ከ27ኛው ሳምንት የሊጉ መርሀ ግብሮች መካከል በፀጥታ ችግር ምክንያት ሳይካሄዱ የቆዩት ሁለት ጨዋታዎች ነገ አዲስ አበባ እና አዳማ ላይ እንደሚደረጉ ይጠበቃል። በዛሬው ቅድመ ጨዋታ ዳሰሳችንም እነዚህን ጨዋታዎች ተመልክተናቸዋል።
ሀዋሳ ከተማ ከ ኢትዮጵያ ቡና
አዳማ ከተማ ላይ ነገ በ9፡00 እንዲደረግ የተወሰነው ይህ ጨዋታ በመጀመሪያ በተዘዋወረበት ወቅት ጨዋታውን ካለማድረግ ባለፈ በተፈጠረው ሁኔታ ልምምድ እስከማቋረጥ ደርሶ የነበረው ሀዋሳ ከተማ ካሳለፍነው ሳምንት ሀሙስ ጀምሮ ወደ መደበኛ ልምምዱ ሲመለስ ኢትዮጵያ ቡና ደግሞ በዛው እለት በኢትዮጵያ ዋንጫ አርባምንጭን ጥሎ ወደ ግማሽ ፍፃሜ ማለፉ የሚታወስ ነው። 5ኛ ደረጃ ላይ ተቀመጠው ቡና ከመሪዎቹ ጋር የአምስት ነጥቦች ርቀት ላይ የተቀመጠ ሲሆን በዋንጫ ፉክክሩ ውስጥ ለመቆየት በቀሪ ጨዋታዎቹ ምንም ስህተት መስራት አይኖርበትም። በመሆኑም በ25ኛው ሳምንት ከሶዶ በድል እንደተመለሰ ሁሉ በተሻለ ሁኔታ ለመዲናዋ በምትቀርበው አዳማ በሚደረገው በዚህ ጨዋታ ላይም ተመሳሳይ ውጤት የማስመዝገብ ግዴታ ይኖርበታል። ከ23ኛው ሳምንት በኋላ ከውጤት ርቆ የቆየው ሀዋሳ ከተማም ከጨዋታው ሙሉ ነጥቦችን ማስመዝገብ ይጠበቅበታል። ይህ የማይሆን ከሆነ እና ከወራጅ ቀጠናው ጋር ያለውን ርቀት አሁን ካለበት በላይ ማስፋት ካልቻለ የመጨረሻዎቹን ሳምንታት በከባድ የመውረድ ስጋት ውስጥ የመግባት ዕጣ ሊገጥመው ይችላል። ድል ከቀናው ደግሞ ለዋንጫ ፉክክሩ ቢርቅም በሰንዝጠረዡ ወገብ ላይ የተቀመጡትን እና ስጋት የሌለባቸው ፋሲል ከተማን እና ደደቢትን ይቀላቀላል።
በጉዳት ረገድ በመጠኑ እፎይ ያለው ሀዋሳ ከተማ ዳንኤል ደርቤ ፣ ዮሀንስ ሴጌቦ እና ቸርነት አውሽ ሲመለሱለት አለምአለም ተስፋዬ እና ደስታ ዮሀንስ ግን አሁንም አላገገሙም። ከዚህ ውጪ ጋብርኤል አህመድ ከቅጣት ሲመለስ ሶሆሆ ሜንሳ በተቃራኒው በቅጣት ጨዋታው ሲያልፈው ሲላ መሀመድ ደግሞ የመኖሪያ ፍቃዱ በማለቁ እና ነገ ከሀገር የሚወጣ በመሆኑ ከስብስቡ ውጪ ሆኗል። በሌላ በኩል ከኢትዮጵያ ቡና ጨዋታው የሚያመልጠው ብቸኛው ተጨዋች ጉዳት ላይ የሚገኘው አቡበከር ነስሩ ነው።
