“የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ የማህበረሰብ ፕሮግራም ልምድ በኢትየጵያ ተግባራዊ ይሆናል” – ጁኔይዲ ባሻ


የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ እግር ኳስ ክለቦች ከውድድር በሻገር የሚያከናውኗቸውን ማህበረሰብ ተኮር ፕሮግራሞች በኢትዮጵያም ተግባራዊ ለማድረግ የሚያስችል ስምምነት ከትናንት በስቲያ ተፈረመ፡፡ ስምምነቱን የፈረሙት የኢትዮጵያ ኳስ እግር ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት አቶ ጁኔይዲ ባሻ እና የብሪቲሽ ካውንስል ተጠባባቂ ዳይሬክተር አቶ ነጻነት ደመወዝ ናቸው፡፡


በስምምነቱ መሰረት የማህበረሰብ ፕሮግራሞችን በሚቀጥሉት ሶስት ዓመታት ውስጥ በኢትዮጵያ ተግባራዊ ለማድረግ የሚያስችል የፕሮጀክት መነሻ ሃሳብ ይዘጋጃል፡፡በመነሻ ሃሳቡ ላይ ውይይት ተካሂዶ ስምምነት ላይ ከተደረሰ በሁዋላም በክልልና የከተማ አስተዳደሮች እግር ኳስ ፌዴሬሽኖችና በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ክለቦች እንዲሁም የኢትዮጵያ ኳስ እግር ፌዴሬሽን በሚያዘጋጁዋቸው ዝርዝር እቅዶች አማካኝነት የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ እግር ኳስ ክለቦች ማህበረሰባዊ ችግሮችን የሚፈቱባቸው ልምዶች በሁሉም ክልሎችና የከተማ አስተዳደሮች በሚቀጥሉት ሶስት ዓመታት እንደሚተገበሩ ለማወቅ ተችሏል፡፡የፕሮግራሙን ዓላማዎች ለማሳካት እንዲያግዝም ለሁሉም ክልሎችና የከተማ አስተዳደሮች እግር ኳስ ፌዴሬሽኖች ፕሬዚዳንቶች እንዲሁም ለኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ እግር ኳስ ክለቦች የበላይ ሃላፊዎች በብሪቲሽ ካውንስልና በኢትዮጵያ ኳስ እግር ፌዴሬሽን አዘጋጅነት የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና ተሰጥቷል፡፡


የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ የማህበረሰብ ፕሮግራም ለተለያዩ ችግሮች የተጋለጡ ታዳጊ ወጣቶችን፤ የተገለሉ የህብረተስብ ክፍሎችንና ሴቶችን በስራ ፈጠራ አማካኝነት ተጠቃሚ የሚያደርግ ከመሆኑም ባሻገር የእንግሊዝኛ ቋንቋ ክህሎትን ለማዳበር እንደሚያስችል ታምኖበታል፡፡እግር ኳስ የአለም ቋንቋ እየሆነ መምጣቱን መሰረት በማድረግ ኢትዮጵያን ጨምሮ በ25 አገሮች ተግባራዊ መሆን የጀመረውና ፕሪሚየም ስኪልስ የሚል መጠሪያ በተሰጠው በዚህ ማህበረሰብ አቀፍ ፕሮግራም አማካኝነት ባለፉት ሰባት ዓመታት 2300 የማህበረሰብ ዳኞችና አሰልጣኞች ደረጃውን የጠበቀ ሙያዊ ስልጠና በመውሰድ ከ500 ሺህ በላይ የሚሆኑ ታዳጊዎችን ተጠቃሚ ማድረግ ችለዋል፡፡

ምንጭ – አስፋው ስለሺ (ስፓይ ስፖርት)

ያጋሩ