ሩሲያ 2018 | ባምላክ ለሁለተኛ ጊዜ በአራተኛ ዳኝነት ተመድቧል

በሩሲያ አስተናጋጅነት እየተካሄደ በሚገኘው የፊፋ የዓለም ዋንጫ ዛሬ ከሰዓት የሚደረግ ጨዋታ ላይ ኢትዮጵያዊው አርቢትር ባምላክ ተሰማ በአራተኛ ዳኛነት ተመርጧል፡

በሳምንቱ መጨረሻ ሰርቢያ ኮስታ ሪካን 1-0 በረታችበትን የምድብ ጨዋታ በአራተኛ ዳኛነት ያገለገለው ባምላክ ዛሬ 9፡00 ሳማራ ከተማ በሚገኘው ሳማራ አሬና በሚደረገው የዴንማርክ እና አውስትራሊያ ጨዋታ ላይ አራተኛ ዳኛ ሆኖ በፊፋ ተሹሟል፡፡

በምድብ ሶስት የሚገኙት የሁለቱ ሃገራትን ጨዋታ ስፔናዊያኑ አንቶኒዮ ማቲዩ፣ ፓዉ ዴቪስ እና ሮቤርቶ ፔሬዝ የሚመሩት ሲሆን ኮስታ ሪካዊው ሁዋን ካርሎስ ሞራ ተጠባባቂ አርቢትር ናቸው፡፡


ባምላክ ሰርቢያ ከኮስታ ሪካ ባደረጉት ጨዋታ ላይ የሰርቢያው ኒማኒያ ማቲች እና የኮስታ ሪካው ረዳት አሰልጣኝ ሉዊስ ማሪን በጨዋታው መጠናቀቂ ደቂቃዎች ላይ የፈጠሩትን ግጭት ሲያበርድ መታየቱ የሚታወስ ነው፡፡
ዴንማርክ በመጀመሪያ ጨዋታዋ ፔሩን በየሱፍ ፖልሰን ግብ 1-0 የረታች ሲሆን ተጋጣሚዋ አውትራሊያ በበኩሏ በመጀመሪያ ጨዋታዋ በፈረንሳይ ተሸንፋለች።