በተለያዩ ምክንያቶች የሶስትዮሽ የአማካይ ክፍሉ ላይ ለውጦችን እያደረገ የሚገኘው ሀዋሳ ከተማ የኳስ ቁጥጥርን መሰረት ያደረገው የማጥቃት ሂደቱ ተዳክሞ እየታየ ይገኛል። የቡድኑ የፈጠራ ሀላፊነትም በወጥነት አማካይ ክፍሉን በመምራት ላይ ለሚገኘው ታፈሰ ሰለሞን ላይ የተጣለ ይመስላል። የመስመር ተከላካዮቹ ጉዳትም የቡድኑ የማጥቃት ሂደት ለመዳከሙ ሌላው ምክንያት እንደሆነ መናገር ይቻላል። ሆኖም በመስመር አጥቂነት የሚሰለፉት ዳዊት ፍቃዱ እና ፍሬው ሰለሞን በነገው ጨዋታ ሁለቱን ኮሪደሮች ከነታፈሰ በሚነሱ ኳሶች በመጠቅም ተጭነው ለመጫወት እንደሚሞክሩ ይጠበቃል። የማጥቃት ተሳትፏቸው ከፍተኛ ከሆነው የኢትዮጵያ ቡና የመስመር ተከላካዮች ጀርባ ለመግባት የሚያደርጉት ጥረትም የመስመር ተከላካዮቻቸው ተሳትፎ ከታከለበት የተሻለ ጥንካሬ ያላብሳቸውል። ከዚህ በተጨማሪ ለፈጣኑ እና ወጣቱ አጥቂ እስራኤል እሸቱ የሚላኩ ኳሶች ለቡድኑ ከሚሰጡት የማጥቃት አማራጭ ሌላ ተጨዋቹ ከኢትዮጵያ ቡና የመሀል ተከላካዮች ጋር የሚያደርገውን ፍልሚያ አጓጊ ያደርገዋል።
ከሀዋሳ በተለየ አማካይ ክፍሉን ታታሪ በሆኑ ተጨዋቾች በማዋቀር እና የተጋጣሚን የመሀል ሜዳ እንቅስቃሴ በመግታት በመስመሮች በኩል በሚሰነዘሩ ጥቃቶች ላይ ትኩረት ማድረግ የጀመረው ኢትዮጵያ ቡና የተለየ መልክ እየተላበሰ ነው። መሀል ሜዳ ላይ ብዙ ኳስ የማይዝ እና በፍጥነት በተጋጣሚ ሜዳ ላይ የሚደርስ ቡድን እየሆነ ከመምጣቱ ባሻገር ተሻጋሪ ኳሶችን መጠቀም እና አስፈላጊ ሲሆን በጥልቀት መከላከልንም ምርጫው ሲያደርግ ይስተዋላል። ውጤት እያገኘበት የሚገኘው የቡድኑ ይህ አካሄድ ነገም ግቦችን የሚያገኝ ከሆነ የሚደገም ይመስላል። በርግጥ ቡድኑ ወደ መጥቃት በሚሸጋገርባቸው ወቅቶች ላይ ተጋጣሚ ክፍትቶችን ሲፈጥር ወደ መስመሮች ያደላ የማጥቃት ምርውጫ በነገው ጨዋታ ላይ የሚስተዋል ከሆነ ተገማች ሊያደርገው እንደሚችል ይታሰባል። በዚህ ውስጥ ግን አማኑኤል ዮሀንስ የታፈሰ ሰለሞንን እንቅስቃሴ ለመግታት የሚያደርገው ጥረት እንዲሁም የሚኪያስ መኮንን እና ሳሙኤል ሳኑሚ የመስመር ጥቃት ከሀዋሳ የመስመር ተከላካዮች ጋር የሚገናኙባቸው ፍልሚያዎችም ትኩረትን የሚስቡ መሆናቸው አይቀርም።
የእርስ በእርስ ግንኙነት እና እውነታዎች
– ሊጉ በአዲስ ፎርማት ከተጀመረበት 1990 ጀምሮ ሳይወርዱ የቆዩት ሁለቱ ቡድኖች እስካሁን 39 ጊዜ ሲገናኙ እኩል 12 ጊዜ ተሸናንፈዋል። ቀሪዎቹ 15 ጨዋታዎች ደግሞ በአቻ ውጤት የተጠናቀቁ ነበሩ። በነዚህ ጊዜያት ኢትዮጵያ ቡና 46 ጊዜ ኳስ እና መረብን ሲያገናኝ ሀዋሳ ከተማም ሶስት የፎርፌ ግቦችን ጨምሮ 42 ግቦችን ማስመዝገብ ችሏል።
