አዲሱ የፌዴሬሽን የፕሬዝዳንት እና የስራ አስፈፃሚ አባላት ትላንት በነበረው መደበኛ ስብሰባቸው የፌዴሬሽኑ የአሰራር እና አደረጃጀት ችግሮችን የሚፈትሽ እና የመፍትሄ አቅጣጫዎችን በጥናታቸው እንዲያስቀምጡ አራት ግለሰቦችን በመምረጥ ኮሚቴ አቋቁሟል።
ሰኔ 14 የተሰበሰበው አዲሱ የፌዴሬሽን አመራር በፌዴሬሽን ውስጥ ያለውን ልማዳዊ አደረጃጀትና እያጋጠሙ ያሉ ችግሮችን ለመቅረፍ እንዲሁም ወደ ለውጥ እንቅስቃሴ ለመግባት በማሰብ የፌዴሬሽኑን አሰራር እና አደረጃጀት ዓለም ወደደረሰበት ዘመናዊ አሰራር ለመቀየር እንዲያስችል አሁን ያለውን ሁኔታ በሚገባ መርምረው በቀጣይ መሆን ስለሚገባው አደረጃጀት የመፍትሄ አቅጣጫ እንዲያስቀምጡ በማሰብ በእግርኳሱ የረዥም አመት ልምዳቸውን ከግምት ባስገባ መልኩ አራት ግለሰቦችን መምረጣቸው ታውቋል።
በጥናት ቡድኑ የተካተቱት ግለሰቦች የአአ ከተማ ክለብ ስራ አስኪያጅ አቶ ገዛኸኝ ወልዴ ፣ የአዳማ ከተማ እግርኳስ ክለብ ስራ አስኪያጅ አቶ አንበሴ መገርሳ፣ ከወጣቶች እና ስፖርት አካዳሚ ተወካይ ባለሙያ አቶ ተሾመ ፣ የፌዴሬሽኑ ምክትል የፅህፈት ቤት ኃላፊ ወ/ት መስከረም ታደሰ ሲሆኑ ጉዳዮችን እየተከታተሉ እንዲያስፈፅሙ ከፌዴሬሽኑ ስራ አስፈፃሚ በኩል አቶ ዮሴፍ ተስፋዬ ተመድበዋል።
ለዘመናት የሚነሱትን የፌዴሬሽኑን የተዝረከረከ ባህላዊ አሰራርን ስር ነቀል በሆነ መልኩ መፍትሄ ያመጣል ተብሎ በታሰበው በዚህ ጥናት ላይ ተሳታፊ የሆኑት ግለሰቦች ዛሬ 10:00 ላይ በፌዴሬሽኑ ቢሮ በመገናኘት ስብሰባ የሚያደርጉ መሆናቸውን የሰማን ሲሆን ጥናታቸውን በአጭር ጊዜ ውስጥ በማጠናቀቅ በዝርዝር ለፌዴሬሽኑ ያቀርባሉ ተብሎ ይጠበቃል።