በጊዚያዊነት ተበትኖ የነበረው የሀዋሳ ከተማ ስብስብ ዛሬ ረፋድ ላይ መደበኛ የልምምድ መርሀ ግብሩን አከናውኗል።
ከአንድ ሳምንት በፊት በክለቡ አሰልጣኞች እና ቡድን መሪ ላይ በአንድአንድ ግለሰቦች በተሰነዘረባቸው ማስፈራርያ እንዲሁም በከተማዋ በነበረው አለመረጋጋት ሳቢያ ከልምምድ ርቀው የቆዩት የሀዋሳ ከተማ ቡድን አባላት ከስምንት ቀናት በኃላ ዛሬ ረፋድ አራት ሰዓት ወደ ልምምድ ተመልሰዋል። በተፈጠረው ሁኔታ አዲስ አበባ ለመቆየት ተገደው የነበሩት አሰልጣኝ ውበቱ አባተም ወደ ከተማዋ በመመለስ የቡድኑን ልምምድ መምራት ችለዋል።
በ27ኛው ሳምንት በዚሁ ችግር ምክንያት ያልተካሄደው የሀዋሳ ከተማ እና ኢትዮጵያ ቡና ጨዋታ የፊታችን ሰኞ በዘጠኝ ሰአት የሚደረግ ሲሆን ቡድኑ ዛሬ ዳግም ተሰብስቦ ወደ ልምምድ ማምራቱ ለሰኞው ጨዋታ ብቁ እንዲሆን እንደሚረዳው ይታሰባል። በደረጃ ሰንጠረዡ በ34 ነጥቦች 8ኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው ሀዋሳ ከተማ በቀሪ የሊጉ መርሀ ግብር በሜዳው ኢትዮጽያ ቡናን ከገጠመ በኃላ ከአርባምንጭን ከተማ ፣ ወልዋሎ ዓ.ዩ እና ቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር የሚገናኝ ይሆናል።