆን ጥሩ በመሆኑ ለራሴ ትምህርት እንዲሆነኝ እያደረግሁ እለወጥበታለሁ፡፡
በአንድ ክለብ (መብራት ኃይል) በተጻራሪ ሁኔታ የሚገኙ ሁለት ሐላፊነቶችን እንድትወጣ የተደረግክ እና የሚጠበቅብህንም በአግባቡ ያበረከትክ አሰልጣኝ ነህ፡፡ በ1993 ዓ.ም ክለቡን ለሊግና ጥሎ ማለፍ ድሎች ለማብቃት ጥረህ አሸናፊ ሆነሀል፡፡ ከዘጠኝ አመታት በኋላ ደግሞ ይህንኑ ክለብ ወደ ታችኛው የሊግ እርከን እንዳይወርድ ታግለህ በመጨረሻው ጨዋታ ተሳክቶልሀል፡፡ ከሁለቱ ጫናዎች የትኛው የበለጠ ከበድ ይላል?
★ ቻምፒዮንነት በአንድ ጊዜ የምታሳካው ሳይሆን በረጅም ጉዞ እንዲሁም በእያንዳንዱ ጨዋታ በተጠራቀመ ነጥብና በሒደት የምታመጣው ውጤት ነው፡፡ በ2002 ዓ.ም የመውረድ ስጋት ላይ የነበረውን ቡድን የተረከብኩት በሁለተኛው የውድድር ዘመን ነበር፡፡ የወቅቱ ተጫዋቾችም እርስበርስ የማይስማሙና ሜዳ ላይ ሁሉ ረብሻ የሚፈጥሩ ስለነበሩ እነርሱን የማስታረቅና በተገቢ መንገድ እንዲቀራረቡ ለማድረግ የገጠመን ስራ በጣም ከባድ ነበር፡፡ ቡድኑ ለሁለት ተከፋፍሎና እኔ መብራት ኃይልን ካወኩበት ጊዜ ጀምሮ የማላውቀው አይነት ከባቢ ተፈጥሮ የሚታየው ሁኔታ ሁሉ ደስ የማይልና የሚያስፈራ ገጽታ ነበረው፡፡ በጣም የምወደው ክለብ ከመሆኑም በላይ አንዴ ራሴን ሐላፊነቱ ውስጥ ስላስገባሁ ወደ ታች እንዳይወርድ በጣም እጥር ነበር፡፡ በእነዚህ ሁኔታዎች ውስጥ መስራት በጣም ከባድ ቢሆንም በውድድሩ መገባደጃ ጊዜ ከመድን ጋር በነጥብና በጎል ክፍያ እኩል ሆነን “ብዙ ያገባ” በሚለው እኛ ከመውረድ ተረፍን፡፡ ሻምፒዮን መሆን እኮ ከክረምት ጀምሮ በሰራኸው ስራ የሚመጣ ስለሚሆን ብዙ ጫና የለውም፤ ወደ ድል አድራጊነት ስትጠጋም የበለጠ እየተደሰትክ፣ ሰውነትህና አዕምሮህ እየተፍታታና ነጻ እየሆነ ትሄዳለህ፡፡ ላለመውረድ ስትጫወት ግን በእያንዳንዱ ጨዋታ ጭንቀት ይገጥምሀል፤ ተጫዋቾች የመጫወት ፍላጎታቸው ይቀንሳል፤ ይርበተበቱና የሚፈልጉትን ነገር መስራት ይከበዳቸዋል፡፡ ስለዚህ ባለመውረድ ትንቅንቅ ውስጥ የሚገጥመው ጫና በጣም ከባድ በመሆኑ የቻምፒዮንነት ጫናው ቀላል ያደርገዋል፡፡
መብራት ኃይል ከሚሌንየሙ በፊት በነበሩት አመታት <ለዋንጫና ለደረጃ የሚፋለም> ስኬታማ ቡድን ነበረ፡፡ ከሚሊኒየሙ ወዲህ ባሉት አመዛኝ የውድድር ዘመናት ደግሞ <ላለመውረድ የሚታገል ቡድን> ሆኗል፡፡ የቡድኑ የቅርብ ሰውና የድርጅቱ ሰራተኛ ስለሆንክ ውስጠ-ምሰጢሩን ታውቀው ይሆናል፡፡ በሁለት አስርት አመታት ውስጥ እንዲህ ለውጤት መፋለሶች የተዳረገበትን ልዩነት የፈጠረው ዋነኛ ምክንያት ምንድን ይመስልሀል?
