በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ተስተካካይ መርሐ ግብር ዛሬ ሀዋሳ ላይ ይደረጋል ተብሎ የተጠበቀው የሀዋሳ ከተማ እና ኢትዮጵያ ቡና ጨዋታ ወደ አዳማ መዞሩን ባለሜዳው ሀዋሳ ከተማ ተቃውሟል።
ባለፈው ሳምንት ሀዋሳ ላይ በነበረው ያለመረጋጋት ምክንያት ሳይካሄድ የቀረው ጨዋታ ፌድሬሽኑ ባወጣው መርሐ ግብር መሰረት ዛሬ 9 ሰአት ላይ ይደረጋል ተብሎ ቢጠቅም የክልሉ ፖሊስ ለሚፈጠሩ ችግሮች ኃላፊነት እንደማይወስድ መግለፁን ተከትሎ ከነገ በስቲያ (ረቡዕ) በአዳማ አበበ ቢቂላ ስታድየም እንዲደረግ መወሰኑ ይታወቃል። ይህ ውሳኔም ተገቢ አይደለም የሚል የቅሬታ ደብዳቤ ሀዋሳ ከተማ ለፌዴሬሽኑ እንዳስገባ የክለቡ ስራ አስኪያጅ አቶ ጠሀ አህመድ በተለይ ለሶከር ኢትዮጵያ ተናግረዋል። “እኛ ከነበረብን የቡድን መበታተን ከተሰበሰብን በኃላ በሚገባ ስንዘጋጅ ነበር። ጨዋታውም እንደሚደረግ ነበር የምናውቀው። ለኛ የደረሰን መረጃም አልነበረም። እኛ ጨዋታውን ለማድረግ አስበን ፌዴሬሽኑ ሆን ብሎ ለመቀየር እና የእኛን ቡድን ለመጉዳት ያደረገው ነው። ” ብለዋል።
አቶ ጠሀ አክለውም የሚከተሉት ጉዳዮችን በደብዳቤው እንዳካተቱ ገልፀዋል። ” ክለቡ የሜዳ አድቫንቴጁን እንዲያጣ ተደርጓል። በለመድነው ደጋፊ ፊት ጨዋታ እንዳናከናውን ከመደረጉ በተጨማሪ የሜዳው ለውጥ ያልታሰበ እና እስከ 80 ሺህ ብር ወጪ የሚያስወጣ በአጠቃላይ የተጠቃሚነት መብታችንን በሙሉ ያጣንበት ነው። ይህ መሆኑ ደግሞ ሁሉም ውጤት በሚፈልግበት አጣብቂኝ ሰዓት ለበርካታ ጉዳት የሚዳርገን ነው። ” ብለዋል።