በ25ኛ ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ሊደርግ ታስቦ በአሰልጣኝ ንጉሴ ደስታ ድንገተኛ ህልፈት ምክንያት ወደ ዛሬ የተላለፈው የደደቢት እና አርባምንጭ ጨዋታ ዛሬ በአዲስ አበባ ስታዲየም ተደርጎ ባለሜዳዎቹ ሁለት ለአንድ በሆነ ውጤት አሸንፈዋል።
ቀዝቃዛ የአየር ሁኔታ በተካሄደው ጨዋታ በመጀመሪያው አጋማሽ እንደ አየሩ ሁሉ ቀዝቀዝ ያለ የሜዳ ላይ ፉክክር የተስተዋለ ሲሆን ባለሜዳዎቹ በ4-3-3 እንግዶቹ ደግሞ በ4-2-3-1 አሰላለፍ ወደ ሜዳ ገብተዋል። በ27ኛው ሳምንት በቅዱስ ጊዮርጊስ ሽንፈት ያስተናገደው ደደቢት ግብ ጠባቂ ቦታ ላይ አማራህ ክሌመንትን ከቅጣት መልስ በታሪክ ጌትነት ሲተካ ኤፍሬም አሻሞም በየአብስራ ተስፋዬ ምትክ ወደ መጀመሪያ አሰላለፍ መጥቷል። አርባምንጭ ከተማ በበኩሉ አዳማ ላይ ነጥብ ከተጋራበት የመጀመሪያ አሰላለፍ በተለየ ምንተስኖት አበራ እና ብርሀኑ አዳሙን በወንደሰን ሚልኪያስ እና በረከት አዲሱ ቦታ ተክቷል።
በጨዋውታ ደደቢቶች በመጀመሪያው አጋማሽ የበላይነቱን የወሰዱ ሲሆን አርባምንጭ ከተማዎች ደግሞ ተከላክለው በሚገኙ የመልሶ ማጥቃት ዕድሎች እና አንዳንዴ ደደቢቶች ኳሷን ሲቀባበሉ በሜዳው አለመመቸት ምክንያት ሲበላሽባቸው በሚገኙ አጋጣሚዎች ከሚሰነዘሩ ጥቃቶች ውጪ ብዙም የተጠና አጨዋወት ያልተገበሩ ሲሆን በመከላከሉ በኩል ግን የደደቢት የአማካይ መስመር ተጨዋቾች ኳሷን ወደ ፊት መስመር እንዳያሳልፉ ክፍተቶችን ሲዘጉ ይታዩ ነበር። አርባምንጭን መሪ ለማድረግ ተቃርባ በነበረችው የጨዋታው የመጀመሪያ ሙከራ ፀጋዬ አበራ ከእንዳለ ከበደ ያገኘውን ኳስ ወደ ግብ ሲሞክር የደደቢት ተከላካዮች አውጥተውበታል። ከሁለት ደቂቃዎች በኃላ በተመሳሳይ ፀጋዬ አበራ ከፍፁም ቅጣት ምት ክልል ውጪ አክሮባቲክ በሆነ መንገድ የሞከረው ኳስም ሌላ የሚነሳ የግብ ማግባት አጋጣሚ ሲሆን ኳሷ ሃይል ስላልነበራት በቀላሉ በደደቢት ግብ ጠባቂ አማራህ ክሊመንት ቁጥጥር ስር ውላለች። በ26ኛው ደቂቃ የአርባምንጭ ግብ ጠባቂ ፅዮን መርዕድ ለመሃል ተከላካዩ ተመስገን ካስትሮ የሰጠውን ኳስ ተመስገን ይዞ ለማለፍ ሲሞክር አቤል ያለው ቀምቶት መልሶ ለመቀማት በሚያደርገው ጥርረት ጥፋት በመስራቱ በተገኘ የፍፁም ቅጣት ምት ደደቢቶች በጌታነህ ከበደ አማካኝነት ቀደሚ የሆኑበትን ጎል አግኝተዋል።
ከጎሉ መቆጠር በኃላ ደደቢቶች አሁንም ተጨማሪ ግብ ለማስቆጠር በጌታነህ ከበደ እና አቤል ያለው አማካኝነት ተደጋጋሚ ሙከራዎችን ያደረጉ ሲሆን በ38ኛው ደቂቃ ጥረታቸው ፍሬ አፍርቶ ሁለተኛ ጎል አስቆጥረዋል። ስዩም ተስፋዬ ከቀኝ መስመር የተሻገረለትን ኳስ በሚገርም የአጨራረስ ብቃት (Half Volly) ግብ ያስቆጠረ ሲሆን በግቧም ደደቢትን በራስ መተማመኑን ከፍ ማድረግ ችሏል። የመጀሪያው አጋማሽ ሊጠናቀቅ ጭማሪው ሰዓት ላይ በአርባምንጭ ተከላካዮች የትኩረት ማነስ ምክንያት ኤፍሬም አሻሞ ተጨማሪ ግብ የማስቆጠር አጋጣሚ አግኝቶ የነበረ ቢሆንም ለብርሃኑ ቦጋለ አቀብሎት ብርሃኑ ሳይጠቀምበት ቀርቷል። .