– ከ1996 ጀምሮ ቡድኖቹ የተናኙባቸው ጨዋታዎች በሙሉ ቢያንስ አንድ ግብ የተቆጠሩባቸው ነበሩ።
– ሀዋሳ ከተማ በመጨረሻዎቹ ሶስት ጨዋታዎቹ ያገኘው አንድ ነጥብ ብቻ ሲሆን ግብም የቀናው በሲዳማ ቡናው ጨዋታ ብቻ ነበር።
– ኢትዮጵያ ቡና ባለፉት አራት ጨዋታዎች የጣለው ሁለት ነጥብ ብቻ ሲሆን በሁሉም ጨዋታዎች ግብ ማስቆጠር ችሏል።
ዳኛ
– ኢንተርናሽናል ዳኛ ብሩክ የማነብርሀን ይህን ጨዋታ በመሀል ዳኝነት የሚመራው ይሆናል።
ወላይታ ድቻ ከ ወልዋሎ ዓ.ዩ
ወደ ቦዲቲ እንዲዞር ተደርጎ የነበረው ይህም ጨዋታ በድጋሜ ማስተካከያ ተደርጎበት ወደ አዲስ አበባ ስታድየም መጥቷል። ጨዋታው ከተላለፈ በኋላ ባሳለፍነው ሳምንት ቅዱስ ጊዮርጊስን በኢትዮጵያ ዋንጫ ገጥሞ የነበረው ወላይታ ድቻ ከደካማ አቋም ጋር ከውድድሩ ውጪ ሆኗል። ፋሲል ከተማን ከረታበት የ21ኛ ሳምንት ጨዋታ በኋላ ወደ አሸናፊነት መመለስ የተሳነው ወላይታ ድቻ ቀስ በቀስ በመንሸራተት አሁን የአደጋ ዞን ውስጥ ገብቷል። ከ30 ነጥብ ማለፍ ያልቻለው ድቻ አሁን ያለበትን ስጋት ለመቀነስ ከዚህ ጨዋታ ሙሉ ነጥብ ያስፈልገዋል። ላለመውረድ በሚደረገው ትግል ውስጥ ከገባ የሰነበተው ወልዋሎ ዓ.ዩም ከተጋጣሞው ዕኩል ነጥብ ይዟል። ቡድኑ ያለበት 9 የግብ ዕዳም ተመሳሳይ ነጥብ ካላቸው ቡድኖች በታች አድርጎታል። በመሆኑም ከረጅም ጊዜያት በኋላ በአንፃራዊነት የተሻለ በሚባል ርቀት የአደጋውን ዞን ለመራቅ ይህ ጨዋታ እጅግ አስፈላጊው ይሆናል። ጨዋታው ሁለቱም ተጋጣሚዎች ተመሳሳይ ስጋት እና ተስፋ ይዘው የሚገናኙበት ጨዋታ በመሆኑም ከባድ ፉክክር እንደሚያስተናግድ ይጠበቃል።
ወላይታ ድቻ ተከላካዮቹን ውብሸት አለማየሁ እና ተስፉ አሰልያስን በጉዳት ሳቢያ ሲያጣ በአንፃሩ ሀይማኖት ወርቁ እና ጃኮ አራፋት ከጉዳት ተክሉ ታፈሰ ደግሞ ከቅጣት ይመለሱለታል፡፡ በወልዋሎ ዓ.ዩ በኩል ግን ከግብ ጠባቂው በረከት አማረ እና አሳሪ አልመሀዲ ቅጣት በስተቀር ሙሉ ስብስቡ ለጨዋታው ብቁ እንደሚሆን ይጠበቃል።