★ ዋነኛው ችግር የአስተዳደር ነው፡፡ በድርጅቱ የቦርድ መሪ ተብለህ በሰው ኃይል አመራርነት ስትቀመጥ ክለቡ በአንተ ስር እንዲተዳደር ይደረጋል፡፡ በዚህ የሐላፊነት ቦታ ላይ ሁለት አመት ብቻ ትሰራና ትለቃለህ፡፡ ከዚያ ደግሞ ሌላ የቦርድ ሃላፊ ይመጣና ይተካል፡፡ በእግር ኳሱ ዘርፍ ያለውን አሰራር ሊያውቅ በሚሞክርበት ጊዜ ጊዜው ያልቅና ድጋሚ በሌላ አመራር ይተካል፡፡ ከዚያ ደግሞ “ስለ እግር ኳስ ምንም አላውቅም!” የሚል አስተዳደር ይመጣል፡፡ እንዳጋጣሚ ሆኖ ደህና እግርኳሳዊ አረዳድ ያላቸው ሰዎች መጥተው እግርኳሱን የሚመሩበት ሁኔታ ሊላመዱት ሲሉ ጊዜያቸው ያበቃና ይለቃሉ፡፡ መብራት ኃይል በእንደዚህ አይነት የማያቋርጥ የአስተዳደር ለውጥ ሒደት ውስጥ ነው እያለፈ የሚገኘው፡፡ አሁንም ከዚህኛው አሰራርና አካሄድ መላቀቅ አለበት፡፡ እግር ኳስን በደንብ የሚረዳና ስራውን የሚያውቅ ሰው ቢኖር መሰራት ስለሚገባቸው ስራዎች ግንዛቤ ስለሚኖረው የተሻለ እድገት እንዲመጣ ያደርጋል፡፡ እስቲ ለምሳሌ የሌሎችን ትልልቅ ክለቦች አመራሮች እንመልከት፡፡ በቅዱስ ጊዮርጊስ አቶ አብነት ገ/መስቀልና በኢትዮጵያ ቡና መቶ አለቃ ፈቃደ ማሞ ክለቦቻቸውን ለረጅም ጊዜያት መርተዋል፡፡ በኤሌክትሪክ ግን የክለቡ መሪዎች በየአመቱና ሁለት አመት ጊዜ ውስጥ ነው የሚገለባበጡት፡፡ እንግዲህ እኔ የክለቡ አንኳር ችግር የሚመስለኝ ይህ ነው፡፡
በመብራት ኃይል ቡድን ውስጥ የብቃት ደረጃቸው የላቁና ትልልቅ ስብዕናን የተላበሱ ተጫዋቾች ነበሩ፡፡ አንተም ወጣትና ከምክትልነት ወደ ዋናነት እንደመጣህ ያሳዩት ጥሩ አቀባበል ላንተ የነበራቸውን ክብር አመላካች ነው፡፡ የተረጋጋ ባህሪን ይዘህ እነዚህን ተጫዋቾች ለአንድ አላማ ለማነሳሳትና ጠንካራ ህብረትን ለመፍጠር የቻልከው እንዴት ባለ ሰው የማስተዳደር ዘዴ ነበር?