በሁለተኛው አጋማሽ ይበልጥ ተጠናክረው የመጡት አርባምንጮች ከጨዋታው ከተቻለ ሶስት ነጥብ ካልተቻለ አንድ ነጥብ ይዞ ለመውጥት ሙሉ ለሙሉ በሚቻል መልኩ አጥቅተው የተጫወቱ ሲሆን በርከት ያሉ የግብ ማግባት አጋጣሚዎችንም ፈጥረዋል። በ56ኛው ደቂቃ እንዳለ ከበደ ከተካልኝ ደጀኔ ጋር አንድ ሁለት ተቀባብሎ ወደ ደደቢቶች የፍፁም ቅጣት ምት ክልል ውስጥ መግባት የቻሉ ሲሆን በእንዳለ ሙከራም ኳሷ ለጥቂት የግቡን አግዳሚ ታካ ወደ ውጪ ወጥታለች። ከአራት ደቂቃዎች በኃላ አርባምንጮች በፀጋዬ አበራ አማካኝነት ሌላ የግብ ማግባት አጋጥሚ ያገኙ ሲሆን ተጨዋቹ ኳሷን ፊት ለፊት በመምታቱ ግብ ጠባቂው በቀላሉ ተቆጣጥሮበታል።
ደደቢቶች ያገኙትን የማሸነፍ አጋጣሚ ከእጃቸው ላለማስወጣት በሁለተኛው አጋማሽ ተከላክለው የተጫወቱ ሲሆን አርባምጮች ለማጥቃት በሚወጡበት ወቅት የሚተውትን ክፍት ቦታ እንኳን ለመጠቀም ሲጥሩ አልተስተዋለም። ይባስ ብሎ በ63ኛው ደቂቃ ስዩም ተስፋዬ ኳስ በሌለበት በመማታቱ በቀጥታ ቀይ ካርድ ከወጣ በኃላ ይበልጥ ወደ ጎል ለመሄድ ባለመፈለጋቸው እና በራሳቸው የሜዳ ክፍል የቁጥር ብልጫ ስለተወሰደባቸው የመስመር አጥቂው ኤፍሬም አሻሞን አስወጥተው የመከላከል ባህሪ ያለውን ፋሲል አበባየሁን በማስገባት ተከላክለው ለመጫወት ሞክረዋል።
ጫና ማሳደራቸው አሁንም የቀጠሉት አርባምንጮች በባዶ ከመሸነፍ ያዳነቻቸውን ኳስ በ78ኛው ደቂቃ በተመስገን ካስትሮ የግንባር ጎል ማግኘት የቻሉ ሲሆን ከግቡም በኃላ ተጨማሪ ግብ ለመስቆጠር ሲጥሩ ተስተውሏል። ወደ መጨረሻው ላይ ደደቢቶች የጨዋታውን ፍጥነት በመቆጣጠር ተረጋግተው በመጫወት እና ሰዓት በማባከን ቀሪውን ጊዜ ያሳለፉ ሲሆን ተሳክቶላቸውም በሜዳቸው ሶስት ነጥብ ይዘው ወጥተዋል። ቡድኑ መጋቢት 21 አዳማ ከተማን ካሸነፈበት ጨዋታ በኋላ የመጀመሪያው የሆነውን ድል አጣጥሞ 37 ነጥቦች ላይ በመድረስ የነበረበትን ስጋት አቃሏል።
የአሰልጣኞች አስተያየት
ም/አሰልጣኝ – ጌቱ ተሾመ (ደደቢት)
የዛሬው ጨዋታ ለኛ ከምንም በላይ አስፈላጊያችን ነበር። ምክንያቱም ጨዋታዎች ካሸነፍን ረጅም ጊዜ ስለሆነን ወደ አሸናፊነት ለመምጣት እንፈልግ ነበር። ያሰብነውን ደግሞ በማድረጋችን እጅግ ደስተኞች ነን። በሁለተኛው አጋማሽ ተከላክለን የተጫወትነው ተገደን ነው። ሜዳውም እኛ ያሰብነውን የጨዋታ ስትራቴጂ ለመተግበር አይመችም። የቁጥር ብልጫም ነበረብን ስለዚህ በተቻለን መጠን ተከላክለን ያገኘነውን የማሸነፍ አጋጣሚ አስጠብቀን ለመውጣት ሞክረናል።
የአርባምንጭ አሰልጣኝ ስሜታችን በመጎዳቱ እና በእለቱ በነበረው የዳኝነት ውሳኔ ደስተኛ ባለመሆናችን አስተያየት አንሰጥም ብለዋል።