ቁልፍ ተጨዋቾቹን በቅዱስ ጊዮርጊሱ የኢትዮጵያ ዋንጫ ጨዋታ ላይ ያሳረፈው ወላይታ ድቻ ነገ ከዚህ ጨዋታ እጅግ በተሻለ አቋም ወደ ሜዳ እንደሚገባ ይጠበቃል። በጨዋታው ማጥቃትን መሰረት ያደረገ አቀራረብ እንደሚኖረው የሚጠበቀው ድቻ የፊት አጥቂው ጃኮ አራፋትን መቋጫ በማድረግ በፈጣን የማጥቃት ሽግግር ላይ መሰረት ያደረገ አቀራረብ እንደሚኖረው ይገመታል። በዚህ ሂደት ውስጥም የአብዱልሰመድ አሊ እና በዛብህ መለዮ የአማካይ ክፍል ጥምረት አንድ የተከላካይ አማካይ ከሚጠቀመው የተጋጣሚያቸው አሰላለፍ ላይ የበላይ ለመሆን በማጥቃት ሽግግሩ ወቅት የሚኖራቸው ፍጥነት እጅግ ወሳኝ ይሆናል። ከዚህ በተጨማሪ እየተዳከመ የመጣው የቡድኑ የመስመር አማካዮች የማጥቃት ተሳትፎ የርቀት ሙከራዎችን ከማድረግ ባለፈ ወደ ውስጥ እየጠበበ በሚመጣ እንቅስቃሴ ለሁለቱ አማካዮች እና ለጃኮ አራፈት በቀረበ መልኩ የቅብብል አማራጮችን መፍጠር ወሳኝ እንደሆነ መናገር ይቻላል።
በኳስ ቁጥጥር ላይ መሰረት ያደረገው ወልዋሎ ዓ.ዩ በዚህ ጨዋታ ጥንቃቄንም ያካተተ አቀራረብ እንደሚኖረው ይገመታል። በመሆኑም የቡድኑ ዋነኛ የማጥቃት መሳሪያዎች የሆኑት ሁለቱ የመስመር አትቂዎች ፕሪንስ ሰቨሪንሆ እና አብዱርሀማን ፉሰይኒ የድቻን የመስመር ጥቃት ከመነሻው የማፈን እንዲሁም ለአማካይ ክፍሉ በመቅረብ የቅብብል አማራጮችን የመስጠት እንዲሁም ኳስ በመንጠቅ ሂደቱ ላይ እገዛ የማድረግ ሀላፊነት ሊኖርባቸው ይችላል። ከዚህ ጎን ለጎን ሁለቱ አጥቂዎች ከሪችሞንድ አዶንጎ ጋር የሚፈጥሩት ጥምረት ቡድኑ የድቻን የተከላካይ መስመር ከሁለቱ ኮሪደሮች በመነሳት ለመፈተን ጥቅም ላይ ሊውል ይችላል። የአፈወርቅ ሀይሉ እና ዋለልኝ ገብሬ የመሀል ሜዳ ጥምረትም ኃይማኖት ወርቁ እና አብዱልሰመድ አሊን በቁመት ከሚያጣምረው የድቻ የአማካይ መስመር ጋር ብርቱ ፍልሚያ እንደሚያደርጉ ይጠበቃል።
የእርስ በእርስ ግንኙነት እና እውነታዎች
– የሁለቱ ቡድኖች የመጀመሪያ የሊግ ግንኙነት 1-1 የተጠናቀቀ ሲሆን አሁን ከቡድኑ ጋር የማይገኘው ሙሉአለም ጥላሁን ለወልዋሎ ዓ.ዩ ዳግም በቀለ ደግሞ ለወላይታ ድቻ ግቦቹን አስቆጥረዋል።
– ወላይታ ድቻ ካለፉት ሰባት ጨዋታዎች ከአቻ ውጤቶች የተገኙ ሶስት ነጥቦችን ብቻ ሲያሳካ ግብ ያስቆጠረውም ከሲዳማ ቡና 2-2 በተለያየበት ጨዋታ ላይ ብቻ ነው።
– መሻሻሎችን እያሳየ የሚገኘው ወልዋልም ዓ.ዩ ከመጨረሻዎቹ ሶስት ጨዋታዎች ሰባት ነጥቦችን የሰበሰበ ሲሆን ሁሉም ጨዋታዎች ላይ አንድ አንድ ግቦችን ማስቆጠር ችሏል።
ዳኛ
– ጨዋታውን በመሀል ዳኝነት ለመምራት ሀላፊነት የተሰጠው ለኢንተርናችናል ዳኛ ለሚ ንጉሴ ነው።