★ ማንም ሰው መስራት የማይችለውን ስራ አንተ ተቆጪ ባህሪ ስላለህና ስለተቆጣኸው ሊሰራው አይችልም፡፡ መብራት ኃይል ምን አይነት ቡድን እንደነበረ ይታወቃል፡፡ ሁሉም ተጨዋቾች ምን መስራት እንዳለባቸው ግንዛቤው ነበራቸው፡፡ ‘ቀደም ብሎ በነበሩት አመታት ክፍተቶቻችን ምንድን ነበሩ? ጠንካራ ጎኖቻችንስ? እነዚህ ላይ ልንወያይና ሀሳብ ልንለዋወጥባቸው ይገባል፡፡’ የሚል ሐሳብ አቅርበን በዚያ መንገድ እንጓዝ ነበር፡፡
መብራት ኃይል ከሌሎች ክለቦች በተሻለ ለወጣት ተጫዋቾች እድል በመስጠትና ተተኪዎችን በማፍራት ረገድ ጥሩ ይሰራ ነበር፡፡ ሀይህ የሆነበት የተለየ ስርዓት ነበረው ማለት ነው?
★ ቡድኑ በልዩነት የሚጠቀስ ሲስተም ኖሮት አይመስለኝም፡፡ ለምሳሌ፦ እኛ የተጫዋችነት ዘመናችን እያበቃ ሲመጣ የተተካነው በነ አፈወርቅ ኪሮስና ጌታቸው ካሳ (ቡቡ) አይነቶቹ ተጫዋቾች ነበር፡፡ ድሮውንም ” ኤልፓ ተጫዋች ያሳድጋል!” ስለሚባል በትንሹ ” እኔ ኳስ እችላለሁ፡፡” የሚል ልጅ ወደ ቡድኑ ይመጣና ታይቶ ይመረጣል፡፡ መጠነኛ ችሎታ ስታሳይ ደግሞ አሰልጣኞች ሁሉ ፍላጎት ያሳድሩብህና በቶሎ ወደ ላይ ታድጋለህ፤ የመጫወት እድልህም ይሰፋል፡፡ እንግዲህ የነበረው ሒደት ይህ ነው፡፡ በአንድ ወቅት የማስታውሰው ወደ 1,000 ተፈታኝ መጥቶ ሜዳው ሁሉ በተጫዋቾች ተሞልቶ ነበር፡፡ አስቡት ከዚህ ሁሉ ሰው ውስጥ ጥቂቶችን ለመምረጥ ምንያህል አስቸጋሪ እንደሚሆን፡፡ በብዙ የማጣራት ድግግሞሽ ወደ 30 እስከሚደርሱ ይጠበቃል፡፡ የዋናው ቡድን አሰልጣኞች የሆነውም ከወጣት ቡድኖቹ ማለትም ከ” B” እና ከ”C” ተጫዋቾች ሲመረጡ ሄደን እናይ ነበር፡፡ በግምገማው ላይም እይታ ውስጥ የሚገቡትን ጠቁመን እንሄዳለን፤ በዚህ መንገድ የጠራ የአመላመል ስርዓትን እንከተል ነበር፡፡ በብዙ ፈተና የሚያልፉት ተጫዋቾች ደግሞ የዋናውን ቡድን አጨዋወትና እንቅስቃሴ እንዲላመዱ ይደረጋሉ፡፡ የዋናው ቡድን ልምምድ 4:00 ከመጀመሩ በፊት እኔ 3:00 አካባቢ ወደ ስልጠናው መስክ እደርስና ታዳጊዎቹ የሚሰሩትን አያለሁ፡፡ አልፎ አልፎም ትርፍ ሰዓት ሲኖረኝ ቁጭ ብዬ ጨዋታዎቻቸውን እየተመለከትኩ ጥሩ እንቅስቃሴ ስለሚያደርጉና የተሻለ ብቃት ስለሚያሳዩ ተጫዋቾች ጥያቄዎችን እያነሳሁ ከአሰልጣኞቻቸው መረጃዎችን እሰበስባለሁ፡፡ የተወሰኑትም እኛ ጋር መጥተው ከአንጋፎቹ ጋር ልምምድ እንዲሰሩ እናደርጋለን፡፡ “ጠንክሬ ሰርቼ ትልልቆቹ ተጫዋቾች የደረሱበት ደረጃ እደርሳለሁ!” የሚል ስሜት ይይዛቸውና ያላቸውን በሙሉ እያወጡ ለመጠቀም የልጆቹ ፍላጎት በአንድ ጊዜ ሲለወጥ እናያለን፡፡
በወጣቶች እድገት ሒደት የኤሌክትሪክ መንገድ የሚለየው አንጋፎቹ ተጫዋቾች ራሳቸው እዚያው ክለቡ ውስጥ አድገው ትልቅ ደረጃ የሚደርሱበት ሁኔታ መኖሩ ይመስለናል፡፡ ከተለያዩ ክለቦች ቡድኑን የሚቀላቀሉ ወጣቶች ቢኖሩም በሌሎቹ ውስጥ እንደሚታየው ቁጥር በርክቶ አናገኘውም፡፡ ስለዚህ በሁለቱም አቅጣጫ ያሉት ተጫዋቾች የመግባባት ውህደት የተሻለ ይሆናል፡፡ ከታች ያደጉት እድል እንደሚያገኙ እርግጠኛ ሆነው የሚጥሩበትና ላይ በትልቅ ደረጃ ያሉትም ታዳጊ ሆነው ያገኙትን እድል በማስመልከት ለአዳዲሶቹ ያላቸው ቅርበት የበለጠ ይጠነክራል፡፡
★ በጣም ትክክል!!! በሌሎች ክለቦች ወደ ዋናው ቡድን በሚያድጉት ልጆች ላይ በነባር ተጫዋቾች አማካኝነት የመመታትና ስነ ልቦናዊ ፍርሃት እንዲያድርባቸው የማድረግ ልማድ እንዳለ ይነገራል፡፡ በመብራት ኃይል ግን ይህ ፈጽሞ የለም፡፡ በልምምድ ወቅት ያልተገባ ጨዋታ መጫወት፣ መደባደብ፣ <አለፍከኝ> ብሎ መጥለፍና ሌሎች አሉታዊ ነገሮች ፈጽሞ የተከለከሉና እጅጉን የተወገዙ ድርጊቶች ናቸው፡፡ ይህ ከለላ ስላለም ትንንሾቹ ልጆች የሚፈልጉትን እንቅስቃሴ ደፍረው ያደርጋሉ፡፡ “እችላለሁ ለካ!” የሚል የመነሳሳት ስሜት ያድርባቸዋል፡፡ ወደ ሜዳ ሲገቡም ” ቡድናችን እንደሚያሸንፍ እናውቃለን፤ እናንተ ደግሞ በግል አንድ ጥሩ ነገር አሳይታችሁ ውጡ፡፡” እያልን በመንገር እናደፋፍራቸዋለን፡፡ ” የፈለገውን ያህል ይበላሽብህ፤ ሳትጨናነቅ እንደፈለግከው ተጫወት፤ አይዞህ! ዋናው የሚታይ ነገር እንዳለህ ማሳየቱ ነው፡፡” እንላቸዋለን፡፡ ትዝ ይለኛል- አለማየሁ ዲሳሳ (ዴልፒየሮ) ለመጀመሪያ ጊዜ በተሰለፈበት ጨዋታ ኳሱን ሳብ ሳብ አደረገና በተጋጣሚ ተጫዋች ሁለት እግሮች መሀል የማሾለክ ቴክኒካዊ ስልት በመጠቀም ሲያልፈው ተጫዋቾቹ ራሱ “እንዴት አይነት ደፋር ነው?” መባባል ጀመሩ፡፡ እሱ ምንም ስለማይመስለው ከዚያ በኋላም ያንን አብዶ ቀጠለበት፡፡ አሰልጣኞች ያለባቸውን ጫና ተቋቁመው በተለይ ለወጣቶች እድልን የመስጠት ድፍረት ካላሳዩና የአገሪቱን እግርኳስ ለማሳደግ ካልሞከሩ የወደፊቱ ሁኔታችን ዋጋ አይኖረውም፡፡